
ባሕር ዳር: ነሐሴ 18/2013 ዓ.ም(አሚኮ) የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል በወሎ ግንባር ለሚገኘው ሠራዊት ድጋፍ አድርጓል።
ክልሉ የሀገርን ክብርና የሕዝብን ነፃነት ለማስከበር ለሚዋደቀው የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ለሦስተኛ ጊዜ ነው ድጋፍ ያደረገው። ክልሉ ለሠራዊቱ የላከውን ድጋፍ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት ተዋካዮች ናቸው በወሎ ግንባር ያስረከቡት።
ከክልሉ የተላከውን ስጦታ ያበረከቱት የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች እስከመጨረሻው ድረስ ከሠራዊቱ ጋር እንደሚሆኑ አረጋግጠዋል።
ልጆቻችን ልናይ ያሉበትን ቦታ ልንመለከት፣ ተጋድሏቸውንም ለመደገፍ መጥተናል ፤ ደስታኖች ነንም ብለዋል። በሠራዊቱ እንኮራለን፣ እንመከላን ተመክተንም ድል እናያለን ፤ እናሸንፋለን ነው ያሉት።

የደቡብ ክልል የሀገር ሽማግሌ ሀይች ዓለማየሁ ሕርቤ አባዮ የኢትዮጵያ አምላክ ከእናንተ ጋር በመሆኑ በድል ታጠናቅቃላችሁ ነው ያሉት። የደቡብ ሕዝብና መንግሥት አድርሱ ያለነን ሰንጋዎች ይዘን መጥተናል፣ ዘመቻው በድል እስከሚጠናቀቅ ድረስ በሁሉም ረገድ የደቡብ ሕዝብና መንግሥት አጋርነቱ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የሃይማኖት አባት ገራድ ሙንዲኖ ሁሴን ሚሴ የደቡብ ሕዝብና መንግሥት ከመከላከያ ሠራዊት ጎን ነው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎናችሁ ነውም ብለዋል። ሀብት ያለው በሀብቱ የሚመካው፣ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ የሚመካው እናንተ ሰላም ስታመጡና ከእናንተ ጋር ሲሆን ነውም ብለዋል።
ሌላው የሀገር ሽማግሌ አለቃ መለቦ መንቻ እናንተ ጣልያንን ድባቅ የመታው አባቶች ልጆች ናችሁ፣ ከእውነተኛ ትግል የተነሳችሁ፣ በእውነተኛው የትግል መንገድ እየተጓዛችሁ ያላችሁ ጀግኖች ናችሁና ድል ከእናንተ ጋር ነው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከእናንተ ጋር ነው፤ ሐሳብ ሳይገባችሁ ለማይቀረው ድል ገስግሱ ነው ያሉት።
የደቡብ ክልል ርእሰ መሥተዳድር የጸጥታና ደኅንነት ጉዳዮች አማካሪና የክልሉ ተወካይ ኩታዬ ኩስያ አባቶቻችን በጀግንነት ያስረከቡንን ሀገር በጀግንነት እናስረክባለን ብለዋል። ጠላት ሀገርን ሊያፈርስ አይችልም፣ በእኛ ዘመን ኢትዮጵያ አትፈርስም፣ አይደለም የውስጥ ባንዳ የውጭ ጠላትም ኢትዮጵያን ማፍረስ አልቻለም ብለዋል።

ኢትዮጵያን ለመግዛት የሚሻ የውጭ ጠላት አይሳካለትም፣ ባንዳም ተሸንፎ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች ሲሉ ገልጸዋል። ጠላታችን የኢትዮጵያውያንን እንባ ረግጦ የተነሳ ከሀዲ ቡድን ነውም ብለዋል። ጠላታችን የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያን እንጂ ለአማራ ክልል ብቻ የሚሰጥ አይደለምም ነው ያሉት። ከታሪክ ላይ ታሪክ ጨምረን ሀገር እናሻግራለን እንጂ ሀገር አናፈርስም ብለዋል። የደቡብ ክልል መንግሥትም ከመከላከያ ሠራዊት ጎን ነው፤ ትግሉን በአጭር ጊዜ ጨርሰን ወደ ልማት እንደምንሄድ አንጠራጠርምም ነው ያሉት። ከእናንተ ጋር የጦር መሳሪያ ብቻ ሳይሆን እውነት ስላለ አሸናፊዎች ናችሁም ብለዋቸዋል።
ስጦታውን የተቀበሉት የ13ኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ኮሎኔል ሀሽም መሐመድ ረጅም ኪሎሜትሮችን አቆራርጣችሁ እዚህ ድረስ መጥታችሁ ስላያችሁን ኩራት ይሰማናል ነው ያሉት። ሥራው ትልቅ ነው፣ ሀገርን የማዳንና ዳር ድንበር የማስከበር ወሳኝ ሥራ ነው ብላችሁ ስለመጣችሁ ክብር ይገባችኋልም ብለዋል።
የሕዝባችን ስጦታና ምክር የበለጠ እንድንጠነክር እና ለድል እንድንገሰግስ ያደርገናል ብለዋል። የሕዝብና የመንግሥት ድጋፍ ትጥቃችንና መንፈሳችንን ያጠነክረዋልም ብለዋል። ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመቀናጀት ትልቅ ሥራዎችን እየሠራን ነው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የድል ዜና ትሰማላችሁ ነው ያሉት። ሳንፈልግ ተገድን የገባንበት ጦርነት ነው፣ ሠራዊቱ እውነትን ይዞ ያለ እረፍት እየተዋጋ ነው፣ ማሸነፉ የማይቀር ነውም ብለዋል። በአባቶች ፀሎት፣ ድጋፍና በሠራዊቱ ብርታት በቅርብ ጊዜ የተሻለ ሥራ ሠርተን ሕዝባችንን እናረካለን፣ ሕዝባችን ወደ መደበኛ ሰላሙ እንመልሰዋለንም ብለዋል።ሕዘቡ ወደ ልማቱ እንዲመለስ እናደርጋለን ነው ያሉት።
ሠራዊቱ ለደቂቃም ቢሆን ሕዝቡ እንዳልተለዬው ያምናል፣ የሕዝብን ድጋፍ ይዘን የማናሸንፈው ጦርነት የለም ብለዋል። ለስጦታውም አመስግነዋል።
❝እናንተ ቆጥባች እንዳልሰጣችሁን ሁሉ እኛም ያለንን አንቆጥብም፤ ውድ ሕይወታችንን ከፍለን የሀገራችን ታሪክ እናስከብራለን። የተበላሸ ታሪክ አንሰጥም የሚያኮራ ታሪክ እናስረክባለን❞ ብለዋል።
ክልሉ 2 ሚሊዮን በሚጠጋ ብር የተገዙ 55 ሰንጋዎችን ለመከላከያ ሠራዊቱ አስረክቧል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ