
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 18/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የይባብ ካምፓስ ተነሽ የበጎ አድራጎት ማኅበር አባላት አሸባሪውን ትህነግ ለመደምሰስ በግንባር እየተፋለሙ ላሉ የመከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ ደም ለግሰዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ በሥልጣን ዘመኑ አማራን ከቀዬው አፈናቅሏል፣ ገድሏል፣ ዘርፏል፡፡ ይህ አልበቃ ብሎት ዛሬም ለዳግም በደል ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በአማራና በአፋር ክልሎች ወረራ ፈጽሟል።
ይህ የአሸባሪ ቡድኑ እኩይ ድርጊት በእውነተኛ የኢትዮጵያ ልጆች የተባበረ ክንድ እንደማይሳካለት የይባብ ካምፓስ ተነሽ የበጎ አድራጎት ማኅበር አባላት ተናግረዋል፡፡
ወጣት ስንታየሁ ንጋቴ በባሕር ዳር ከተማ የቀበሌ 16 ነዋሪ ነው። ስንታየሁ የባሕር ዳር ከተማ የይባብ ካምፓስ ተነሽ በጎ አድራጎት ማኅበር ባዘጋጀው የደም ልገሳ መርኀ ግብር ላይ ተገኝቶ ደም ለግሷል፡፡ ስንታየሁ “የተደቀነብንን የህልውና አደጋ በድል ለመወጣት ወጣቱ ደም ከመለገስ በተጨማሪ መደራጀት፣ መሠልጠን፣ እንዲሁም ወደ ግንባር ሄዶ የሀገሩን ህልውና ማስከበር አለበት” ብሏል፡፡

ስንታየሁ የበጎ አድራጎት ማኅበሩ አባላት እና ማኅበረሰቡ ተደራጅቶ አካባቢውን ነቅቶ እየጠበቀ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ወጣቶች ሐሰተኛ መረጃ ከሚያሰራጩ የሽብርተኛው ትህነግ ተላላኪዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁም መልዕክት አስተላልፏል፡፡
ወጣት ጥሩዬ ዓይናለም የባሕር ዳር ከተማ የቀበሌ 16 ነዋሪ ናት፤ ጥሩዬ የባሕር ዳር ከተማ የይባብ ካምፓስ ተነሽ ወጣቶች በጎ አድራጎት ማኅበር ባዘጋጀው የደም ልገሳ መርኀ ግብር ላይ ደም ለግሳለች፤ ጥሩዬ ግንባር ላይ የሕዝቡን ደኅንነት፣ የሀገርን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ አጥንቱን ለሚከሰክሰው፣ ደሙን ለሚያፈሠው መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ ደም መለገሷ እንዳስደሰታት ነግራናለች፡፡
“ሽፍታ ሀገር አይገዛም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሽፍታው፣ ወራሪው እና አሸባሪው ትህነግ አይንበረከክም፤ ተባብረን እናሸንፋለን” ነው ያለችው፡፡
ማኅበረሰቡ ከደም ልገሳው ጎን ለጎንም መደራጀት እና አካባቢውን መጠበቅ አለበት፤ መረጃን ከትክክለኛ ምንጭ በመከታተልም የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጠይቃለች፡፡

መከፈል የሚገባው መስዋእትነት ተከፍሎ ሀገር መቀጠል እንዳለባትም ነው የተናገረችው፡፡
ሌላኛው እስተያየት ሰጪ አስቻለው ምትኩ የተጠባባቂ ኀይል ወታደራዊ ሥልጠና ወስዷል፤ ወደ ግንባር ለመሄድም እየተጠባበቀ ነው፡፡ ደም በመለገስም ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ነግሮናል፡፡
አስቻለው “በሰላም ለመኖር እኛ ወደ ግንባር መዝመት አለብን፤ አሸባሪው የትህነግ ቡድን በሕጻናት፣ በወጣቶች፣ በሴቶች፣ በአቅመ ደካሞች እና አካል ጉዳተኞች ላይ በደል እየፈጸመ ነው፤ ይኽን ነውረኛ ቡድን ለመደምሰስ ደም መለገስ በቂ አይደለም፤ ግንባር በመሰለፍ ልኩን ማሳየት ይጠበቅብናል” ብሏል።
ብሩክ ልዑል ሰገድ በባሕር ዳር ከተማ ወጣቶች የበጎ አድራጎት ማኅበር አስተባባሪ ነው፡፡ በጎ አድራጎት ማኅበሩ ወጣቶችን ደም እንዲለግሱ በማስተባበር ሠፊ ሥራ እየሠራ መሆኑን ነግሮናል፡፡ ብሩክ ከደም ልገሳው በተጨማሪ በአካባቢው ከሚኖሩ የይባብ ካምፓስ ተነሽ የማኅበረሰብ ክፍሎች 80 ሺህ ብር በማሰባሰብ ለሀብት አሰባሳቢ ግብረ ኀይል ለማስረከብ መዘጋጀታቸውን ገልጿል፡፡
ከደም ልገሳው ባለፈም ሥንቅ የማዘጋጀት፣ ሀብት የማሰባሰብ ሥራውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቋል፡፡ አካባቢያቸውን ከሠርጎ ገቦች የመከላከል ሥራ እንደሚሠሩም ገልጿል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ