የደቡብ ዕዝ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ለአሸባሪው የህወሓት ቡድን ሲሰሩ በነበሩ የሰራዊቱ አባላት ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ሰጠ።

283
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 19/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ዕዝ ወታደራዊ ፍርድ ቤት የዕዙ የሰራዊት አባላት ሆነው ለአሸባሪው የህወሓት ቡድን ሲሰሩ በነበሩ የሰራዊት አባላት ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ሰጠ።
የሰራዊት አባላቱ ለህገ-መንግስቱና ለሀገራቸው የገቡትን ቃል ኪዳን ወደጎን በመተው የሠራዊቱን አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች አደጋ ላይ የሚጥሉ ተግባራትን ሲያከናውኑ መቆየታቸው በችሎቱ ተነስቷል፡፡
በተለይም የሠራዊቱን ልዩ ልዩ ምስጢራዊ ሰነዶች አሳልፈው በመስጠት፣ የሠራዊቱን ልዩ ልዩ ትጥቆች የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት እንዳይሰጡ ምስጢራዊ ቡድን በማደራጀትና መሳሪያዎቹን በማበላሸት ሠረራ ላይ ተጠምደው እንደነበር በችሎቱ ተገልጿል፡፡
በዚህ የተከሳሾች መዝገብ ስር፡-
1. ለግዳጅ የተዘጋጁ መሳርያዎች የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት እንዳይሰጡ በማድረግ፣
2. ሰራዊቱ ሽብርተኛውን የሸኔ አባላትን ለመደምሰስ በሚንቀሳቀስበት ዕለት ቀድሞ መረጃ በመስጠትና ተልዕኮው ተፈላጊውን ውጤት እንዳያገኝ በማድረግ፣
3. የሠራዊቱን ምስጢራዊ ክንዋኔዎች ለሽብርተኛው አካል እንዲደርስ በማድረግ፣
4. በበላይ አካል የሚሰጣቸውን ተልዕኮ ወደጎን በመተው ከሽብርተኛው አካል የሚሰጣቸውን ድብቅ አጀንዳ መፈፀም በሚያስችላቸው አካሄድ ላይ ብቻ ማተኮር፣
5. የትግራይ ልዩ ሃይሎች “የብልፅግና ወታደሮችን” ድል እያደረጉ ነው የሚል ሽብር በመንዛት በሠራዊቱ ውስጥ የሚገኙ የትግራይ ተወላጅ የሠራዊት አባላትን በማነሳሳት የቆሙለትን አላማ ወደጎን በመተው የወንጀል ድርጊታቸው አካል እንዲሆኑ በማድረግ፣
6. ከቆሙለት ሀገራዊ ዓላማ ይልቅ ለክልል ልዩ ሃይል የሚጠቅሙ ተግባራትን ማከናዎን የሚሉ ክሶች ተዘርዝረዋል።
ተከሳሽ የሠራዊት አባላትም የቀረቡላቸውን ክሶች ክደው የተከራከሩ ሲሆን የዕዙ ፍትሕ ቡድን የሰነድና የሰው ማስረጃዎችን አቅርቦ ተከራክሯል፡፡
የተከሳሾች ጠበቃ በበኩሉ ተከሳሽ የሰራዊት አባላቱ ከዚህ ቀደም ሃገራቸውንና ህዝባችውን ለማገልገል በርካታ አወንታዊ ተግባራትን ያከናወኑ መሆናቸውንና የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ፍርድ ቤቱ የቅጣት ማቅለያ እንዲያደርግላቸው ጠይቋል፡፡
ግራ ቀኙን ያዳመጠው ወታደራዊ ፍርድ ቤትም ተከሳሾቹ በቀረቡባቸው ክሶች ላይ በትክክል መከላከል ያልቻሉ በመሆኑ ጥፋተኛ ናቸው ሲል በመወሰን የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት ችሎቱን አጠናቋል ሲል የዘገበው ኢቢሲ ነው።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleምሽግ ላይ በድንጋይ የጦር መሳሪያ ከነሙሉ ትጥቁ የማረከው የሚኒሊክ ልጅ!
Next article“ኦነግ ሸኔ ከወለጋ ሕወሓት ከቆቦ አፈናቅሎኛል” በሁሉቱ አሽባሪዎች የተፈናቀሉት እናት