
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 19/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ዳይሬክተር ጀነራል ተመስገን ጥሩነህ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው እንዳሉት አሸባሪው ቡድን ከማዕከላዊ ፖለቲካ ራሱን ሲያገል የተማመነበት ጉዳይ የፌዴራሊስት ኀይሎች በሚል አደራጅቶ የማዕከላዊ የለውጥ ፓርቲና መንግሥቱን መገዳደር ነበር፤ አልቻለም።
የመጀመሪያውን የሽንፈት ነጥብ ጣለ:: ያለህግ ምርጫ አደርጋለሁ አለ:: አደረገ::
ከመስከረም 30 በኃላ ህጋዊ መንግሥት የለም አለ:: ማንም አልሰማውም:: እሱ ግን ምርጫ አድርጊያለሁ እናም ህጋዊ መንግሥት ነኝ በሚል አዲስ መንግሥት አዋቀርኩ አለ:: የፌደሬሽን ምክር ቤት በሀገሪቱ ሕግን ተከትሎ ምርጫ የተራዘመ ቢሆንም በህገወጥ ምርጫ ለተቋቋመ ህገወጥ መንግሥት በጀት እንዳይሰጥ፤ ይሁን እንጂ የወረዳና ቀበሌ አስተዳደር አካላት በጀት በቀጥታ ከማዕከላዊ መንግሥት እንዲሰጣቸው መወሰኑን አስታውሰዋል፡፡
አሸባሪው ቡድን ክልል የሚባል ህገወጥ መንግሥት በመሆን ሁለተኛውን ነጥብ ጥሏል ብለዋል፡፡
ጡረተኛና ዘራፊ ፖለቲከኞች፣ የጦር መሪዎችና የደኅንነት ሹሞችን የሰበሰበው አሸባሪው ቡድን በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመሰንዘር ሶስተኛ ነጥቡን መጣሉንም በትስስር ገጻቸው አንስተዋል፡፡ ይህም በሀገሪቱ አሳፋሪና አስነዋሪ ታሪክ አስመዘግቧል ብለዋል፡፡
አሁን ደግሞ የአማራና አፋር ክልሎችን በመውረር ንፁሓንን በመጨፍጨፍ፣ በመዝረፍ እና በማጎሳቆል አራተኛውን ነጥብ ጥሏል ብለዋል ዳይሬክተር ጀነራሉ፡፡
አሸባሪው ትህነግ ሩብ ክፍለ ዘመን ሀገር በመራበት ጊዜ የፈፀማቸው ጥፋቶች የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም እንኳ ቢበደልም ለይቅርታ የሚሆን ልብ እና አንጀት ይቅርታን አግኝቶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ይሁን እንጅ ይቅርታ ይሉኝታን ለሚያውቅ በኢትዮጵያዊ ጨዋነትና ሥነ ምግባር ተኮትኩቶና ተገርቶ ላደገ እንጂ ሳያውቅ አውቃለሁ ለሚል፤ ሳይማር ተማርኩ ለሚል፤ ማታለሉ እየታወቀበት እንደማይታወቅበት ለሚያስብ ብልጣብልጥ፤ እየዘረፈ መዝረፍ ከፈጣሪው የተሰጠ ፀጋ ለሚመስለው ወመኔ፤ ሞቶም አልሞትኩም ለሚል እርኩስ መንፈስ ለተጠናወተው፤ እርሱ ከሌለ ትውልዱም እንዲጠፋ ለሚፈርድ ፍርደ ገምድል እንደማይሰራ ተረጋግጧል ብለዋል::
ይህ የአሸባሪው ቡድን አስተሳሰብ ደግሞ የጥቂት ዘራፊ፣ ቀማኛ፣ ውሸታም፣ ገዳይ ወንበዴና አሸባሪ ጡረተኛ ቡድን ብቻ አለመሆኑን አንስተዋል፡፡
‹‹የዓለም የዴሞክራሲ አስተማሪዎች ነን ባዮች፣ በጊዜ መዛባት እና ኢ-ፍትሐዊ ዓለማዊ ሁኔታ አድገናል የሚሉ ሀገራት፣ ይህ አሸባሪ ቡድን ሀገራችንን ለማፍረስ ችግሩን ከመጠንሰስ ጀምሮ የሚያደርገውን ግልፅ የንፁሓን ጭፍጨፋ፣ ዘረፋ፣ ወረራ ወዘተ… ነውረኛ ድርጊቶች እንኳን ሊገስፁ ቀርቶ እንዲያውም ቀለብ ከመስፈር ጀምሮ የህክምና መድኃኒቶችና የመገናኛ መሳሪያዎችን እያመቻቹ መገኘታቸው ሳያንስ፣ መንግሥትን ሲተቹ፣ ሲጎነትሉና ሲያስፈራሩ ማየት ልብን ያደማል፤ ጨጓራ ይመልጣል፤ ቆሽትን ያሳርራል›› ብለዋል ዳይሬክተር ጀነራሉ፡፡
ጨው ሲበዛ ይመራል እንዲሉ እነዚህ አካላት እንደ ትኋን እየመጠመጡን እንደማይዘልቁ አንስተዋል፡፡ ከውስጥ ባንዳዎች ጋር በመተባበር የሚሰሩት ሥራ እንደተደረሰበትም ጠቅሰዋል፡፡
‹‹ለአሁኑ ከሳሽም፣ ፈራጅም፣ አልቃሽም አንጋሽም፣ አጣሪም መርማሪም፣ ጯሂም ገላጋይም እነሱው በመሆናቸው እውነት ብንይዝም ጆሮ ዳባ ለብሷል፤ ፍትሕና ርትዕም ተቀብሯል›› ብለዋል፡፡ ‹‹የትኛውም ቦታ ቢሆን አሸባሪውን ቡድን እና ተባባሪዎቹ የእጃቸውን ያገኛሉ፤ ሞትን ይመርጣሉ እንጅ ኢትዮጵያውያን በነፃነታቸው ላፍታም አይደራደሩም›› ነው ያሉት፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ