“ንጉሥ ዳዊት በፍቅር የተቀበለውን መስቀል ወደ ሀገሩ በክብር ማድረስ ባይችልም፤ አባት የጀመረውን ልጅ ይጨርሳልና ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ መስቀሉን ይዞ ሀገሩ ገብቷል፡፡”

863

“ንጉሥ ዳዊት በፍቅር የተቀበለውን መስቀል ወደ ሀገሩ በክብር ማድረስ ባይችልም፤ አባት የጀመረውን ልጅ ይጨርሳልና ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ መስቀሉን ይዞ ሀገሩ ገብቷል፡፡”

“ፍቅር የማይንቀሳቀስ አንቀሳቃሽ ነውና ዛሬም በጋራ ተንቀሳቅሰን የተደበቀውን የጥንት ፍቅራችንን እንፈልግ፡፡” መምህር ጥበቡ ክብር

ባሕር ዳር፡ መስከረም 17/2012 ዓ/ም (አብመድ) መስቀል የፍለጋ በዓል ነው፤ መስቀል በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ብርሃንን የማየት ዕድል ነው፡፡ መስቀል ከሰማይ የዙፋኑ መቀመጫ እስከ ምድር የእግሩ መረገጫ ያለውን ትስስር “ዕፁብ ድንቅ” የሚሉበት ነው፡፡ መስቀል ከስጋ አልፎ ለነብስ፤ ከራስ አልፎ ለሌሎች መኖር ነው፡፡ መስቀል ስለእምነት፣ ስለፍቅር እና ስለእውነት የተከፈለ መስዋትነት የፈነጠቀው ቀስተ ደመና ነው፡፡ የመስቀል በዓል ተምሳሌት ወድቆ መነሳት፣ ተረስቶ መታወስ፣ ሞቶ መዳን፣ ጠፍቶ መገኘት፣ ስለፍቅር መውረድ እና ስለሰው ልጅ ተላልፎ መሰጠትን ሁሉ የያዘ እንደሆነ የሃይማኖቱ አባቶች ያስተምራሉ፡፡

ኢትዮጵያውያን የመስቀል በዓልን ታሪካዊ ዳራ ሲያስቡ ከቀራኒዮ እስከ ጎለጎታ፣ ከሮም እስከ እስራኤል፣ ከአሌክሳንድሪያ እስከ ኢትዮጵያ በፍቅር፣ በእምነት እና በተስፋ የወጡ የወረዱትን ሁሉ ያስቡ ዘንድ ግድ ይላቸዋል፡፡ መስቀል በኢትዮጵያ ከሃይማኖታዊ ዳራ አለፍ ብሎ ባሕላዊ ገፅታው የሚጎላበትም አካባቢ ቀላል አይደለም፤ ለምሳሌ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በመስቀል በዓል ዘመናቸውን ይቀይሩበታል፤ ዓመታዊ መሰባሰቢያቸውም ያደርጉታል፡፡

መስቀል በኢትዮጵያውያን ዘንድ እንዲህ ልዩ በዓል ነው፡፡ በዓሉ ከቤተሰባዊ መሰባሰብ አልፎ የጎረቤት እና የማኅበረሰብ የስብስብ በዓል ነው፡፡ የመስቀል በዓል በየግል ቤት ውስጥ ሲከበር አይታይም፡፡ እንደ ግሽን በታላላቅ አድባራት፣ እንደ ትልልቅ ከተሞች በአደባባይ እና እንደ ሰፈር በጎረቤት ተሰባስበው የሚያከብሩት በዓል ነው፡፡ የዚህን በዓል ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ዳራ ምን እንደሚመስል ያስረዱን የሥነ መለኮት ምሩቁ እና በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ልዩ ፀሐፊ መምህር ጥበቡ ክብር ሲናገሩ ‹‹የመስቀል በዓል ከሰው ልጅ ጥንተ ታሪክ ጋር ቁርኝት አለው›› ብለዋል፡፡

መምህር ጥበቡ የበዓሉን ታሪክ የአዳምን በደል በደሙ ለመሻር ከሰማየ ሰማያት ከወረደው የኢየሱስ ክርስቶስ በስጋ መገለጥ እስከ ቀራኒዮ ተላልፎ መሰጠቱ ድረስ ያንሰላስሉታል፡፡ ‹‹መስቀል በቀደምት ሮማውያን ዘንድ የሚታወቀው የወንጀለኞች መቅጫ ሆኖ ሲያገለግል ነበር፡፡ ነገር ግን ዛሬ እንዲህ በዓለሙ ሁሉ ይከበር ዘንድ በግራ እና በቀኝ ከተሰቀሉት ፈያታዊ ዘየማን እና ፀጋማይ ጋር ክርስቶስ ተሰቀለበት፡፡ ከዚህ በኋላ ነበር የመስቀል ታሪክ በዓለሙ ሁሉ የተቀየረው›› ይላሉ መምህር ጥበቡ፡፡

የክርስቶስ መስቀል ከቀራኒዮ ተራራ ወርዶ የተቀመጠው ሐዋሪያው ቅዱስ ያዕቆብ መንበረ ጵጵስናውን ባደረገባት ጎልጎታ ነበር፡፡ መስቀሉ ሙታንን ሲያስነሳ፤ ሕሙማንን ሲፈውስ፣ ለምፅ ሲያነፃ እና መሰል ታምራትን ሲያደርግ ያዩት አይሁዳውያን ቅናት አደረባቸውና ከእየሩሳሌም ወጣ አድርገው ጉድጓድ ቆፍረው ሦስቱንም መስቀሎች ቀበሯቸው፤ ቆሻሻ እንዲደፋባቸውም አዋጅ አስነገሩ፡፡ ይህም ከ300 ዓመታት በላይ ቆሻሻ ሲደፋበት ስለነበር ታላቅ ተራራ እንደሆነ መምህር ጥበቡ መዛግብተ ቤተ ክርስቲያንን ዋቢ አድርው ነግረውናል፡፡

ወቅቱ 326 ዓ.ም ገደማ የሮማው ንጉሥ የነበረው የቄሳር ቆስጠንጢኖስ እናት ቅድስት እሌኒ ስለመስቀሉ ፍቅር ስትል ከሮም ወደ እየሩሳሌም አመራች፡፡ በእየሩሳሌም እየተንቀሳቀሰች ቅዱሳን ቦታዎችን እና መካነ መቃብሮችን ሁሉ በማየት አብዝታ ብትደሰትም የመስቀሉ ነገር ግን ከውስጧ አልወጣም ነበርና ሳትሰለች ፍለጋዋን ቀጠለች፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድና ድካም በኋላ ግን በአዛውንቱ እና በታሪክ አዋቂው ካህኑ ኪራቆስ አማካኝነት የተቀበረበትን ተራራ ለመለየት በቃች፡፡

በመጨረሻም ቅድስት እሌኒ ደመራ ደምራ በእሳት ባቃጠለችው ጊዜ ጭሱ ወደ ላይ ከወጣ በኋላ ተመልሶ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ወደ ተቀበረበት ተራራ ላይ አመለከተ፡፡ በዚህ ጊዜ ታዲያ እሌኒ ተራራውን አስቆፍራ መስቀሉን አወጣች፡፡ ‹‹ከተቀበሩት ሦስት መስቀሎች ውስጥ የክርስቶስን መስቀል ለመለየት ተዓምራትን ያደርጉ ዘንድ በላያቸው ላይ ሙታንን በማስቀመጥ የክርስቶስን መስቀል ለየች፡፡ በአካባቢው ቤተ ክረስቲያን አሳንፃም አስቀመጠችው›› ብለዋል መምህር ጥበቡ፡፡

ዘመናት ሲያልፉ የግማደ መስቀሉ የቀኝ ክፍል በግብፅ ይኖር ነበርና በዘመኑ በኢትዮጵያ ነግሠው የነበሩት ንጉሥ ዳዊት ለመልካም ግንኙነታቸው ወሮታ፤ ለፍቅራቸው መገለጫ በማድረግ ግማደ መስቀሉን ይሰጧቸው ዘንድ ግብፃውያኑን ጠየቋቸው፡፡ መልካም ምላሽ አግኝተው መስቀሉን ይዘው በመመለስ ላይ የነበሩት ንጉሥ ዳዊት በመንገድ ላይ እያሉ አረፉና የዙፋን ልጃቸው ንግሥናውን ብቻ ሳይሆን መስቀሉንም ተቀብሎ ወደ ኢትዮጵያ “በማስገባት መስቀሉን በመስቀለኛ ቦታ” ከፍ አድርጎ በግሸን ደብረ ከርቤ አስቀመጠው፡፡

‹‹ዛሬ የመስቀልን በዓል የምናከብር እኛ እንደ ቅድስት እሌኒ ስለውንድሞቻችን ፍቅር፣ ተስፋ እና አንድነት ስንል በፅናት መፈላለግ ያስፈልገናል፡፡ ከአባቶቻችን የወረስነው ሃይማኖት፣ እምነትና ጀግንነት በፍቅር ሊገለፅ ይገባል›› ነው ያሉ መምህሩ በመልዕክታቸው፡፡

መስቀሉ ሙታንን ስላስነሳ፣ ሕሙማንን ስለፈወሰ እና ተዓምራትን ስላደረገ ከተቀመጠበት የክብር ቦታ ወርዶ ቆሻሻ ላይ ተጣለ፡፡ ለ300 ዓመታትም የቆሻሻ ብርድ ልብስ ሲያለብሱት ሀሰት በእውነት ላይ ለዘለዓለም የምትነግሥ መስሏቸው ነበር፡፡ ዳሩ እውነት ይገለጣል፤ ብርሃንም ይወጣልና ዘመኑ ሲደርስ ከነተዓምራቱ ወጣ፡፡ ይህ የዛሬዎቹን ወጣቶች የሚያስተምረው ሀሰት በበዛበት ዓለም ትዕግስት፣ ተስፋ እና ፍቅር ካለ ሁሉም ነገር እንደሚገለጥ ነው፡፡ ጥላቻ፣ መለያየት፣ ግጭት እና ማፈናቀል የዚህ ዘመን ቆሻሻዎች በመሆናቸው ወጣቶች ይህንን የቆሻሻ ክምር ይንዱ ዘንድ ግድ ይላቸዋል፡፡

መምህር ጥበቡ እንደሚሉት ኢትዮጵያ የፍቅር ሀገር ናትና አባት ንጉሥ ዳዊት በፍቅር የተቀበለውን መስቀል ወደ ሀገሩ በክብር ማድረስ ባይችልም፤ አባት የጀመረውን ልጅ ይጨርሳልና የዛሬዎቹ ወጣቶች ከአባታቸው ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ በመማር የአባቶቻቸውን አደራ ተሸክመውና ተቀብለው ዘመኑን መዋጀት ግድ ይላቸዋል፡፡
‹‹ትህትና፣ አገልጋይነት፣ ወደ ራስ ማንነት መመለስ እና ሃይማኖትን መጠበቅ በዚህ ትውልድ የሚታዩ በጎ ጀምሮች ናቸው›› የሚሉት መምህር ጥበቡ ይህ የወጣቶቹ በጎ ጅማሮ በአባቶች ተግሳፅ፣ በመንግሥት ትጋት እና በታላላቆች አስተምህሮ በፍቅር እና በመቻቻል እንዲጎለምስ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ “ፍቅር የማይንቀሳቀስ አንቀሳቃሽ ነውና ዛሬም በጋራ ተንቀሳቅሰን የተደበቀውን የጥንት ፍቅራችን እንፈልግ” ሲሉ መምህር ጥበቡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ምስል፡- ከድረገጽ

Previous article“የደመራው ቋሚ እንጨት ወደየትኛው አቅጣጫ ወድቆ ይሆን?”
Next articleበውስጥ ሱሪው ደብቆ 12 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ከሀገር ሊያስወጣ የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡