አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ከምድረገጽ እስኪጠፋ ትግላቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በወልቃይት ጠገዴ የከፋኝ መሥራች አባላት ገለጹ።

357

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 23/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የዘመናት ምኞቱን ለማሳካት ሐምሌ 1972 ዓ.ም በካቦ እና በታንኳ ተከዜን መሻገር ጀመረ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ትግላቸውን ጀመሩ፣ ካቦውንም በጠሱ፣ ታንኳዋንም ከጥቅም ውጪ አደረጉ፣ ሽምቅ ውጊያ በመክፈትም አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ መመከት ቀጠሉ። ሕዝቡ በአንድ በኩል ከአፋኙ የደርግ ሥርዓት ለመላቀቅ በሌላ በኩል ደግሞ የአማራ ሕዝብ የምንጊዜም ጠላት የሆነው የትግራይ ወራሪ ቡድን ሥር እንዳይሰድ ነው ትግል የጀመሩት።

የሕዝቡ መደራጀት የደርግ መንግሥት ስላላስደሰተው ርምጃ መውሰድ በጀመረ ጊዜ 100 ገደማ በሚሆኑ ሰዎች አብደራፊ ላይ የተመሰረተው የከፋኝ ቡድን 4 ሺህ 600 ደርሶ እንደነበር ማወቅ ተችሏል።

ከፋኞች ደርግ የሚያደርስባቸውን ጥቃት ለመመከት ባደረጉት የሽምቅ ውጊያ የደርግን ሠራዊት ማርከው እንደነበር የከፋኝ መሥራች አባሉ ታጋይ ካሳሁን ሲሳይ አስታውሰዋል።

ከዚያም ተገንጣዩን የትግራይ ወራሪ ቡድን በመፋለም ትግላቸውን አጠናክረው ቀጠሉ።

አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በወልቃይት በኩል ጎንደርን የመቆጣጠር ሕልሙ በከሸፈበት ጊዜ በወሎ በኩል አድርጎ አዲስ አበባን መቆጣጠሩን አወጀ። የከፋኝ ቡድኑ ትግል ግን ከታወጀ በኋላም ቀጥሏል። ወያኔ በትረ ስልጣኑን ከተቆጣጠረች በኋላ ለከፋኝ አባላት ምህረት ማድረጓን ብታውጅም ከተወሰኑት በስተቀር የተቀበለ አልነበረም። የሽብር ቡድኑ ሴራ ቀድሞ ገብቷቸው ስለነበር አብዛኛው ወደ ሱዳን ተሰድዶ ትግሉን ቀጠለ። ሱዳን ሆኖ የሚታገለውን ኀይል ለመያዝ አሸባሪው ትህነግ ከሱዳን መንግሥት ጋር አሻጥር በሠራ ጊዜም ወደ ኤርትራ በርሃ ተሻግረው ታግለዋል፤ ሕዝቡንም አታግለዋል።

አሸባሪው ትህነግ ለፍትሕ፣ ለነጻነትና ለእኩልነት እታገላለሁ በሚል ድብቅ አጀንዳውን ለማሳካት እንቅስቃሴ እንደጀመረ አባታቸውን ጨምሮ 51 ትላልቅ ሰዎችን እንዳጠፋ የነገሩን ደግሞ የከፋኝ ቡድኑ አባል ልዑል አሰፋ ኀይሌ ናቸው።

ስልጣኑን ተጠቅሞ በማስፈራራት እና የተወሰኑ ሰዎችን በጥቅም በመግዛት ሰዎችን ሲያደራጅ የሚቃወሙትን መግደል፣ ማሰር፣ ማሰቃየት፣ የኢኮኖሚ አሻጥርን ጨምሮ በርካታ በደሎችን አድርሷል። የኢትዮጵያ ሕዝብ የቡድኑን አደገኛነት በውል ባልተገነዘበበት ጊዜ በነበረው ትግል ወያኔ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ቢደርስባትም እንደ ሕዝብ ከደረሰው ህልቆ መሳፍርት የሌለውን በደል ውጪ አንድ ሺህ የከፋኝ አባላት መስዋእትነት ከፍለዋል።

ታጋዮቹ በትግላቸው ጽናት ከሕዝቡ ጋር በመሆን በጉልበት የተወሰደበትን ማንነት አስመልሰዋል። አሁን እንደ አዲስ ተወልደን መኖር ጀምረናል ብለዋል ታጋዮቹ።

“ከዚህ በኋላ ወያኔ ተመልሳ ወልቃይትን ትረግጣለች ማለት የተፈጨ እህል ይበቅላል እንደማለት ነው” ያሉት ታጋዮቹ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን እስከመጨረሻ እንዲጠፋ የተጀመረው ትግል ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

በመስዋእትነት ማንነቱንና ነጻነቱን ያስከበረው የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ከምድረገጽ እስኪጠፋ ትግላቸውን እንደሚያጠናክርም ተናግረዋል።

አሸባሪው የትህነግ ቡድን የአማራን ሕልውና ለማጥፋት ቆርጦ ስለተነሳ አጥብቆ መታገል ይገባል ነው ያሉት።

ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከርና ብልሹ አሠራር ማጥፋት ለሕልውና ዘመቻው በአጭር ጊዜ መጠናቀቅ ወሳኝ ነው ብለዋል።

ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleትግላችን ፍትሐዊ ነውና ኢትዮጵያ ማሸነፏን ትቀጥላለች!
Next articleአሸባሪው እና ወራሪው የትህነግ ቡድን ከእያንዳንዱ የቤተሰብ አባላት ወደ ጦርነት በግዴታ እንዲገቡ እያደረገ እንደሚገኝ በማይጠብሪ ግንባር እጃቸውን የሰጡ የቡድኑ አባላት ገለጹ፡፡