በደሴ ከተማ ስምንት የአሸባሪው ቡድን ሰርጎ ገቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡

274

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 18/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ አስተዳደር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አበበ ገብረመስቀል እንዳሉት ለከተማዋ ደኅንነት መጠበቅ የተለያዩ ግብረኃይሎችን በማቋቋም እየተሠራ ይገኛል፡፡ በዚህ ተግባርም ማኅብረሰቡን ያሳተፈ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የጠቀሱት፡፡

የጸጥታና ደኅንነት መዋቅሩ ባከናወነው ሥራ 354 ተጠርጣሪዎች ተይዘው ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከተጠርጣሪዎች ውስጥ ስምንቱ ከአሸባሪው የትህነግ ቡድን ጋር ግንኙነት እንዳላቸው አረጋግጠዋል፡፡

ፀጉረልውጥን በመከታተል ረገድ ሁሉንም ኬላዎችና በሮች በጥብቅ የመፈተሸ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ወጣቱ አካባቢውን እንዲጠብቅ እየተሠራ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡ ከፍርድ ቤት ጋር በመቀናጀት በተከናወነ የቤት ለቤት እና የአልጋ ቤት ፍተሻ በርካታ የጦር መሳሪያ መገኘቱንም አስታውቀዋል፡፡

የአካባቢ ጥበቃ ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ የሥራ ኀላፊዎች የተቀናጀ ሥራ እየሠሩ ይገኛል ያሉት ከንቲባው ሁሉም የከተማው የጸጥታ ኃይል በአንድ ማዕከል ሥር እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

ከንቲባ አበበ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በሎጅስቲክ ግብረ ኃይል ከሕዝቡና ከባለሃብቱ የተዋቀሩ ኮሚቴዎች ለመከላከያ፣ ለልዩ ኀይልና ለሚሊሻ ስንቅ እየተዘጋጁ ነው። ከ136 ሚሊየን በላይ ገንዘብ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አሸባሪው ትህነግ በወረራቸው አካባቢዎች ከ99 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ወደ በደሴ እንደተጠለሉ የገለጹት ከንቲባው በስምንት መጠለያ ጣቢያዎች እንዲያርፉ መደረጉንም አመላክተዋል፡፡ የደሴ ከተማ ሕዝብና ወጣቱ በተለያየ አደረጃጀት ምግብና ልዩ ልዩ ድጋፍ እያደረገላቸው እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡

ተፈናቃይ ወገኖች ወደቀያቸው እስከሚመለሱ ድረስ ረጅ ድርጅቶች እገዛ ሊያደርጉልን ይገባል ነው ያሉት።

ዘጋቢ፡- ካሳሁን ኃይለሚካኤል – ከደሴ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article“ሽብርተኛው ትህነግ ከእኛ የተሻለ መሳሪያ ቢታጠቅም አልሞ ተኳሽ በመሆናችን ልናንበረክከው ችለናል” የእስቴ ወረዳ አርሶ አደሮች
Next article“የሕልውና ዘመቻውን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ኅብረተሰቡ የሚያደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል” ዶክተር ሙሉነሽ አበበ