
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 17/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪውን ትህነግ በመደምሰስ የተገኘው ድል በጉና ተራራ ታሪክ እንዲደገም ማድረጉን የእስቴ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡ ወራሪው እና አሸባሪው ትህነግን ለመደምሰስ የታወጀው የህልውና ዘመቻ በርካታ ታሪክ የማይረሳቸው ጀግኖችን ፈጥሯል። 11 የወራሪውን እና አሸባሪውን ትህነግ አባላት የረፈረፈው የክምር ድንጋዩ ጌጤ መኳንንት (አባ ረፍረፍ)፣ የጋንታ መሪውን ጨምሮ ሦስት የሽብርተኛው ተላላኪዎችን የረፈረፈው የጋይንቱ አቶ ተመስገን ነጋሽ ከበርካቶቹ መካከል ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።
ዛሬም ኅብረተሰቡ ተበታትነው መግቢያ የጠፋቸውን የአሸባሪው ትህነግ ርዝራዦችን እየለቀመ ቀሪዉን ደግሞ እየማረከ ይገኛል። የእስቴ ወረዳ የዳት፣ ድባና፣ ደስኳ፣ አንጋጫት፣ አጎና እና ዱርጌ ማሸንት ቀበሌ አርሶ አደሮች በመደራጀት በጉና ተራራ ላይ በታሪክ የሚዘከር ጀብድ ፈጽመዋል።
በጉና ተራራ ተሻግሮ እስቴ፣ ስማዳን እና ደብረ ታቦር ከተሞችን ከተሳካለትም ሀገርን ለመውረር አሰፍስፎ ሲክለፈለፍ የነበረውን አሸባሪውን ትህነግ በእስቴ አርሶ አደሮች ጉና ተራራ ላይ ተቀብሮ ቀርቷል፡፡ ቀሪውም ወደ ኋላ ፈርጥጧል።
አቶ ውለታው ገላው ሁለት ቀን በፈጀው ውጊያ የሽብር ቡድኑ አባላትን ሲፋለሙ በመቆየት ተገቢዉን ቅጣት እንደሰጡት ተናግረዋል። “ጠላት ከእኛ የተሻለ መሳሪያ ቢታጠቅም አልሞ ተኳሽ በመሆናችን ልናንበረክከው ችለናል” ብለዋል። የአጥፍቶ ጠፊዉን ቡድን መደምሰስና መማረክ መቻላቸዉን ነው አርሶ አደሩ የተናገሩት። አቶ ውለታው የሽብርተኛው ትህነግ ቡድንን ለመረፍረፍ ቀድመው ዝግጅት ሲያደርጉ እንደነበር ነግረውናል።
በትግሉ ወቅት የወረዳው አስተዳደር የመሳሪያ ድጋፍ እንዳደረገላቸው አቶ ውለታው አስረድተዋል። በውጊያው ወቅት የሴቶች ተሳትፎም የላቀ መሆኑን አስታውሰዋል።
ወጣት ጥጋቡ ውለታው የተገኘው ድል የጉና ተራራ ታሪክ እንዲደግም ያደረገ ነው ብሏል። “እሁድ ደብረ ታቦር ነበርኩ፤ ጠላት አካባቢዬን ለመውረር መምጣቱን ስሰማ ሰኞ ስዋጋ ዋልኩ፤ በዚህም በርካታ ጠላትን ለመጨፍጨፍ ችያለሁ” ነው ያለው። በነበራቸው የቆረጣ ልምድ ጠላትን ከብበው መጨፍለቃቸውን ነው ወጣቱ የተናገረው።
ቻሌ ዓለምነው የተባሉት አርሶ አደር “አሸባሪው ትህነግ ቀድሞ ወደ ጉና ተራራ እንደሚመጣ መረጃው ስለነበረን ተደራጅተን፣ ምሽግ ቆፍረን ስንጠብቀው ነበር” ብለዋል። በመሆኑም ጠላት ወዳለመበት አካባቢ እንዳይዛመት መደምሰስና መማረክ መቻላቸውን ተናግረዋል።
አሸባሪው ትህነግ በ1983 ዓ.ም በጉና ተራራ ላይ የገጠመውን ሽንፈት ለመበቀል ቢመጣም ራሱ በለኮሰው እሳት ዳግም እንደለበለቡት ነው የነገሩን።
ሌላኛው አርሶ አደር ብናልፈው ታረቀኝ ጠላት “እናንተን አንፈልግም፤ የምንፈልገው መንግሥትን ነው” ብሎ ለማታለል ቢሞክርም የሚታለልለት በማጣቱ ተገቢውን ቅጣት ማግኘት ችሏል ብለዋል።
ሁሉም አካባቢ እንደ እስቴ ወረዳ አርሶ አደሮች ጠላትን መደምሰስ ይጠበቅበታል ነው ያሉት። የቡድኑ ርዝራዦች ዳግም ለመመለስ ቢሞክሩ የተለመደው ሽንፈትና ሞት እንደሚጠብቃቸው አርሶ አደሩ አስጠንቅቀዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ – ከእስቴ ወረዳ ጉና ተራራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m