
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 20/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአሚኮ የጋዜጠኞች ቡድን በደብረ ዘቢጥ ግንባር ምሽግ ድረስ በመገኘት ሠራዊቱ ያለበትን ቁመናና ወኔ ተመልክቷል።
ሕዝቡ እስከ ግንባር ድረስ በመገኘት ስንቅ በማቅረብ፣ በሁሉም ተግባር አሌንታነቱን በመግለጽ እያደረገ ያለው ድጋፍ ሞራል እንደሰጣቸው በደብረ ዘቢጥ ግንባር የሚገኙ የሠራዊት አባላት ተናግረዋል።
የ34ኛ ክፍለ ጦር 3ኛ ብርጌድ 1ኛ ሻለቃ ምክትል ኦፕሬሽናል አዛዥ ሻምበል ጋሻው ክንዴ ሠራዊቱ ከጋሳይ ጀምሮ ጠላትን እየደመሰሰ፣ እየማረከ፣ የዘረፈውን ሽሮና በርበሬ እያንጠባጠበ እንዲፈረጥጥ እንደተገደደ ነው የነገሩን።
ጠላት ወደ መጣበት እንደማይመለስ ጠንቅቆ ያውቀዋል ነው ያሉት።
የአማራ ሕዝብ እስከ ምሽጋችን ድረስ በመገኘት ሁለንተናዊ ድጋፍ እያደረገ በመሆኑ በሠራዊቱ ስም ምስጋና እናቀርባለን ነው ያሉት።
ሕዝቡ የሰጣቸውን ኀላፊነት በብቃትና በአሸናፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም ሻምበል ጋሻው ተናግረዋል።
ሃምሳ አለቃ ማሙሽ ጉተማ ከጋሳይ ከተማ ጀምሮ እስከ ደብረ ዘቢጥ ድረስ የጠላትን ኀይል እየደመሰሱና እየማረኩ መሆኑን አስረድተዋል።
ጠላትን በቅርብ ቀን እንደሚቀብሩትም ነው የገለጹት። ሠራዊቱ በተደራጀና በአንድነት ሆኖ ጠላትን እየደመሰሰ ይገኛል ብለዋል። አሁን ላይ የጠላት አባላት ሥነልቦናቸው ስለሞተ እጅ እየሰጡ ነው ብለዋል።
የ34ኛ ክፍለ ጦር 3ኛ ብርጌድ 1ኛ ሻለቃ አዛዥ ሻምበል ተስፋዬ ወርቁ እንዳሉት ሠራዊቱ በአሁኑ ጊዜ ጠንካራ አቋም ስላለው ጠላትን ለመደምሰስ ዝግጁ ነው።
“በየግንባሩ ጠላትን እየደመሰስን ነው እዚህ የደረስነው” ብለዋል። ሻምበል ተስፋዬ ከሕዝቡ ከፍተኛ የስንቅ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ-ከደብረ ዘቢጥ ግንባር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ