
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 18/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና፣ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኀይል ንቅናቄ (አዴኀን) ፓርቲ አመራሮች በጋይንት ግንባር ጨጨሆ ተገኝተው የመከላከያ ሠራዊቱን ተጋድሎ ተመልክተዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ዮሐንስ ቧያለው ወደ ጨጨሆ ግንባር የመጣነው በአካባቢው ያለውን ሁኔታ ለመቃኘት፣ ከወገን ኃይል ጎን መሆናችንን ለማሳየት ነው ብለዋል። አሸባሪውን ቡድን ይዟቸው የነበሩ ቦታዎችን ማስለቀቅና መያዝ ሳይሆን ቡድኑ ከገባበት እንዳይወጣ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ ትምህርት ቤቶችን፣ የመንግሥትና የግል ተቋማትን አውድሟል፣ የግለሰብ ቤቶችን አቃጥሏል፣ ሴቶችን ደፍሯል፣ ወጣቶችን ገድሏል ሌሎች በርካታ ጥፋቶችንም ፈጽሟል ብለዋል።
የሽብር ቡድኑ ያጠፋው ጥፋት ቀላል ስላልሆነ በሚደረገው የመልሶ ግንባታ ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን ሊቆም እንደሚገባ ገልጸዋል።
ከሕዝብ ጋር ሆነን የወደሙ ማኅበራዊ ተቋማትን እንገነባለን ነው ያሉት፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ጣሒር ሙሐመድ ሠራዊቱን ለማበረታታት፣ በአጥፊው ቡድን የተጎዱትን ዜጎችና የወደሙትን ንብረቶች ለመቃኘትና እድሳት ለማድረግ ያለንን ትብብር ለማሳየት ወደ ጨጨሆ ግንባር መጥተናል ብለዋል። የሽብር ቡድኑን መደምሰስ ብቻ ሳይሆን በጦርነት ቀጣና የወደሙትን ንብረቶች በጋራ ርብርብ መተካት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ሊቀመንበር የሽዋስ አሰፋ አሸባሪ ቡድኑ ተጨማሪ ጉዳት ሳያደርስ መወገድ አለበት ነው ያሉት፡፡ የወደሙ የመንግሥትም ሆነ የሕዝብ ንብረቶችን መልሶ መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ (አዴኃን) ሊቀመንበር ተስፋሁን ዓለምነህ ጸረ አማራና ኢትዮጵያ የሆነውን የሽብር ቡድን መላ አባላቶቻችንን በማንቀሳቀስ እየታገልነው ነው ብለዋል። የሽብር ቡድኑ የሚደመሰስበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጨጨሆ ግንባር መገኘታቸውን አቶ ተስፋሁን ተናግረዋል። ቡድኑ ተራ የሽፍታነት ሥራ እየፈጸመ ነው ብለዋል።
ቡድኑ መላ ኢትዮጵያውያንን አደጋ ላይ ስለጣለ የወደሙ ንብረቶችን ለመተካት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ተባብረው ሊተኩ እንደሚገባ ሊቀመንበሩ ጥሪ አድረገዋል።
ዘጋቢ:- ብሩክ ተሾመ – ከጨጨሆ ግንባር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ