“ዮ መስቀላ” የጋሞዎቹ የዘመን መለወጫ::

744

ባሕር ዳር፡ መስከረም 17/2012 ዓ/ም (አብመድ) መስቀል በጋሞዎች በኩል በጉጉት ተጠባቂና በሀገራችን ልዩ የበዓሉ ድባብ ከሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የአካባቢው ሰዎች ‹ዮ መስቀላ› ብለው ይጠሩታል፡፡ ‹መስቀል እንኳን ደህና መጣልን› ማለት ነው፡፡ የሕዝቡ የዘመን መለወጫም በመሆኑ በዓሉን ልዩ ያደርገዋል፡፡

ለበዓሉ ሲባል ዓመቱን ሙሉ ዝግጅት ይካሄዳል፡፡ እናቶችና አባቶች እቁብ በመጣል ዝግጅቱን ረዥም ጉዞ ያስኬዱታል፡፡ እናቶች ለመስቀሉ ቡላ፣ ወተት፣ ቅንጬ ለመሥራት የሚያገለግለውን ገብስ፣ በቆሎ፣ ቅቤና ቅመማ ቅመም ለማዘጋጀት ዓመቱን ሙሉ እቁብ ሲጥሉ ይከርማሉ፡፡ አባቶች ደግሞ የሚጥሉት እቁብ ለሰንጋ መግዣነት የሚውል ነው፡፡

ወጣቶች ለደመራ እንጨት በመሰብሰብና በማሰናዳት፣ ለከብቶች ሳር አጭዶ በመከመርና ጉልበት የሚጠይቁ ሥራዎች ላይ በመሳተፍ ያግዛሉ፡፡ ዮ መስቀላ በጋሞ ብሔረሰብ በኩል ሁሉም ቂሙን ረስቶ በእርቅ፣ በይቅርታ፣ በሠላምና በአብሮነት ከክፉ ተግባርና ሐሳብ ወጥቶ በአዲስ መንፈስ የሚታደስበት ጊዜ ነው፡፡
የዮ መስቀላ በዓል በዞኑ ረዘም ላለ ጊዜ ይዘልቃል፡፡ “ኡሻቻ” (ቀኝ) ይሉታል በሀገሬው ቋንቋ ከሰሜኑ የጋሞ ዞን ተነስቶ ወደ ደቡቡ ክፍል በመጓዝ በየአካባቢው በዓሉ በቅደም ተከተል ይከበራል፡፡

ዝግጅቱ ለሰዎች ብቻ ሳይሆን ከብቶችን በማካተትና በማሰብ የሚከናወን ነው፡፡ በበዓሉ ሰሞን ሁሉም ወደ በዓሉ የሚሄዱ በመሆኑ ሰኔ ወር ላይ ለመስቀል ሰሞን ከብቶች የሚመገቡት ድርቆሽ ይዘጋጅላቸዋል፡፡ ሕጻናት ከብቶቹን ወደሚመገቡበት ስፍራ ካሰማሩ በኋላ በዓሉን በዝማሬ ያደምቁታል፡፡
‹‹ለአዲሱ ዓመት እንኳን አደረሰን፤
እንኳን ለመስቀል በሰላም አደረሰን፤
… … በደስታ አደረሰን፤
ለዚህ ቀን እንኳን አበቃን እያሉ›› ይጨፍራሉ፡፡

በዓመቱ ውስጥ በትዳር ለተሳሰሩ ጥንዶች “የሶፌ” ሥርዓት የሚፈፀመውም በዚሁ ዮ መስቀላ ክብረ በዓል ጊዜ ነው፡፡ “የሶፌ” ሥርዓት በዓመቱ ውስጥ ያገቡ ሰዎች በአካባቢያቸው ባለ ትልቅ ገበያ ገብተው የባል ቅርብ ዘመድ (ሴት) “ማዳ” ወይም ለሙሽራዋ የተበጠበጠ ማር በአራት ዙር አጠጥታ “ካጫ” ታካሂዳለች፡፡ “ካጫ” ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀላቀል ሙሽሮች ሥራ እንዲጀምሩ የሚደረግበት ተግባር ነው፡፡

በጋሞ ባሕል መሠረት ሰኔ ወይም ሐምሌ ላይ ጋብቻ ተፈፅሞ ባልና ሚስት ሥራ አይሰሩም፤ አርፈው የጫጉላ ሕይወት ይመራሉ፡፡ ይሁን እንጅ ይህ በዓል ሙሽሮቹ ከጫጉላ ወጥተው ወደ ሥራ የሚሸጋገሩበት ጊዜም ነው፡፡ ማር መጠጣት ብቻ ሳይሆን ሚስት ቅቤ ትቀባለች፤ በትከሻዋ ግራና ቀኝ ለምለም ሳር ይቀመጥላታል፤ ‹እንዲህ ለምልሚ› የሚል ትርጓሜ አለው፡፡ ይህ የሚከወነው ‹‹አግብተሻል ከባለቤትሽ ጋር በመሆን ወደ ሥራ ግቢ›› በሚል የሚደረግ ምርቃት ስለሆነ ነው፡፡

“የሲዳታ”(መታያ) ወይም በዘመናዊው ዓለም የቁንጅና ውድድር ብለን የምንጠራው ሥርዓትም አለ፤ በዓመት ውስጥ ሁሉም በትዳር የተሳሰሩ ሴቶች ገበያ ላይ ተሰባስበው ይቀመጣሉ፤ ከዚያም ማን ጥሩ እንደለበሰ፣ በጥሩ ሁኔታ እንደተቀለበ (እንደወፈረ)፣ ማን መልከ መልካም እንደሆነ ዳኞች ተሰይመውና “ምሽሬ ሚጫ” (ሙሽሪት ሳቂ) እየተባለ ቆንጆዋ ሴት ትመረጣለች፡፡

“የሹካ” (እርድ) ራሱን የቻለ ሌላ ሥርዓት ነው፡፡ በተመሳሳይ የሰንጋ እርድ ሥርዓቱ በሰፊ ገበያ ላይ ይከናወናል፡፡ ዓመቱን ሙሉ እቁብ በመጣል ገንዘብ ሲያጠራቅሙ የነበሩ አባቶች ለየግል ወይም ለጋራ ከብት ገዝተው ያርዱና ስጋውን ተከፋፍለው ወደየቤቶቻቸው ያቀናሉ፡፡

“ፆምፔ ኬሶ”(የደመራ ሥርዓት) የዮ መስቀላ አንዱ አካል ነው፡፡ ከቀርቀሃ ወይም ከሌላ ግብዓት የተዘጋጀ ችቦ አባዎራዎች በየቤቶቻቸው በር ምረቃ ካካሄዱ በኋላ ይዘው ይወጣሉ፡፡ ወጣቶችም እንደዚሁ ችቧቸውን ይዘው አባቶቻቸውን ተከትለው ይወጣሉ፡፡ አንድ ላይ በመሰባሰብ ደመራውን ያቃጥላሉ፡፡

ሁሉም የማኅበረሰብ ከፍሎች የሚሳተፉበት ሌላው ሥርዓት ደግሞ “ጋዜ” ብለው ይጠሩታል፡፡ በዚህ ሥርዓት ሴቶችና ወንዶች ጭፈራ ያካሂዳሉ፡፡ የፈረስ ጉግስ ውድድር ያደረጋሉ፡፡ በመጨረሻ ደመራ የተደረገበትን ቦታ ሦስት ጊዜ ከዞሩ በኋላ ውድድሩን በቀዳሚነት ያጠናቀቀው ተወዳዳሪና ፈረሱ ይወደሳሉ፤ ይመረቃሉ፤
መሪው ከፊትለፊት በመሆን ጭፈራ የሚካሄድበት “የጉራ” ሥርዓትም አለ፡፡ በአንድ አካባቢ ያሉት ሁሉም ሰዎች በሰልፍ ጭፈራቸውን ያስነኩታል፡፡ እርቅና ሌሎች ሥነ ስርዓቶች የሚፈፀሙበት ባሕላዊ የሕዝብ መሰባሰቢያ አደባባይ በጋሞዎቹ አጠራር “ቡቡሻ” ላይ እነዚህ ሥርዓቶች ይካሄዱበታል፡፡
በመጨረሻ “የቼዬሳ” (የመስቀል ሽኝት) ሥርዓት ይፈፀማል፡፡ ‹‹በቀጣዩ ዓመት በሠላም አድርሰን›› በሚል በመጠጣትና በመጨፈር የሽኝት ሥርዓቱ ይከወናል፡፡

ዮ መስቀላን ልዩ ቦታ የሚሰጡት በዓል በመሆኑ ‹ለበዓሉ ያልሆነ ልብስ ይበጣጠስ› በሚል ብሂል አባቶች “ጉቼ” ፀጉር ላይ የሚሰካ ባሕላዊ ጌጥ ያደርጋሉ፤ “ካላቻ” በጭንቅላት ፊት ላይ የሚቀመጥ “የባሕላዊ አለቆች” የተባለውን ያጠልቃሉ፤ “ድንጉዛ” ባሕላዊ ሱሪ ያደርጋሉ፤ የአንበሳ የነብር ቆዳ ላያቸው ላይ ይደርባሉ፤ ጎንዳሌ ወይም ጋሻ ይይዛሉ፤ ባሕላዊ አለቆች ብቻ የሚይዙት ጠምባሮና ጦር ይይዛሉ፡፡ ሴቶች ደግሞ ቡልኮ ወይም ጋቢ ይለብሳሉ፤ ዳንጮ ወይም መቀነትና ሻሽ ያስራሉ፤ አልቦ፣ የጆሮና የእጅ ጌጥ አድርገው ወደ አደባባይ እንደሚወጡ የነገሩን የጋሞ ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘነበ በየነ ናቸው፡፡

ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ

ፎቶ፦ ከጋሞ ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ

Previous articleበውስጥ ሱሪው ደብቆ 12 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ከሀገር ሊያስወጣ የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
Next articleየመስቀል በዓል እና የአረጋውያን ትዝብት፡፡