ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ለመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በቱኒዚያ የቀረበው ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ ውድቅ እንዲያደረግ ተጠየቀ፡፡

229
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 20/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አባል ሀገራት አምባሳደሮችን አነጋግረዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ በቱኒዚያ አማካይነት የቀረበውን ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ ውድቅ እንዲያደረግ የምክር ቤቱ አባል ሀገራት አምባሳደሮችን ባነጋገሩበት ወቅት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሽ በቀለ በበኩላቸው የዓባይን ውኃ አጠቃላይ መረጃ፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የግንባታ ደረጃ እና የግድቡ ጠቀሜታን በቱኒዚያ አማካይነት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የቀረበውን ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ ይዘት በተመለከተ እንዲሁም በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያን አቋምን አስመልክቶ ለአምባሳደሮቹ ገለጻ ሰጥተዋል፡፡
ዶክተር ኢንጅነር ስለሽ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የልማት ፕሮጀክት በመሆኑ በጸጥታው ምክር ቤት መታየት የሌለበት ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከዚህ በፊት ጉዳዩ ለጸጥታው ምክር ቤት ቀርቦ፤ ሦስቱ ሀገራት በአፍሪካ ሕብረት አስተባባሪነት የሚካሄደውን የሦስትዮሽ ድርድር በማስቀጠል መፍትሔ ላይ እንዲደርሱ አቅጣጫ መቀመጡን አስታውሰዋል። ይሁን እንጂ ጉዳዩ ዳግም በቱኒዚያ በኩል ወደ ምክር ቤቱ መቅረቡ ተገቢ እንዳልሆነ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በቱኒዚያ የቀረበው ረቂቅ የውሳኔ ሐሳቡ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቷ የመጠቀም መብት የሚጋፋ እና ኢ-ፍትሐዊ የሆነውን የታችኞቹን የተፋሰሱ ሀገራት ጥቅም ብቻ ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ በምንም መልኩ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ሱዳንና ግብጽ ጉዳዩን ፖለቲካዊና ዓለም አቀፋዊ ከማድረግ ይልቅ በአፍሪካ ሕብረት አስተባባሪነት የሚካሄደው የሦስትዮሽ ድርድር እንዲሳተፉ እንዲሁም የናይል አጠቃላይ ስምምነት ማዕቀፍን እንዲፈርሙ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግፊት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሦስትዮሽ ድርድሩን በማስቀጠል የሦስቱን ሀገሮች ሐሳብ በማካተት ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ላይ እንዲደረስ በዝግጅት ላይ መሆኗን አመላክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት አስተባባሪነት የሚካሄደው የሦስትዮሽ ድርድርን በማስቀጠል ከስምምነት ላይ እንዲደረስ ቁርጠኛ መሆኗን አቶ ደመቀ አስገንዝበዋል፡፡
በቱኒዚያ የቀረበው ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ ምክር ቤቱ እንዳያሳልፈው አምባሳደሮቹ ለየሀገሮቻቸው መልዕክቱን እንዲያስተላልፉ መጠየቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ ጽሕፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ቡድን እንቀብረዋለን” ተመራቂ የልዩ ኀይል አባላት
Next article“ደብረ ዘቢጥ ተራራማ ላይ የተወሸቀው የአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በቅርቡ ይቀበራል” በደብረ ዘቢጥ ግንባር የሚገኙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አዛዥ