
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 18/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው፣ ዘራፊውና ወንበዴው የትህነግ ቡድን በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያውያን ላይ በከፈተው ጦርነት የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ፣ ፋኖ እና ከሌሎች ክልሎች የመጡ ልዩ ኀይሎች እየተፋለሙት ነው።
ሀገርና ሕዝብን ክዶ በሕዝብ ላይ ጦርነት ከፈተ፣ ሃብትና ንብረት አወደመ፣ ንፁኃንን በግፍ ጨፈጨፈ። ታዲያ የትህነግ ክፉ ሥራ ያስቆጣቸው ኢትዮጵያውያን ከዳር ዳር ተንቀሳቅሰው ሊያሳድዳቸው እንዳሰበ እያሳደዱት፣ ሊገድላቸው እንደከጀለ ሁሉ እየገደሉት፣ ከምድራቸው እያፀዱት ነው።
የትህነግን አሸባሪ ቡድን ከኢትዮጵያ ምድር፣ ከኢትዮጵያውያን ጀርባ ለማላቀቅ በወሎ ግንባር የተሰለፈው የተቀናጀው ሠራዊት ከድል ላይ ድል እየፈጸመ እየገሰገሰ ነው።
በግንባር ያገኘነው መሠረታዊ ወታደር ገመቹ በዳሱ ጠላትን በየትኛውም ቦታና ጊዜ እየተዋጋን እየደመሰስን ነው ብሏል። ጠላት በገባበት እየገባን እየደመሰስን ወደፊት እየገሰገሰን ነው፣ ጠላትም እየሸሸ ነው ብሏል።
አሸባሪው ቡድን ወደ ትግራይ ክልል ተመልሶ እንዲሄድ ሳይሆን አሁን በገባበት ሥፍራ መቃብሩን ማዬት እንደሚፈልግም ነግሮናል። ጠላትን በገባበት የማስቀረት ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ተናግሯል።
እስካሁን አሸባሪውን ቡድን እየመታንበት ያለው መንገድ አስደሳች ነው ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ደምስሰን ሰላምን እናረጋግጣለን፣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ትህነግ የሚባል አሸባሪ ቡድን አይኖርም፣ በአዲስ ዓመት አዲስ መንፈስ፣ ከጠላት የፀዳች ሀገር እንድትኖር እናደርጋለንም ብሏል።
ከሠራዊቱ ጋር በቅንጅት እየተፋለመ ያገኘነው የአማራ ሚሊሻ አበበ አስማው አሸባሪውን ትህነግ ደምስሰን ሀገራችን ሰላም ለማድረግ እየተፋለምን ነው ብሏል። የትህነግ አሸባሪ ቡድንን እየደመሰስን እየገሰገስን ነው፤ ከሠራዊታችን ጋር በመሆን በአጭር ጊዜ ድል እናመጣለንም ነው ያለው።
ሌላኛው የሚሊሻ አባል ደረጀ ብርሌው ወራሪውን ቡድን እየደመሰስን ቦታዎችን እያሰለቀቅን፣ አካባቢውን እያፀዳን ወደፊት ቀጥለናል ብሎናል። ጠላት በትጥቅም ሆነ በጦር ስልት ከእኛ ጋር አይመጣጠንም ያለው ደረጀ አጥፍተን እንጥፋ ካልሆነ በስተቀር እኛን የመቋቋም አቅም የላቸውም ብሏል።
ጠላትን ሙትና ቁስለኛ እያደረጉ ወደፊት እየገሰገሱ መሆናቸውንም ተናግሯል። ሕዝቡ እያደረገው ያለው ድጋፍ ለድል እንዲበቁ እንዳበረታታቸውም ገልጿል።
ከሠራዊቱ ጋር ያላቸው ቅንጅት አስደናቂ መሆኑንም ነግሮናል።
ዓላማችን አሸባሪውን ቡድን ድል እያደረጉ ወደፊት መገስገስ ብቻ ነውም ብሏል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ተልዕኳችንን እናጠናቅቃለን፣ ጠላትንም እንዳይመለስ አድርገን እንቀብራለን ነው ያለው።
የሠራዊት አባላቱ መዳረሻቸው የሀገርና የሕዝብ ጠላት የሆነው አሸባሪ ቡድንን ደምስሶ ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ ነው። የሚያቆመን ድል ማድረግ ብቻ ነውም ብለውናል።
ቆፈን ሳይበግራቸው፣ ተራራና ሸንተረሩ፣ ዋሻና ገደሉ ሳያስቆማቸው፣ የሀገርና የሕዝብ አደራ ከስንቅና ከትጥቃቸው በላይ ተሸክመው ዓልመው እየተኮሱና ጠላትን እየደመሰሱ ጉዟቸውን ቀጥለዋል።
የማይሸነፍ ታሪክ ባላደራዎች፣ የዚህ ዘመን ታሪክ ሠሪዎች፣ የነገ የታሪክ አደራ አስቀማጮች የአረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ አፍቃሪዎች እና እስከ ሞት ድረስ ተጓዦች ድል መትተው፣ ሕዝብ አኩርተው እራሳቸውም ኮርተው ለመኖር ሳይሰስቱ ሕይወት እየሰጡ ነው።
ለኢትዮጵያ ደም ማፍሰስ፣ አጥንት መከስከስ ለእነርሱ የእየዕለት ሥራቸው ሆኗል። ደግሞም አሸንፈው ይመለሳሉ። ጠላትን በሀፍረት ያስለቅሳሉ።
ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m