“ሽብርተኛው ትህነግ መተዳደሪያችን የሆኑትን እንስሳት ገድሎ ቀሪ ንብረታችንን አውድሞ ነው የሄደው” አርሶ አደሮች

228
ባሕር ዳር: ነሐሴ 19/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አርሶ አደር እንየው ባይሌ በደቡብ ጎንደር ዞን ፋርጣ ወረዳ የሳርና ቅስናጥ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ሽብርተኛው ትህነግ ባካሄደው ወረራ እና ጥቃት 4 ከብቶችና 4 በጎቻቸውን እንደገደለባቸው ተናግረዋል።
ቡድኑ በጦር መሳሪያ ቤታቸውን እንዳወደመባቸውም የተናገሩት አርሶ አደሩ አሁን በኅብረተሰቡ ርብርብ በአዲስ መልኩ እየተሠራ እንደሆነ አስረድተዋል።
አሸባሪው ቡድን የቤት እቃዎቻቸውንም እንደዘረፈባቸው ተናግረዋል። “ተሹለክልከው ወደ ሰፈራችን ገብተው ንብረታችንን አጠፉ እነሱም አለቁ” ብለዋል።
ሌላው አርሶ አደር ገደፋው ቢሰጥ ሽብርተኛው ቡድን ባደረሰባቸው ጥቃት መተዳደሪያቸው የሆኑትን ከብቶቻቸውን ማጣታቸውን ተናግረዋል። አርሶ አደሩ በገበያ ላይ በ50 ሺህ ብር የማይገኙ ከብቶቻቸውን ማጣታቸውን ነው በሐዘን ስሜት የነገሩን። የቤት እቃቸው እንደተዘረፈና እንደወደመም ተናግረዋል።
መንግሥትና መላው ሕዝብ በአንድ ላይ በመሆን ሰው ገድሎ፣ አፈናቅሎ፣ ንብረት አውድሞ የሄደውን ወራሪ እንዲያጠፉም ጠይቀዋል።
አርሶ አደር ክንዴ አባተ በበኩላቸው በሽብር ቡድኑ ምክንያት ከ300 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የባሕር ዛፍ ሀብት እንደወደመባቸው ተናግረዋል። ቡድኑ ለጥፋት እንደተሰማራ በሚሠራው ሥራ መገንዘብ እንደቻሉ ገልጸዋል። ካደረሰው ጥፋት በተጨማሪም ሀብትና ንብረታቸውን እንደዘረፈባቸው አስረድተዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“አሸባሪውን ቡድን በቅርቡ ግብዓተ መሬቱ ይፈፀማል” ሴት የመከላከያ የሠራዊት አባላት
Next article“የወሎ ገበሬ ደጉ ደጉ ሰው፣ ያባቱን ባድማ በማረሻ ሳይሆን በአፈሙዝ አረሰው።”