“የደመራው ቋሚ እንጨት ወደየትኛው አቅጣጫ ወድቆ ይሆን?”

505

“ሕዝቤ ሆይ መስቀል በራ፤ ሀገሩ ሁሉ ይቀደስ፤ በምድር ሁሉ ሠላም ይስፈን፡፡ ክብራችንም ይመለስ፡፡”

ባሕር ዳር፡ መስከረም 17/2012 ዓ/ም (አብመድ) መስቀል በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ታላቅ ክብር የሚሰጠውና የመዳኛ ኃይል እንደሆነ በጽኑ ይታመንበታል፡፡ የመስቀል መዳኛነት ከክርስቶስ ስቅለት ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ የመስቀሉ ክብረ በዓል የሚጀምረው ንግሥት እሌኒ በጎለጎታ የተቀበረውን መስቀል ቆፍራ ካወጣችበት ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ አባቶች ይናገራሉ፡፡

የመስቀል በዓል በኢትዮጵያውያ ግን ከሃይማኖታዊ ክዋኔው ባለፈ ከሃይማኖቱ ጋር የተሳሰረ ባሕላዊ ክዋኔም አለው፡፡ መስቀል በኢትዮጵያውያን መስሪያ ቤት ተዘግቶ ሕዝቡ ሁሉ በየቤቱ አረፍ ብሎ መስከረም 17 ቀን የሚያከብረው በዓል ነው፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ መስከረም 16 ደመራ ተደምሮ አመሻሽ ላይ የሚለኮስበት ሁኔታ ያለ ሲሆን በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ደግሞ በ16 ተደምሮ በ17 አጥብያ ነው ደመራው የሚለኮሰው፡፡

ደመራው ሲደመር የተላጠ እርጥብ እንጨት መሬት ተቆፍሮ ይተከላል፡፡ የእርጥቡ እንጨት አንድምታ ዓመቱን በአዲስ መንፈስ በአዲስ ተስፋ ለመጀመር ምሳሌ እንደሆነ መርጌታ ዮሴፍ ዳኘው ተናግረዋል፡፡ በዙሪያውዋ ተደርድረው የሚቆሙት አንጨቶች ወይም ችቦዎች ደግሞ አንድነትን፣ ተደጋግፎ መኖርንና መረዳዳትን የሚያመለክቱ እንደሆነ ነው መርጌታ ዮሴፍ ያስረዱት፡፡

በሰሜኑ ክፍል ደመራው ማታ ከተደመረ በኋላ ደመራ የሰሩት የቀዬው ልጆች ደመራውን ‹‹እዮሃ አበባዬ መስከረም ጠባዬ› እያሉ ሦስት ጊዜ ይዞሩታል፡፡ ሦስት ጊዜ ከተዞረ በኋላ ሌሊቱ ሳይነጋ ተነስተው ደመራውን ለመለኮስና የመስቀሉን ማብራት ለማብሰር ቀጠሮ ይዘው ይለያያሉ፡፡

ሌሊቱ ሊነጋጋ ሲል ዶሮ መጮህ ሲጀምር የቀየው ሰዎች በየቤታቸው የሰቀሉትን ችቦ እያወረዱ የቤታቸውን ጎተራ፣ የሊጥ እቃ፣ እንስራ፣ ጋን፣ የቤቱን በር፣ የበሬውን ሻኛና የበረቱን በር እየተረኮሱ ደመራው ወደ ተሰራበት ስፍራ ይተማሉ፡፡ በተለይም የበሬዎቻቸውን ሻኛ ሲተኩሱ “በበሬው ሻኛ በላሟ ጉኛ ያለውን አውጣልን፤ ጣልልን” ይላሉ፡፡

ደመራው ከተሰራበት ስፍራ ሲደርሱ በቀየው ዘንድ የሚከበር መካሪ፣ አስታራቂ፣ ታሪክ ነጋሪ፣ ታላቁ አባት ፊት ለፊት እየመሩ ሌላው የቀየው ሰው ደግሞ ከኋላ ኋላ እየተከተለ ደመራውን ይዞራሉ፡፡
የታላቁ አባት መምራትና የሌላው ሕዝብ መከተል መከባባርን፣ መሪና ተመሪ መኖሩን ማሳያ እንደሚሆንም መምህር ዮሴፍ ነግረውናል፡፡ ደመራውን ከሁሉም ቀድመው የሚለኩሱት ታላቁ አባት ናቸው፡፡ እርሳቸው ከለኮሱት በኋላ የተሰበሰበው ሕዝብ የያዘውን ችቦ ወደደመራው ይሸጉጣል፡፡ ደማራውም ይቀጣጠላል፤ ደስታም ይሆናል፡፡

ጨለማው በብርሃን ሲገለጥ የሕዝቡ ተስፋም በብርሃኑ ይፈካል፡፡ ደመራው ተቀጣጥሎ የቀየው ሰውም በደመራው ዙሪያ ተቀምጦ ስለአዝመራውና ኑሮው እያወጋ ያነጋል፡፡ ሌሊቱ ሲነጋ እናቶች በዱባ (ዝኩኒ) ቅጠል የተጠቀለለ እርሚጦ በሌማት፣ በሰፌድ ወይም በቁና ይዘው ይመጣሉ፡፡ የደረሰ በቆሎ ካለም የበቆሎ እሸት ያመጣሉ፡፡ እናቶች ይሄን ይዘው ሲመጡ በደመራው የተቀመጡ ሰዎች ‹‹እንጎሮገባሽ›› ይሏቸዋል፡፡ እንጎሮ ገባሽ ማለት እንኳን ወደ ጓሮ ገባሽ፣ እንኳንም አዲስ እህል ይዘሽ መጣሽ ማለት እንደሆነም መሪጌታ ዮሴፍ አብራርተዋል፡፡

የመስቀል ደመራ ሌላው እንጨት ጋይቶ ሲወዳድቅ ተቆፍሮ የሚተከለው ነጭ እንጬት ብቻውን ቆሞ ይቆያል፡፡ በዙሪያው የከበበው ሕዝብም የእንጨቱን መውደቂያ በጉጉት ይጠባበቃል፡፡ ለምን ቢሉ አባቶች አራቱንም አቅጣጫ ትርጉም ስለሚሰጡትና የሚወድቅበትን አቅጣጫ አይተው ዘመኑን ለመተንበይ ስለሚችሉ ነው፡፡ ምሥራቅ፣ ምዕራብ፣ ሰሜንና ደቡብ አራቱ አቅጣጫዎች በአባቶች ትርጉም ይሰጣቸዋል፡፡

እንጨቱ ወደምሥራቅ ከወደቀ ‹‹ዘመኑ ተስፋ፣ ሠላም፣ ደስታና ፍቅር ይሆናል፡፡ እንጨቱ ወደ ደቡብ ከወደቀ ደግሞ ዘመኑ ጥጋብ ደስታ፣ ተድላ፣ ጎተራው ሙሉ ዘመኑም ስሉ የሆነ ነው›› ይላሉ፡፡ በዚህ መሠረት ለአራቱም አቅጣጫ ትርጉም ይሰጣሉ፡፡

አራቱ አቅጣጫዎች በሃይማኖቱም ትርጓሜ እንዳላቸው አባቶች ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ምሥራቅ ገነት ያለበት፤ ምዕራብ ሲዖል ያለበት፣ ሰሜን ብሔረ ሔዋን ያሉበት፣ ደቡብ ደግሞ ብሔረ ብፁዓን የሚኖሩበት ነው›› ተብሎም ይታመናል፡፡ ንግሥት እሌኒ በጎለጎታ ደመራ አስደምራ የደመራው ጪስ መስቀሉን አሳዬ፣ መስቀሉም ለዓለም አበራ፣ ጭሱ የችቦዎቹ አንድነት ነው፡፡ የአንደነቱ ጭስም መስቀሉን አስገኝቷል፡፡ መስቀሉም ለዓለም ሁሉ አብርቷል›› እንዳሉ አባቶች፡፡

ኢትዮጵያውያንም በጋራ ሲሰሩ የአንድነት ኃይላቸው አዲስ ተስፋ ያጭል፡፡ አዲሱ ተስፋቸውን እውን ሲያደርጉት ደግሞ ከራሳቸው አልፈው ለዓለም ያበራሉ፡፡ አባቶች ኢትዮጵያ በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ተባርካለችና ቅድስት ሀገር ናት ይላሉ፡፡

እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሳችሁ፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

Previous articleኢትዮጵያዊው የአትሌቲክስ አሰልጣኝ ብቸኛው አፍሪካዊ ተመራጭ ሆነዋል፡፡
Next article“ንጉሥ ዳዊት በፍቅር የተቀበለውን መስቀል ወደ ሀገሩ በክብር ማድረስ ባይችልም፤ አባት የጀመረውን ልጅ ይጨርሳልና ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ መስቀሉን ይዞ ሀገሩ ገብቷል፡፡”