“ወጣቱ በየአካባቢው መከላከያ ሠራዊታችንን መቀላቀል አለበት” የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው

232

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 18/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ወጣቱ መከላከያ ሠራዊትን መቀላቀልና ማጠናከር እንዳለበት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የሀገሪቱን ሕልውና ለመጠበቅና ሕዝቧን ለመታደግ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ ትግል እያካሄደ እንደሚገኝ አቶ ገዱ ተናግረዋል፡፡ እናት ሀገሩን ላለማስደፈር ዋጋ እየከፈለ እንደሆነም አንስተዋል፡፡

የአማራ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ፣ ፋኖ እና ከየክልሎች የተውጣጡ የልዩ ኀይል አባላት ከሠራዊቱ ጎን ተሰልፈው አሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ እየሠሩ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ወጣቱም ግንባር በመሰለፍ እና ምልምል ወታደር ሆኖ መከላከያ ሠራዊትን በማጠናከር ርብርብ እያደረገ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ዘመቻው በስኬት እንዲጠናቀቅ ሁለንተናዊ ድጋፍ እያደረገ ነው የሚገኘው፤ ኀይሉ እየተመናመነ ያለውን አሸባሪ ቡድን ለመደምሰስና ሀገርን ወደ ተረጋጋ ሁኔታ ለመመለስ የተጀመረው ትግል በተደራጀ አግባብ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

አቶ ገዱ እንዳሉት ጠላት በሕዝባዊ ንቅናቄ ብቻ ስለማይመለስ ወጣቱ ወታደር መሆን ይጠበቅበታል፤ ለዚህም ውትድርና መሰልጠን አለበት ብለዋል፡፡

አሸባሪው ቡድን የኢትዮጵያ ሕዝብ አንቅሮ የተፋው በመሆኑ ፖለቲካዊ መሠረት የለውም፣ ሕዝቡን አንገት ለማስደፋት እየሠራ በመሆኑም ይህንን ቡድን ማምከን የሚቻለው በወታደራዊ ኀይል እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡ በመሆኑም ወጣቱ በተለይ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ለማጠናከር ተመዝግቦ፣ ሰልጥኖ እና ተደራጅቶ ጠላትን መዋጋትና ሀገሩን ማስከበር ይገባዋል ብለዋል፡፡

ወጣቶች ሰርጎ ገቦችን ለመያዝ እያደረጉት ያለው ርብርብ የሚበረታታ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

በውስጥ ሆነው እርስ በእርስ ቅራኔ እንዲፈጠር፣ የወገን የጸጥታ ኀይል እንቅስቃሴ እንዲስተጓጎል፣ በመሪውና በወጣቱ፣ በሕዝብና በፖለቲካ መሪ መካከል አለመግባባት እንዲፈጠር የሚሠሩ መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ወጣቱ ለጠላት መጠቀሚያ እንዳይሆን ሁኔታዎችን አገናዝቦና ተደራጅቶ በአንድ የዕዝ ሰንሰለት መሥራት እንደሚኖርበት መክረዋል፡፡ ጠላት ተደራጅቶና ሰልጥኖ ጦርነት መክፈቱን በማንሳትም የአማራ ወጣት መከላከያ ሠራዊትን፣ ልዩ ኀይሉን እና ሚሊሻውን እንዴት ማጠናከር እንዳለበት ማሰብ ይገባዋል ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleአሸባሪው የትህነግ ቡድንን መደምሰስ ብቻ ሳይሆን ያወደማቸውን ሃብቶች መልሶ ማልማት እንደሚገባ በጨጨሆ ግንባር የተገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ፡፡
Next article“በእያንዳንዷ ቀን እያደገ የሚሄድ ሥነ ልቡናዊ፣ አካላዊ እና ቁሳዊ ዝግጁነት ሁልግዜም ከሁላችንም ይጠበቃል” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ