
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 20/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በአማራ የፈጸመውን ወረራ ለመመከት የክልሉ መንግሥት የሕልውና ዘመቻ ሎጂስቲክስ አቋቁሞ ሀብት የማሰባሰብ ሥራ እያከናወነ ይገኛል፡፡
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር እና የሕልውና ዘመቻው የሀብት ማሰባሰብ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ ፋንታ ማንደፍሮ (ዶክተር ) ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ጦርነቱ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ በማድረስ ንጹኃንን ለችግር እየዳረገ ነው ብለዋል፡፡ ይህ ጦርነት በብዙ ጥረት የተሠሩ ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን እና የኢኮኖሚ መሠረተ ልማት አውታሮችን ብቻ ሳይሆን ዝናብ ጠብቆ የዓመት ቀለቡን ለማምረት ደፋ ቀና የሚለውን አርሶ አደር ሳይቀር ከልማቱ ነቅሏል፡፡ አማራ እና አፋር ክልሎች አዋሳኝ በመሆናቸው የወረራው ፍላጻ አረፈባቸው እንጂ የከሃዲው ቡድን መዳረሻ ኢትዮጵያን ማጥፋት እንደሆነ ተነስቷል፡፡
ለሕልውና ዘመቻው መላው ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ መቅረቡ ይታወሳል፡፡ የወረራው የመጀመሪያና ዋንኛ ገፈት ቀማሹ የአማራ ክልል ሕዝብ ደግሞ ጉዳዩ በሕይወት የመኖርና ያለመኖር በመሆኑ እያንዳንዱ የአማራ ሕዝብ በድጋፉ እንዲሳተፍ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡ በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ሕዝቡ በቀረበለት ጥያቄ መሠረት ያቅሙን ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡ የክልሉ የመንግሥት ሠራተኞች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑና የግል ድርጅቶች ተቀጣሪዎች፣ ባለሀብቶችና የንግዱ ማኅበረሰብ በድጋፉ ተሳታፊ እንደሆኑ ተመላክቷል፡፡
የተሰበሰበው ሀብትም ለወታደራዊ ዝግጅት፣ ጦርነቱን ለመመከት ለተሠማራው የወገን ሠራዊት ቀለብና አልባሳት ከማቅረብ ጀምሮ የሕልውና ዘመቻው ለሚጠይቀው ወጪ ሁሉ ጥቅም ላይ እየዋለ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ ዶክተር ፋንታ የሕልውና ዘመቻውን በትልቁ የደገፉት ባለሀብቶች ናቸው፤ ኅብረተሰቡ የአቅሙን ድጋፍ ቢያደርግም ከተጋረጠው አደጋ አንጻር ግን በቂ አይደለም ብለዋል፡፡
ወረራው በተፈጸመባቸው አካባቢዎች አሸባሪው የትግራይ ወራራ ቡድን ምንም ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማይል በተግባር አሳይቷል፡፡ ንጹሐንን ገድሏል፤ ሀብትና ንብረት ዘርፎ ወደ ትግራይ ጭኗል፣ መውሰድ ያልቻለውንም አውድሟል፤ የግለሰብ ካልሲ ከመስረቅ ጀምሮ እንስሳትን ሳይቀር መግደሉን አስረድተዋል፡፡
ይህንን ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ እና የወደሙ መሠረተልማቶችን መልሶ ለማልማት እና የተጎዱ ወገኖች እንዲያገግሙ ለማድረግ አሁንም የሕዝቡ ድጋፍ አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይ የአማራ ክልል ሕዝብ የአቅሙን ብቻ ሳይሆን ያለውን በመስጠት ሳይሰስትና ሳይሰለች እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
‹‹የአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የአማራ ሕዝብን የማጥፋት አጀንዳ ለማክሸፍና ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ሁሉም ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቀርባለሁ›› ብለዋል፡፡ ጦርነቱ እስኪቋጭ የሚያደርገውን አስተዋጽኦ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡ በየደረጃው ያሉ መሪዎችም የተሰበሰበውን ሀብት በአግባቡ ለታለመለት ዓላማ እንዲያውሉ አሳስበዋል፡፡
በሌላ በኩል ረጅ ድርጅቶች በጦርነቱ የተጎዱ ዜጎችን ይደግፋሉ፡፡ በአማራ ክልል ተጎጂዎችን ለመርዳት ፈቃደኛ የሆኑ እና በተወሰነ መልኩ ድጋፍ ማድረግ የጀመሩ ድርጅቶች እንዳሉ አንስተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ድጋፍ ማድረግ አልቻልንም ያሉ ረጅ ድርጅቶች በአማራ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮችን ለመርዳት ጥያቄ ሊያቀርቡ ቀርቶ የክልሉ መንግሥት ያቀረበላቸውን ጥያቄ እንኳን አልተቀበሉም ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ