
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 18/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአሸባሪው ትህነግ የተፈጸመውን ወረራ ለመመከት፣ተፈናቃዮችን ለመርዳት እና የደረሰውን ውድመት መልሶ ለማቋቋም ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ የአማራ ክልል መንግሥት አስታውቋል፡፡
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊና የሕልውና ዘመቻ ስንቅ ዝግጅት ንዑስ ኮሚቴ አስተባባሪ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ የማኅበረሰብ ስንቅ ዝግጅትን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ከሐምሌ 1/2013 ዓ.ም ጀምሮ የሦስት ወራት እቅድ በማዘጋጀት ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል በስንቅ ዝግጅት ለማሳተፍ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ዶክተር ሙሉነሽ ማብራሪያ ባለፉት 15 ቀናትም 29 ሺህ 188 ኩንታል ስንቅ ተሰብስቧል፤ 15 ሺህ 966 ኩንታል ስንቅ ወደ ግንባር ተልኳል፡፡ ድጋፉ በግንባር አቅራቢያ ያለው ማኅበረሰብ ከሚያቀርበው ስንቅ ውጪ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡ የእርድ እንስሳት፣ ዘይት፣ ውኃ፣ ብስኩት፣ መኮረኒ፣ ፓስታ፣ ከ7 ሺህ ዩኒት በላይ ደምና ሌሎች ቁሳቁሶች ተሰብስቧል፡፡ ድጋፉ ከባለሀብቶች የተሰበሰበውን አይጨምርም፡፡
የክልሉ መንግሥት ጦርነቱን ለመመከት 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዷል፡፡ ድጋፉ ጥሩ እንቅስቃሴ የታየበት ቢሆንም ከዕቅዱ አንጻር በከፍተኛ ደረጃ መሥራት እንደሚጠይቅ ተጠቅሷል፡፡
ጦርነቱን በድል ለማጠናቀቅ እና በጦርነቱ የደረሰውን ውድመት መልሶ ለማልማት አሁንም ከአይነትና ከገንዘብ ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል፡፡ የተጋረጠውን አደጋ እና የወገን ኀይል ብዛት ታሳቢ ባደረገ መልኩ ተጨማሪ የስንቅ ድጋፍ እንዲደረግ ብዙ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ የፌዴራል የመንግሥት ሠራተኞችና ሌሎች የግል ሠራተኞችም ሁኔታውን በመገንዘብ ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የሠራዊት አባላት ለሀገራቸው ሕይወታቸውን እየሰጡ ነው፤ ከሕይወት በመለስ ያለ ሀብት ትንሽ ነገር በመሆኑ ሀገር መውደድን በተግባር የምናሳይበት ጊዜ አሁን ነው ብለዋል ዶክተር ሙሉነሽ፡፡ ሁሉም በአቅሙ አስተዋጽኦ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ሆስፒታሎች ደም ይፈልጋሉና ከገንዘብና ቁሳቁስ ድጋፍ በተጨማሪ መስፈርቱን የሚያሟላ ሁሉም ሰው ደም መለገስ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ ለዘማች ቤተሰብ እንክብካቤ የማድረግ፣ ሰብል የመንከባከብ ሥራ ሊከናወን እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ዶክተር ሙሉነሽ ‹‹የአማራ እናቶች፣ እህቶች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች ሕይወቱን ለሚሰዋው መከላከያ፣ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻና ፋኖ በቂ ስንቅ ማቅረብ አለብን›› ብለዋል፡፡ “አሁን የመስጠት ጊዜ ነው፣ ኢትዮጵያን ለማትረፍና እንደ ሕዝብ ለመትረፍ በአንድ ላይ የምንቆምበት ጊዜ አሁን ነው” ብለዋል፡፡
ወረራውን ተከትሎ ከፍተኛ ዝርፊያ፣ ውድመት ደርሷል፤ከጦርነቱ አካባቢዎች በርካታ ሰዎች ተፈናቅለዋል፤ በመሆኑም ለእነዚህ ተፈናቃዮች ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል፡፡
ዶክተር ሙሉነሽ እንዳሉት በሕልውና ዘመቻው ባለሀብቶች ትልቁን ድርሻ ሸፍነዋል፤ ለዚህም የክልሉ መንግሥት እውቅና ይሰጣል ብለዋል፡፡
ለህልውና ዘመቻው እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡-ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ