
ባሕር ዳር: ነሐሴ 19/2013 ዓ.ም (አሚኮ)የሀገሬ ግመሎች ሠንደቅ አክባሪዎች፣ ሀገርና ክብር አዋቂዎች፣ ዘመን ለኪዎችና ተራማጆች ናቸው። አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ ወደ ሚውለበለብበት፣ ጀግና ወደ ሚፈጠርበት፣ አሸናፊነት ወደ አለበት፣ ፅናት ወደ መላበት ሥፍራ ዓይናቸውን ያዞራሉ። እግራቸውንም ያነሳሉ። ወደ ፊትም ይገሰግሳሉ። ሠንደቁን ያውቁታል፣ ለክብሩ እጅ ይነሱለታል፣ ለግርማው ይዘምቱለታል፣ ለፍቅሩ ይሞቱለታል።
የሠንደቅ ክብር፣ የሀገር ፍቅር ያውቃሉና። በረሃ ሳይበግራቸው፣ የውኃ ጥም ሳያስቆማቸው የወገናቸውን ስንቅ በጀርባቸው፣ የሀገራቸውን ፍቅር በልባቸው ይዘው እንደሠራዊቱ ሁሉ በጥበብ ይጓዛሉ። በመከራ ቀን ይዘምታሉ፣ የደከመውን ይሸከማሉ፣ የሚታገለውን ያግዛሉ። የሚናገሩበት አንደበት ሳይኖራቸው፣ አልሞ መተኮስ፣ ተራማዶ ምሽግ ማፍረስ ሳይቸራቸው፣ ቡድን ሳይፈጠርላቸው ለድል የሚገሰግሰውን ስንቅና ትጥቅ ተሸክመው ይዘምታሉ፣ ያዘምታሉ። ያዋጋሉ።
የኢትዮጵያ ግመሎች እስከሞት ድረስ ለሀገራቸው እና ለባለቤቶቻቸው ሲታመኑ፣ በርካታ የኢትዮጵያ ልጆች ግን ከስልጣን ማግስት ኢትዮጵያን ይክዳሉ፣ ያጎረሰ እጇን፣ ያጠባ ጡቷን ይነክሳሉ። የኢትዮጵያ ግመሎች የሠንደቁን አስፈሪነት፣ ቀዳሚነት፣ ክቡርነት፣ የክብሩን ኃያልነት፣ የግርማውን አይደፈሬነት አስቀድመው ያውቁታል። በልባቸው ያከብሩታል። እንደ እሳት በሚጋረፈው በረሃ በረድፍ ሲጓዙ በላያቸው ላይ ሠንደቁን እያውለበለቡ፣ ለበረሃው ምድር ውበት፣ ለበረኸኛው ፅናት፣ አንድነት፣ ኢትዮጵያዊነት፣ አይደፈሬነት ያስተምራሉ። ለምድር ተስፋ፣ በረከትና ክብር ፣ ለሰማይ ምስክር ይሆን ዘንድ በኢትዮጵያ የሚውለበለበውን ታላቁን ሠንደቅ በመለሎው ቁመታቸው፣ በማይደክመው ጉልበታቸው ይዘውት ይጓዛሉ። ክብሩን በላያቸው ይመሰክራሉ። የሰማዩን በምድር ያውለበልባሉ። እነርሱም ታሪክ ቀርፀው ያልፋሉ።

ታሪካቸው ለብቻው ባይፃፍም፣ በአውደ ውጊያ አንገት ቆርጠው ባይፎክሩም፣ ከድል መልስ በሕበረ ዜማ በጋራ ባይዘምሩም የኢትዮጵያ ግመሎች የታሪክ ተካፋዮች ናቸው። ታሪክ የሚሠራውን ያደርሳሉ፣ ስንቅ ያቀበልላሉ፣ ጠመንጃና ጥይት፣ ጦርና ጎራዴ በጀርባቸው አዝለው ያቀርባሉ። ለምን ካሉ ኢትዮጵያን ይወዷታልና። እንደ ባለቤቶቻቸው ይታመናሉና ነው።
ጦረኛው ሲገሰግስ፣ ግመልና አጋስስም አብሮ ይገሰግሳል። ከሜዳው ያድርሳሉ፣ በባለቤታቸው ወኔ ጦር ሜዳ መካከል ላይ ይገኛሉ። ዘመን ደጉ እነርሱን የሚያግዝ መሣሪያ ቢሰጥም ዘመን ያልደረሰብትን፣ ሠው ሰራሽ ያልገባበትን እነርሱ ይደርሱበታል፣ ያለ ድካም ይጓዙበታል። ለማን ካሉ ለአምሳለ ቀስተ ደመናው፣ ለተስፋው ምልክት አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ፣ ሠንደቁ ስለ ተሰጣት፣ የፈጣሪ ኃያልነት የልጆቿ ጀግንነት ስለሚጠብቃት ድንቅ ምድር ኢትዮጵያ።
ወሎ ውስጥ ነኝ ተሁለደሬ። በማለዳ ነበር ወደ ተሁለደሬ ያቀናሁት። ከማለዳው የክረምት ጉም ጋር እየታገለች በምሥራቅ ንፍቅ ብቅ ጥልቅ የምትለው ጀንበር ብርድ የበዛበትን ማለዳ እያሟሟቀችው ነው። በግርማ በቀሞመው ኮረብታ አጠገብ በወገባቸው ዝናርና ጩቤ ፣ በልባቸው አንጄት አርስ ወኔ፣ በትክሻው ክላሽ የያዙት የተሁለደሬ ጀግኖች በጠዋት ለተልዕኮ ተዘጋጅተዋል። ከጀግኖቹ ጀርባ ታማኞቹ ግመሎችና ሌሎች የጋማ ከብቶች ቆመዋል። እነርሱም ለተልዕኮ ተዘጋጅተዋል። ሀገርና ሕዝብ ለጣለባቸው ተልእኮ። ሁኔታው ቀልብ ይስባል። ጀግኖቹስ ተነክተው፣ ግመሎቹስ ምን ሆነው ነው በሚያስፈራ ግርማ የቆሙት? ያስብላል።
ክላሻቸውን አመቻችተው፣ ግመሎቻቸውን አዘጋጅተው፣ ፊታቸውን አስቆጥተው ወደቆሙት ጀግኖች ተጠጋሁ። ሰላምታ ሰጠኋቸው። በወሎዬ ለዛ፣ አንጄት በሚያሳስር ልብን በሚያዋዛ፣ ቀልብን በሚገዛ ሰላምታ አፃፋውን መለሱልኝ። ከፊታቸው ጀግንነት፣ ከአንደበታቸው የዋህነት፣ ከነፍጥ አያያዛቸው አልሞ ተኳሽነት ይታያል።

በአማራ ላይ ወረራ የፈፀመው ከሃዲ ቡድን ድፈርትና አልጠግብ ባይነት እንዳናደዳቸው ሳይጠይቋቸው ፊታቸው ይናገራል። ከወረዳቸው ሳይደርስ በአሻገር ገና ሲያንጃብብ በአፈሙዝ ቀብረውት፣ በክረምት ጭቃ ለውሰውት እየፈረጠጠ እንኳን ሀጃቸው አልሞላም። ስሙና ግብሩ ከስጋው እኩል ከአፈር ጋር እንዲደባለቅ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ በድላቸው አልተደሰቱም። ሌላ ድል እየናፈቃቸው እያሸተቱ፣ ጠላትን ድል እየመቱ መሄድ እንጂ ፍላጎታቸው።
ፈጣሪ ሌላ ቀንና ተጨማሪ እድል ሰጥቷቸው ለሌላ ድል ነበር በጠዋት በሚያስፈራ ግርማ መቆማቸው። ዓይናቸው በአሻገር ወደ ሚገኘው ተራራ ቶሎ ቶሎ ይወረወራል። የእኔም ዓይን የእነርሱን ረጅም ምልከታ እየተከተለች በአሻገር ያለውን ተራራ ትመለከታለች። በዚያ ተራራ ጀግኖች ጠላትን ድባቅ መትተው እንደ ንብ ሠፍረውበት፣ ለሌላ ድል ተማክረውበት አልፈውት ሄደዋል። በተራራው አናትና ገርጌ ጠላትን አጭደውታል። በጠዋት ከነግመሎቻቸው በተጠንቀቅ ስለቆሙበት ጉዳይ ማውጋት ጀምረናል።
የተሁለደሬ ወረዳ ነዋሪው አቶ መሐመድ ይማም በአሻገር እያሳዩ በዚያ ታች የሚመጣውን ኃይል በመዋጋት፣ ኅብረተሰቡን አሳትፈን ትግል ላይ እንገኛለን አሉኝ። ከሚያደርጉት ውጊያ በላይ ለሠራዊቱ ሥንቅ በማቀበል እና ቦታዎችን በማመልከት ሌላ ጀብዱ ይፈፅማሉ። ለዘመቻ ስለተዘጋጁት ግመሎችና ሌሎች የጋማ ከብቶች ሲነግሩኝ ❝በእነዚህ ግመሎች መኪና ወደ ማይደርስበት ሥፍራ እየተዋጋ ለሚገኘው ሠራዊት ጥይት፣ ምግብ፣ ውኃ እናቀርብባቸዋለን፣ በግመሎቹ ወደ ሠራዊቱ የሚፈልገውን ወደ ተራራ ይዘን እንወጣለን። በግመል በታገዘው ውጊያ ጠላት እየተመታ ነው፣ እየሸሸ ወደ ኋላ እየፈረጠጠ ነው❞ አሉኝ። ጀግኖቹ ከግመሎቹ ጋር ኾነው ጀብዱ እየፈፀሙ መሆኑን ተረዳሁ። ኢትዮጵያ ስትነካ፣ ማንነት ሲደፈር ግመልም አይተኛም።
ጠላት እየተመታ ነው፣ ዙሪያውን ተከቧል፣ ኅብረተሰቡና ሠራዊቱ ከቧቸዋል፣ የግመሎቻችን እና የእኛ ትግል ጠላት እስኪጠፋ ድረስ ይቀጥላል፣ ጠላት እስከሚደመመስ ድረስ አዳራችንም ውሏችንም ከሠራዊቱ ጋር ነው ብለውኛል። ግሩም ጥምረት የነዋሪው መናበብ፣ የግመሎቹ ዝግጁነት፣ የጀግኖቹ ቆራጥነት አስደናቂ ሁነት። ማን ደፍሮ የሚጋረፈውን የጀግኖችን ግንባር ችሎ ይቆማል? ማን ችሎ የጀግኖችን ሥፍራ ይረግጣል ? በምን አቅሙስ ይቀናጣል? ለነፃነት የተገባ መሃላ፣ ግንባሩም ደጀኑም የማይላላ ድንቅ ጥምረት።
አብዱ ሙሐባም ቀበል አድርገው ያወጉኝ ጀመር ❝አንተ ወዳጄ ታጣቂውም ሁሉም ሕዝብ ለመዋጋት ሙሉ ዝግጅት አድርጓል፣ አብሽር ወደኋላ የሚል የለም>> አሉኝ። ግመሎቻችን ገበሬው የሚያዋጣውን እንጀራ፣ ጥይት፣ ውኃ እና ሌሎችን እቃዎች እየያዙ ምሽግ ድረስ ያደርሳሉም አሉኝ። አዳራቸውና ውሏቸው ምሽግ ላይ የሆነ ጠላትን በጫረው ጉድጓድ እየቀበሩ የሚገኙ ጀግኖች እንዳሉም ነግረውኛል። ❝አርሶ አደሩ ቆርጧል፣ በስሜት ነው የተነሳው፣ ወደ ኋላ አይልም፣ ከመከላከያ ኃይሉ ጋር ከመነሻው ድረስ እንሄዳለን፣ ቁሳቁስ ብቻ ሳይሆን ሕይወታችን ለመስጠት ዝግጁ ነን❞ አሉኝ አብዱ በወሎ ለዛቸው። አንደበታቸው አይጠገብም፣ ወኔያቸው፣ ነፍጥ አያያዛቸው ሀሴት ይሰጣል። እናት ወንድ ወለደች፣ ሀገርም መከታ አገኘች ይላሉ እነዚያን ጀግኖች ሲያዩ።

አሸባሪው ትህነግ ደርሶባቸው በነበሩ አጎራባች ወረዳዎች የእለት የሚበላ ምግብ ሳይቀር ከመሶብ አውርዶ እንደወሰደም ነግረውኛል። ይህን አለመዋጋት ንፉግነት ነውም ብለዋል። ግመሎቻችንም ሁሌም ዝግጁ ናቸው ነው ያሉኝ። አብዱ መሐመድ ደግሞ ሕዝባዊ ውጊያ እየተካሄደ ነው፣ ሕዝቡ ስንቅና ትጥቅ በማቀበል፣ መሀል ገብቶም በመዋጋት ታላቅ ጀብዱ እየፈፀመ ነው ብለውኛል። አካባቢያችንን አላስደፈርንም፣ ከዚያ አልፈን አጎራባች ወረዳዎች የነበረውን ጠላት እየመታን አካባቢዎችን አፅድተናል ነው ያሉት። ትህነግ ቀብሩን በዱርና በገደሉ አድርጓል፣ የሚመጣው ሁሉ አይመለሰም፣ ብዙውን ቀብረነዋል፣ የአካባቢው ሕዝብ ጀግንነቱን አስከብሯልም ነው ያሉት።
❝ጠላታችን ካልጠፋ መኖር አንችልም፣ ለዚያም ነው ሁሉን ትተን ጠላታችን ለማጥፋት ሆ ብለን የተነሳነው፣ ወያኔ ካልተቀበረ እንተኛም፣ የዘረፈውን የምናካክሰው ቀብሩ ከዚሁ ሲሆን ነው፣ ያን ስናደርግ ተክሰናል እንላለን። ከዚሁ ቀብረን ካሳችንን እንወስዳለን❞ ነው ያሉት።
ሰይድ አዲሱም አሸባሪው የትህነግ ቡድን በደረሳቸው አካባቢ አስገድደው እየደፈሩ፣ ቤት እያቃጣሉ፣ እየዘረፉ ነው ብለውናል። ሠራዊቱና የአካባቢው ማኅበረሰብ ሞገደኝነት ግብ እየመታ፣ ጠላትን እየደመሰሰ ነውም ብለዋል። ❝እሷን ጭርስርስ ካላደረግን አናቆምም፣ እኔ ሽማግሌ ነኝ፣ ልጄ እየተዋጋ ነው፣ እኔም አልመለስም ብዬ እስከመጨረሻው እፋለማታለሁ። በድላናለች፣ ሠርተን እንዳንበላ አድርጋናለች፣ ጭርስ ብላ ከተጠናቀቀች በኋላ ወደ ልማታችን እንመለሳለን❞ ነው ያሉት።
የደቡብ ወሎ ዞን የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መምሪያ ኃላፊና በሚሌ ግንባር የጦርነቱ ሂደት አስተባባሪ መሐመድ አሊ አሸባሪውን ቡድን ወደ ዞኑ እንዳይገባ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። ጠላት በሚሌ ግንባር በኩል አድርጎ ለመግባት የሚያደርገው ሙከራ በማኅበረሰቡ ንቃት ሳይደፈር ቆይቷል ብለዋል።
ከሰሜን ወሎ አጎራባች ቀበሌዎች ጋር በጋራ በመሥራት ጠላት መውጫ መግቢያ እንዲያጣና እንዲገታ አድርገናልም ነው ያሉት። ማኅበረሰቡ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በቅንጅት እንዲሠራ መደረጉንና ስንቅና ትጥቅ ለማቀበል በቀን ከ50 እስከ 100 ግመሎች እንደሚጠቀሙም ተናግረዋል። ይህንንም የአካባቢው ማኅበረሰብ እየሸፈነው እንደሆነ ነው የተናገሩት። የአካባቢው ማኅበረሰብ ባደረገው ትግል የሰሜን ወሎ አካባቢዎችን ማስለቀቁንም ተናግረዋል። እየተገኘው ያለው ድል ማኅበረሰቡ ከቀን ቀን እንዲነሳሳ እንዳደረገውና መነሳሳቱ ወጥ ኾኖ እንዲቀጥል እየተሠራ መሆኑን ነግረውናል።
እኔ ጀግንነት አይቻለሁ። ለሞት የማይሳሱ፣ ፊታቸውን የማይመልሱ ወደፊት ብቻ የሚገሰግሱ አንበሶች። ይብላኝ ለጠላት አጣብቂኝ ውስጥ ለገባው፣ ጀግኖቹማ በሚያነደው ክንዳቸው እየለበለቡ ያነዱታል፣ አመድ ያደርጉታል። ጀንበር እየሳሳ በሄደው ደመና እየተሹለከለከች ከፍ ብላለች። በጠዋት በተጠንቀቅ ቆመው የነበሩት ጀግኖች ጠመንጃቸውን አሳምረው፣ በግመሎቻቸው ስንቅና ትጥቅ ጭነው ወደ ግንባር ገሰገሱ።
❝የጩቤያቸው እንኳን አለው ሚዶ ሚዶ
አስለምደውታል የታፋ ብርንዶ❞ የሚለውን ዘፈን እያንሰላሰልኩ በወገባቸው የወረደውን ጩቤ፣ በትክሻቸው ላይ በኩራት የተቀመጠውን ነፍጥ እያየሁ በአግራሞት ተከተልኳቸው። እንኳን ጀግኖቹ ግመሎቹ ጠላት ሳይጠፋ የሚመለሱ አይመስልም። ለነፃነት፣ ለአንድነትና ለእኩልነት እንኳን ሰው ግመል ይዘምታል። እንኳን ነፍጥ ያነገተ ኢትዮጵያዊ ቀርቶ የኢትዮጵያ ድንጋይ ይማታል። ለምን ካሉ በኢትዮጵያ አይቀለድምና።
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ