
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 22/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከልጅነት እስከ ሞት ሀገር ሀገር ማለት፣ ለእናት ሀገር መሰጠት፣ ለእናት ሀገር በዱር በገደል መንከራተት፣ እምብኝ ለነፃነት፣ እምብኝ ለሉዓላዊነት ማለት። ፍርሃት ያልፈጠረባቸው፣ ጠላት የማያስቆማቸው፣ ተኩሰው የማይስቱ፣ ከወሰኑ የማያመነቱ ድንቅ አርበኛ። ጥይት እንደ ዶፍ ቢዘንብ፣ ጠላት በፊት በኋላ ቢከብ ልባቸው አይሸበር፣ ወንድነታቸው አይጠረጠር። በሚያስፈራው ግርማቸው፣ በማይስተው ነፍጣቸው እንደቅጠል እያረገፉት፣ ወደፊት ይገሰግሳሉ። ፊታቸው ከጠቆረ፣ አፈሙዛቸው ከዞረ ወዲያ አንድ ጥይት ለአንድ ጠላት እያደሉ፣ ሀገር የሚያደላድሉ፣ ከታሪክ ላይ ታሪክ የሚደራርቡ ናቸው።
የአርማጭሆ፣ የወልቃይት ጠገዴ፣ የአጅሬ ጃንወራ በረሃዎች፣ የበለሳ ቆላማ ሥፍራዎች፣ የደንቢያ፣ የአለፋ፣ የጭልጋ ሸንተረቶች በጥቅሉ የሰሜን በጌ ምድርና የሰሜን ኢትዮጵያ አስቸጋሪ ቦታዎች እሳቸው ተረማምደውባቸዋል፣ ጠላትንም ሀገሩ እስኪጠፋው፣ ማጣፊያ እስኪያጥረው ድረስ አሯሩጠውበታል፣ ሲዞር ግንባሩን፣ ሲመለስ እግሩን ካለበለዚያም ጀርባውን እያላቀቁ እስከወዲያኛው እንዳይመለስ ሸኝተውታል። ሕዝብ የሚመካባቸው፣ ወገን የሚኮራባቸው፣ ጀግንነት የተቸራቸው፣ ለሀገር እንቅልፍ የሌላቸው ትጉህ የጦር ቀማሪ፣ ጥበበኛ መሪ፣ ምሽግ ሠባሪ፣ ክፉ ዘመን አሻጋሪ።
በታች ሲመጡ በላይ ቢታዩዋቸው፣ ሲገጥሟቸው ቢመቷቸው፣ ሲሞግቷቸው ቢረቷቸው፣ የጦር ስልታቸው የአተኳከስ ፍጥነታቸው ከሰውነት ከፍ ቢልባቸው አሞራው አሏቸው። በሰማይ ከሚበር ፈጣን ፍጡር ጋር ሲያመሳስሏቸው። እንደ አሞራ እየበረሩ፣ በፈረስ እየሰገሩ፣ ከግንባር ግንባር እያነጠሩ፣ ጠላትን ሲመነጥሩ ቢያዩዋቸው እንኳን ወዳጆቻቸው፣ እንኳን ተከታዮቻቸው፣ እየመቷቸው የሚሸሹት ጠላቶቻቸው አደነቋቸው። በጠላት ከመደነቅ፣ ለሀገር ሲሉ በዱር በገደል ከመዋደቅ የበለጠ ጀግንነት የትስ ይገኝና? የአሸናፊነት ምልክት፣ የድል ዜና ብሥራት፣ የጦር አለቃ ራስ አሞራው ውበነህ ተሰማ።
ኢትዮጵያ ጀግና ትወልዳለች፣ ወልዳም ታሳድጋለች፣ አጀግና መከበሪያዋ፣ መታፈሪያዋ ታደርገዋለች። እልፍ ጀግና እየወለደች፣ እልፍ ጀግና እያሳደገች፣ በእልፍ ጀግና እየተመካች፣ የጠላትን ጦር በጀግኖች ልጆቿ እየመከተች፣ እንግፋሽ ያሏትን እየገፋች፣ እንጎትትሽ ያሏትን እየጣለች፣ እንግዛሽ ያሏትን እየረገጠች፣ ጠላቷን ከአፈር ጋር እየቀላቀለች ተከብራ የኖረች ሀገር ናት። ጠላቶች ያልቻሏት፣ መከራዎች ያላስቆሟት። የግፍ ማዕበል ያልገፋት፣ ግዙፍ ታሪክ ያደመቃት፣ ጠላትም ወዳጅም ያደነቃት።

በየዘመናቱ ዘመኑን የዋጁ ጀግኖች ልጆችን እየወለደች፣ በጀግና ልጆቿ የተባበረ ክንድ ተከብራ የኖረችው። አንድነት አስከብሯታል፣ ጀግንነት ኃያል እንድትሆን አድርጓታል። ኢትዮጵያ በየዘመኑ በጠላት ተፈትናለች። ነገር ግን ሁሉንም በድል አሸንፋለች፣ በዓድዋ ተራራ ላይ አንገታቸው የተሰበረው፣ ታሪካቸው የተንኮታኮተው፣ በዓለም ሕዝብ ፊት ያፈሩት፣ በኢትዮጵያውያን አርበኞች ጎራዴ ተበልው የቀሩት ሮማውያን ታሪካቸውን የሚያድሱበት፣ የወደቀ ስማቸውን የሚያነሱበት፣ ደስታ ሲሹ ሀዘን ያቀረቡላቸውን የሀገራቸው ሰዎች የሚክሱበት ሌላ እድል ይፈልጉ ነበር። በዓድዋ ተራራ ላይ የዘለቀችው ጀንበር በሮም አደባባይ ላይ ብርሃኗን ከልክላለች። ሮማውያን በጨለመ ታሪክ ውስጥ እየተርመሰመሱ፣ ብርሃንን ያስሱ ጀመር። እንደ ጠለቀች የቀረችውን ጀንበራቸውን ለመፈለግ አመታት ወሰደባቸው። ጀንበራቸውን ለማስመለስ ሲሉ አርባ ዓመታት ተዘጋጅተው በእነርሱ ሰማይ ሥር ጠልቃ በዓድዋ ሰማይ ሥር ዘልቃ ወደ ምትገኝበት ገሰገሱ። ጀንበር ሊያስመልሱ፣ ታሪክ ሊያድሱ፣ በተራራው ግርጌ የወደቀውን ስማቸውን ሊያነሱ።
በደማቸውና በአጥንታቸው ብርሃንን ያመጡት፣ የማይመሽ ቀን ያወጡት ኢትዮጵያውያን ለበቀል አርባ ዓመታት የተዘጋጁትን ጠበቋቸው። ፍቅር ይሻላል ሲሏቸው አይሆንም ብለው ገጠሟቸው። በፍቅር ተጠይቆ እንቢ ካለ ለሀገር ክብር የማይዘመት ማን አለ? ያሉት ኢትዮጵያውያንም ሳንጃቸውን አሹለው፣ ጎራዴያቸውን ስለው ወደ ጦር ሜዳ ገቡ።
“ሲሆን መጡብነ እንባል ነበረ፣
እንሂድባቸው መቼ ተጀመረ” ያሉት ኢትዮጵያውያን አርበኞች ገፍቶ ወደ መጣው ጠላት ተመሙ።
በጎራዴያቸው አንገቱን ሊቀነጥሱት፣ በሳንጃቸው ሊወጉት፣ በግርማቸው ሊጥሉት፣ ወንድነትን ሊያሳዩት፣ አርበኝነትን ሊያስተምሩት፣ በሀገር የመጣውን ሊቀጡት፣ ዘር ማንዝሩ ኢትዮጵያን ቢነካ መጨረሻው ሞት እንደሆነ ሊያስጠነቅቁት። በዚህ ዘመን ጦር እየመሩ፣ እየሸለሉና እየፎከሩ በጀግንነት ከጠላት ጋር አንገት ለአንገት የተናነቁት፣ ወዳጅ ብቻ ሳይሆን ጠላት ያደነቃቸው፣ ወላፈናቸውን ያልቻላቸው ታላቁ ሰው ራስ አሞራው ውብነህ ናቸው።
የኢትዮጵያን አምላክ አብዝተው የሚወዱት፣ በሕጉ የሚኖሩት፣ ትእዛዙን የሚጠብቁት ታላቁ አርበኛ ፈጣሪ የሚወዳትን፣ ለምስክርነት ያስቀመጣትን፣ ፀጋና በረከት የተሰጣትን ውብ ሀገር ኢትዮጵያን ጠላት ከሚነካት እና ክብሯን ከሚጋፋት ሞትን ይመርጣሉ። አጀግኖ ባሳደጋቸው የሀገራቸው በረሃ እየተመላለሱ ጠላትን ቁም ስቅል ያሳዩት ጀመር። ጥይታቸው መሬት ላይ ጠብ አትልም፣ ተመልከት ብለው ከላኳት ማረፊያዋ ከጠላት ላይ ነበር።
“ንጉሡ ተሰደው ያልሆነላቸውን
ራስ ደጅአዝማቹ ያልሆነላቸውን
ይነዳው ያጉዘው ጀመረ አሞራው ብቻውን” እየተባለላቸው የጣልያንን ሠራዊት እንደአሻቸው ይነዱት ነበር።
ታላቁ የጦር መሪ ሃይማኖታቸውን የሚወዱና እግዚአብሔርን አብዝተው የሚያምኑ ስለነበሩ ከጦርነት በፊት ፀሎት ያደርሱ ነበር። ፈጣሪ እንዲረዳቸው የኢትዮጵያ አምላክ ከፊታቸው እንዲቀድምላቸው ይማፀኑታል፣ ቸርነቱን ይጠይቁታል። ውዳሴ ማርያም ደግመው ምልጃዋን ጠይቀው በእውነት፣ ለእውነት፣ ስለ እውነት ይዋጋሉ ይሏቸዋል። አሞራው ሲፀልዩ መሬቱን እስከ ወገባቸው ድረስ ቆፍረው በመግባት ነበር ይላሉ፡፡ ከጸሎት በማስቀጠል ስልት ይነድፋሉ፣ ገስግሰው ወደ ጦርነት ይገባሉ።
ገሪማ ታፈረ ጎንደሬ በጋሻው በሚለው መፅሐፋቸው ሲገልፁ “ጠላት እግዚአብሔር ከተፈጠረላቸው ወጥመድ በገባላቸው ጊዜ ኮቱ እንዳይበላሽ ከአንገቱ በላይ መለዮውን እያየህ በልልኝ ይባባሉ ነበር። በአንድ ላይ እየሆኑ ድንጋያቸውን ለብሰው እንደቀትር ንብ ይጠዘጥዙትና ያንገበግቡት ጀመር። አጥብቆ ጠላትን የጎዳው ከዛፍ ላይ ሆኖ ለሚተኩሰው አርበኛ ከሜዳ ላይ እንደ ቆመ ግመል መስሎ የሚታየው ስለሆነ በውድ የተገዛው ጥይት አንድም አይወድቅም ነበር” ሲሉ የአርበኛውን ጥበብ ገልፀውታል። አሞራው የተኮሱት ጥይት መሬት ላይ ጠብ አይልም ነበር። ይልቁንስ አንገቱን እየለዩ ይቀነጥሱታል እንጂ።
በአንድ ወቅት የጣልያን ጦር ከአምባ ጊዮርጊስ መረባ ሊወርድ እንደሆነ ተሰማ። በዚህ ጊዜ አሞራው እንቃሽ ወይበኝ ይሄዳሉ። በዚያም ከግራአዝማች በላይ ዘወልዴ ቤት ይገባሉ ። የቤቱ ባለቤትም ምን ልታደርግ መጣህ? አሏቸው። አሞራውም ጣልያንን ልዋጋ አሏቸው። እኒያ ሰውዬም አንድ መላ ፈጠሩ። በል እነዚህን አሽከሮችህን በየጎጡ አንዳንዳቸውን አስቀምጥና እኔም አምባ ጊዮርጊስ ሊሂድና ለጣልያኑ ልንገረው አሉ። ወደ አምባ ጊዮርጊስም ሄዱ። አሞራውም እንደ ምክራቸው አደረጉ። ወደ አምባ ጊዮርጊስ የሄዱት ሰውም አሞራው ዘረፈን የሀገሩ ሰው ግን እናንተን አምኗል አሉት። ወጥመድ ውስጥ እያስገቡት እንደሆነ ያልተረዳው ተስፈኛ የጣልያን ወታደር ጦሩ ብዙ ነው ወይ? ብሎ ጠየቃቸው። እሳቸውም ምድሩ አልበቃው ብሎ ተራራው ሁሉ ሰው ብቻ ሆኗል። እንኳን ሀበሻ ሱዳንም አልቀረ አሻግሮ የሚያይ ሰው ስጠኝና ላሳይ አሉት። ጣልያኑም አንድ ሰው ሰጣቸውና አይተው እንዲመጡ ላካቸው። ገና ሲዘልቁ በየጎጡ የተመደበው አርበኛ ወደ ሰማይ ሲተኩስ ሊያይ የሄደው ሰው ተመልሶ ወደ አምባ ጊዮርጊስ ሄደ። የጣልያን ወታደርም አሞራው ወደ እነርሱ እንዳይመጡ ስለፈሩ እኒያን ሰውዬ አደራ ወደ እኛ እንዳይመጣ የሚፈልገውን ሁሉ ስጡት፣ አትከልክሉት በኋላ እኔ እከፍላችኋለሁ ብሎ ሰደዳቸው። የጣልያን ወታደርም አሞራው ካሉበት ሄዶ ለማጥቃት ይችል ዘንድ ኃይል እንዲጨመረው ይላላክ ጀመር። አሞራውም በዚህ መካከል ወደ አምባ ጊዮርጊስ ገቡ። የጣልያን ሠራዊት ከአምባ ጊዮርጊስ ተነቃንቆ እንቃሽ ወይበኝ አደጋ ለመጣል ሲጓዝ አሞራው ብራ ኢየሱስ ላይ ከኋላ ወጉት። ሠራዊቱ ወደ ብራ ኢየሱስ ፊቱን ሲያዞር አሞራው ኮሰጌ ታዩ። እንቅስቃሴያቸውን እና ጥቃታቸውን ያልቻለው የጣሊያን ሠራዊት እውነትም አሞራው አላቸው ሲሉ ገርማ ታፈረ ፅፈዋል።

ታላቁ አርበኛ ጠላት ከሚጠብቀውና ከሚገምተው በላይ እየተዘዋወሩ አሰቃዩት። ወጉት፣ አሳደዱት፣ ወደ ኢትዮጵያ የገባበትን ቀን እንዲረግም አደረጉት። ሀገሩን አስናፈቁት፣ ወጥረው ይዘው አስጨነቁት። የተወለደባትን ቀን፣ ከሮም የተሸኘባትን አጋጣሚ፣ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የማለባትንም ጊዜ አስረገሙት። ከሮም ሲነሳ ወዮላት ለኢትዮጵያ ብሎ የነበረው አሞራው ሲጠብሱት ወዮለኝ ለእኔ አለ። ጀግና ሲወጥር እንዲህ ነውና። የጣሊያን ሠራዊት ምጥ ያዘው፣ አብዝቶ ተጨነቀ፣ በአሞራው ብርቱ ክንድ ደቀቀ።
“የሮም ነጭ በሬ ተከቧል በብረት፣
ሊበላው ነው መሰል አሞራው ዞረበት” የተባለውም አሞራው ውብነህ በብረት ከበው ስላሰቃዩት ነው። አሞራው ከጠላት እንቅስቃሴ ግምትና ፍጥረት በእጅጉ በላቀና ባልተጠበቀ መንገድ እየተንቀሳቀሱ ነጩን በሬ መውጫ መግቢያ አሳጡት። ቁም ስቅል አሳዩት። በማይሰለቸው ፅናታቸው፣ በማይስተው አፈሙዛቸው፣ በማይደፈረው ግርማቸው፣ በማይፈተው ሱሪያቸው ጠላትን አንገብግበው፣ ብዙውን ቀብረው፣ ብዙውን ማርከው፣ የቀረውን አባረው ሀገራቸውን ነፃ አወጡ። በመከራው ቀን ተረማምደው መልካም ቀን አመጡ።
እነሆ እሞራው የተዋደቁላት፣ ምቾት ረስተው የኖሩላት፣ ከነብሳቸው በላይ የወደዷት ሀገራቸው ኢትዮጵያ እሳቸው አሳፍረው የሰደዱት ጠላት ተላለኪ ዛሬ ላይ እየወጋት ነው። አንተ የአሞራው ውብነህ ልጅ ነህ እንደ አሞራ የምትበር፣ በጣለት ሰፈር እንደ አሻህ የምትዞር፣ የምትሽከረከር፣ አሞራው ጀግንነትን፣ አይደፈሬነት፣ አሸናፊነት እና ኢትዮጵያዊነት ያወረሱህ፣ ጀግኖች የወለዱህ፣ ጀግኖች ያሳደጉህ ጀግና ነህ። ጀግኖች አባቶችህ ደማቅ ታሪክ ፅፈው አልፈዋል። አንተም እንደ አባቶችህ የጀግንነት ታሪክ ፃፍ። ጀግኖች ያከበሯትን፣ ጠላት የፈራትን ሀገርህን እንዳታስደፍር እንደ አሞራው በፅናት፣ በጀግንነት ተዋጋ እንጂ።
አባትህ አሞራው እንዲኮሩብህ፣ እንዲያመሰግኑህ፣ እሰይ ልጄ እንዲሉህ፣ ከእሳቸው በፊትና በእሳቸው ዘመን የነበሩ እልፍ ጀግኖች አበጀህ እንዲሉ በጀግንነት ተፋለም፣ በጀግንነት ታሪክ ሥራ። የአሞራው ልጅ ነኝ ብለህ ተነስ፣ ጠላትህን ከአፈር ጋር ለውስ፣ በአሻገር ገና መለስ፣ መንደርህን እንዳያረክስ። ሞተው መኖርን፣ ተዋድቀው ማሸነፍን፣ ያስተማሩህ አባቶች ልጅ ሆነህ ታሪክ የሌለው በባንዳነት ያደገ በባንዳነት የኖረ ጠላት ሊያሸንፍህ ቀርቶ ሊታገልህ አይችልም። የአንተ ጀግንነት፣ የአንተ አይደፈሬነት ሚዛኑ አሁን ከገጠመህ ጠላት ብዙ ይልቃል፣ ብዙም ይርቃል። በእጥፍ እጥፍ ይበልጣል።
ለባንዳው ጠላትህ እጅህን አንሳበት፣ ነፍጥህን አዙርበት፣ በግንባሩ ልቀቅበት፣ አንደበቱን ቆልፍበት፣ ተስፋውን አጨለምበት፣ ምኞቱን መና አስቀርበት። አዎን አንተ የአባ ዘልስ የአሞራው ውብነህ ልጅ ነህ። የእርሳቸውን ታሪክ ብትረሳ ቀኝህ ትረሳሃለች፣ ነፃነት ትርቅሃለች፣ ኢትዮጵያ ትታዘብሃለች፣ አብዝታ ታዝንብሃለች። አዎን አንተ የአሞራው ልጅ ነህ ለነጻነት ተነስ፣ ለድል ገስግስ።
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
