ትግላችን ፍትሐዊ ነውና ኢትዮጵያ ማሸነፏን ትቀጥላለች!

1120

የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ያስተላለፈው ዕለታዊ መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል።

አሸባሪው ትህነግ የጭፍጨፋና ውድመት ዓላማውን አንግቦ እግሩ በመራው ሁሉ በአማራ እና አፋር ክልሎች ላይ ወረራ ላይ ነው።

አሸባሪው የትህነግ ኃይል በገባበት መስመር ሁሉ በጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊትና በክልላችን የጸጥታ ኃይሎች እንዲሁም በግንባር በሚገኘው ሕዝባችን የተባበረ ክንድ፣ የማያቋርጥ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ማስተናገዱን ቀጥሏል፡፡

ሆኖም ይህንን ኪሳራውን ለማካካስና ይዞት የተነሳውን አማራን የማጎሳቆልና የማጥፋት፣ ኢትዮጵያን የማፍረስ በደረሰበት ሁሉ ንፁሐንን መጨፍጨፍና የተገኘን ሀብትና ንብረት መዝረፍና የሽንፈት በቀል አውዳሚ እርምጃውን ቀጥሏል።

ጠላትን በቅጥረኛነት ያሠማሩት የውጭ ጠላቶች እንዲሁም ቅጥረኛውንና ያሠማራቸውን የውስጥ ጠላቶች መክቶ የሀገር ሕልውናን ዋስትና ለማረጋገጥ የተጀመረው የሠራዊት ግንባታ ስራችን ከዘመቻችን ጎንለጎን በተከታታይ በተለያዩ ዙሮች ተጠናክሮ እየተሠራ መሆኑ ይታወቃል።

ሕዝባችን እንደሕዝብ በየደረጃው በተሰለፈበት ዘመቻ ድርብርብ ድል ለማስመዝገብ እና ዛሬም የሀገር ሉዓላዊነትን አስከብረን ለመቀጠል ታሪክ አጭቶናል፡፡

ስለሆነም በክልላችን ውስም ይሁን ከክልላችን ውጭ በተለያዩ የሀገራችን አከባቢዎች የምትኖሩ የክልላችን ተወላጅ ወጣቶች አሁን ለህልውና ዘመቻው ከምታደርጉት የተለያዬ አስተዋፅዖ በተጓዳኝ ለክልላችን በተሰጠው ኮታ መሰረት ለመደበኛ ሀገር መከላከያ ሠራዊትና ለአማራ ልዩ ኃይል ፖሊስነት መስፈርቱን የምታሟሉ ሁሉ በፈቃደኝነት በስፋት እንድትመዘገቡ የአብክመ በድጋሚ ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የአማራ ልዩ ኃይል ፖሊሶች በጥራትና በብዛት ማጠናከር ዋነኞቹ የደህንት ዋስትናችን እንደመሆናቸው መጠን ሀገራዊና ክልላዊ ክንዳችን በማጠናከር በጠላቶቻችን ከየአቅጣጫው የተጋረጠብንን አደጋ መቀልበስና ሰላማችንን በዘላቂነት ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡

ኢትዮጵያችን ታፍራና ተከብራ እንድትኖር ወጣቶቻችን ትውልዳዊ አደራችሁን እንድትወጡ ልናስታውሳችሁ እንወዳለን፡፡

ስለሆነም የክልላችንን ልዩ ኃይል ከማጠናከር ጎንለጎን ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ምልመላም ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታችሁ በአባልነት እንድትሳተፉ ለክልላችን ወጣቶች በድጋሚ ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን፡፡

በተጨማሪም እንደህዝብ የታወጀብንን ጦርነት እንደህዝብ ለመመከት ማሕበረሰቡ የሚያደርገውን ሁሉ አቀፍ ዝግጅት በየአካባቢው አጠናክሮ እንዲቀጥል እናሳስባለን። ለዘመቻው ስኬታማነት ደጀኑ ሕዝባችን ሠራዊቱን በመረጃ፣ በስንቅ ዝግጅት፣ በሀብት ማሰባሰብ፣… ወዘተ የማያቋርጥ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪያችን እናቀርባለን፡፡

ትግላችን ፍትሐዊ ነውና ኢትዮጵያ ማሸነፏን ትቀጥላለች!!

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
ነሐሴ 22/2013 ዓ.ም.
ባህርዳር-ኢትዮጵያ

Previous article“ዩኒቨርሲቲው በአዲስና በዘመናዊ አስተሳሰብ ተቃኝቶ እየሠራ ነው” የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት
Next articleአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ከምድረገጽ እስኪጠፋ ትግላቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በወልቃይት ጠገዴ የከፋኝ መሥራች አባላት ገለጹ።