42 የአሸባሪው የትግራይ ወራሪ እና የኦነግ ሸኔ የጥፋት ቡድን አባላትን በቁጥጥር ሥር በማዋል ምርመራ እያካሄደ መሆኑን የምዕራብ ጎጃም ዞን አስተዳደር አስታወቀ፡፡

263
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 21/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአሸባሪው የትግራይ ወራሪ እና የኦነግ ሸኔ የጥፋት ቡድኖች እስኪደመሰሱ ሕዝቡ የጀመረውን ጠላትን የመመከት እና የመቅበር ዘመቻውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል፡፡
የምዕራብ ጎጃም ዞን አስተዳደር ወቅታዊ የሕልውና ዘመቻን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በመላው የአማራ እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የደቀነውን አደጋ ለመመከት ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን የሕልውና ዘመቻ እያካሄደ ነው፡፡
የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ ስሜነህ አያሌው በመግለጫቸው እንዳሉት አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን እና የእርሱ ቅጥረኞች የከፈቱትን ጦርነት ለመመከት መንግሥት ያቀረበውን የክተት ጥሪ መነሻ በማድረግ የዞኑ ሕዝብ ግንባር ከመዝመት ጀምሮ ለሕልውና ዘመቻው ሀብት በማሰባሰብ ተሳትፎ እያደረጉ ነው፡፡
ዞኑ ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋና ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አዋሳኝ መሆኑን ተከትሎ ከነዚህ አካባቢዎች የሚመጣን የአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ቅጥረኛን ትንኮሳ መመከት የሚያስችል የጸጥታ ኀይል በበቂ ሁኔታ መሠማራቱን ዋና አስተዳዳሪው አብራርተዋል፡፡
በተደረገው የሰርጎ ገብ ፍተሻም በዞኑ 174 ጸጉረ ልውጦች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ በተደረገው ምርመራም 42ቱ በተጨባጭ የአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን እና የኦነግ ሸኔ አሸባሪ ቡድንን ተልእኮ ይዘው ወደ ዞኑ መግባታቸው ተረጋግጧል፡፡
በቀሪዎቹም ላይ ምርመራ መቀጠሉን ነው የተናገሩት፡፡
እስካሁን እየተደረገ ባለው የሕልውና ዘመቻ የአሸባሪው አከርካሪ እየተሰበረ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ግብዓተ መሬቱ ተፈጽሞ ሕዝቡ ወደ ልማት እስኪዞር የዞኑ ሕዝብ ለሕልውና ዘመቻው የሚያደርገውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ወጣቱ እየወሰደ ያለውን የተለያዩ ወታደራዊ ስልጠናዎች በማጠናከር የአካባቢውን ሰላም ከማስጠበቅ ባሻገር ግንባር ድረስ በመዝመት በሕዝቡ ላይ የተጋረጠውን አደጋ መመከት እንደሚጠበቅበት ነው የተናገሩት፡፡
ዘጋቢ፡-ዘመኑ ይርጋ-ከፍኖተ ሰላም
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየኢትዮጵያን ሕልውና በዘላቂነት ለማረጋገጥ አሸባሪው ትህነግ ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ አርበኛ መሳፍንት ተስፉ ገለጹ፡፡
Next article“የወታደር ልጅ ነኝ ኢትዮጵያ ስትደፈር ቆሜ አላይም” አርቲስት ተሾመ በላይ(ተሾመ ባለሀገሩ)