“አሸባሪው ህወሃት ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ልብና ህሊና ውስጥ ወጥቷል” አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ

369
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 21/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ህወሃት ከስልጣን መወገድ ብቻ ሳይሆን ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ልብና ህሊና ውስጥ እንደወጣ በተመድ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ገለጹ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለመምከር በተያዘው አጀንዳ ላይ የሚመክር ስብሰባ አካሂዷል።
በመድረኩ ስለ ኢትዮጵያ ሁኔታ ያስረዱት በተመድ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ስለወቅታዊ ሁኔታ ማብራሪያ አቅርበዋል።
አምባሳደሩ፤ አሸባሪው ህወሃት በፖለቲካ፣ በደኅንነትና በኢኮኖሚ የበላይነትን በመውሰድ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለችግር አጋልጦ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ቡድኑ በዘመነ አገዛዙ ሁሉ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተቃውሞ ያስተናግድ እንደነበር አስታውሰው፤ ከፍተኛና ተከታታይ የሕዝብ ተቃውሞ ቀርቦበት ከስልጣን ተወግዶ ሀገራዊ ለውጥ መምጣቱን ገልጸዋል።
“አሸባሪው ህወሃት ከስልጣን መወገድ ብቻ ሳይሆን ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ልብና ህሊና ውስጥ ወጥቷል” ነው ያሉት።
በሚከተለው አካታች ያልሆነ ርዕዮተ ዓለም የተነሳ አንድነትን ለማሳጣት ከፋፋይ መንገድ ይከተል እንደነበርም አስገንዝበዋል።
“ከመንበረ ስልጣን የተወገደው ህወሃት የትግራይ ሕዝብን እንደመያዣ ይዟል” ያሉት አምባሳደር ታዬ፤ መንግሥት ቡድኑ ወደ መስመር እንዲገባና ለህግ እንዲገዛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አብራርተዋል።
መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ አሳልፎ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከትግራይ ክልል እንዲወጣ በማድረግ አርሶ አደሩ እንዲያርስና አሸባሪው ቡድንም የማሰቢያ ጊዜ እንደተሰጠው ለጸጥታው ምክር ቤት አስገንዝበዋል።
አሸባሪ ቡድኑ የተኩስ አቁም ውሳኔውን በመናቅ ህጻናትን በግዳጅ ለጦርነት በማሰማራት የጥይት ማብረጃ እያደረጋቸው እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከትግራይ ክልል አልፎ በአፋርና በአማራ ክልሎች የሚገኙ አርሶ አደሮች ሥራቸውን መስራት እንዳይችሉ ማድረጉን አስረድተዋል።
ይህ ብቻ ሳይሆን የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ድጋፉ እንዳይደርስ አሸባሪው ህወሃት መዝጋቱን አብራርተዋል።
ቡድኑ ከውስጥና ከውጭ ተባባሪ ኀይሎቹ ጋር በመቀናጀትና በመናበብ ታላቋን ኢትዮጵያ አለመረጋጋት ውስጥ ለመክተት እየተንቀሳቀሰ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
የአፋርና አማራ ክልሎች ሕዝቦች የማይገባቸው ስቃይ ውስጥ መግባታቸውን ገልጸው፤ ለህግ የማይገዛው ቡድን ላይ ጫና በማድረግ የሰላም ጥረቱን ማገዝ እንደሚገባም ጠይቀዋል።
የዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብም ለቡድኑ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያቋርጥ ጠይቀው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ሰላም ለማምጣትና ሕግን ለማስከበር እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
በጸጥታው ምክር ቤት አንዳንድ አባላት የቀረቡት ጉዳዮች በተሳሳተ መረጃ ላይ የተመሠረተ ስለመሆኑ ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያ ሃይማኖት፣ ብሔርና ወይም ሌላ ጉዳይን መነሻ አድርጎ የሚፈጸም ማግለል እንደሌለ ገልጸዋል።
“እኛ እሴት ያለን ሕዝብ ነን እንጂ፤ የወረደ ሞራል የለንም” ያሉት አምባሳደር ታዬ፤ የኢትዮጵያ አንድነት የተመሰረተው ልዩነትን በማክበር እንደሆነ በአንክሮ አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ማስተናገድ የሚችል ሁኔታ እንደሌለ ገልጸው፤ “ከእኛ ጋር ለመስራት ከሚፈልጉ ጋር አብረን ለመስራት ዝግጁ ነን” ብለዋል።
የሩሲያ፣ የቻይና የህንድና የኬኒያ አምባሳደሮች ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሯን በራሷ መፍታት እንደምትችልም አስረድተዋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ደብረ ዘቢጥ ተራራማ ላይ የተወሸቀው የአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በቅርቡ ይቀበራል” በደብረ ዘቢጥ ግንባር የሚገኙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አዛዥ
Next articleበደቡብ ጎንደር ዞን ላይ ጋይንት ወረዳ ነፋስ መውጫ ከተማ የዩኤስ አይ ዲ ቅርንጫፍ የሆነው ኤፍ-ኤች ኢትዮጵያ ዓለምአቀፍ ግብረሰናይ ድርጅት በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን መዘረፉ ተገለጸ፡፡