አሸባሪውን የትህነግ ቡድን እስከመጨረሻው ለማስወገድ መተባበር እንሚገባ በደባርቅ ከተማ የቀድሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ገለጹ።

226

ወጣቱ ለህልውና ዘመቻው የሰጠው ምላሽ የሚደነቅ መሆኑን እና እያደረገ ያለው ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 17/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ትህነግ በ1983 ዓ.ም ወደ ስልጣን እንደመጣ ለሀገር ክብር የማይደራደሩ የቀድሞ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላትን በመበተን መከላከያን ራሱ በሚፈልገው መንገድ ማዋቀሩ ይታወሳል። በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ከፍተኛውን ስልጣን በብዛት በመያዝ የነበረውን የሀገር ፍቅር ስሜት እንዲጠፋ እንዳደረገውም የቀድሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል።

፶ አለቃ አሻግሬ ጌጤ የደባርቅ ከተማ ነዋሪና የቀድሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባል ናቸው። አሸባሪው ትህነግ በጠንካራ የሀገር ስሜት ላይ የተገነባውን የቀድሞ የሀገር መከላከያ ሠራዊት መበተኑ ተገቢ እንዳልነበር አንስተዋል፤ ጠንካራ ብሔራዊ የመከላከያ ኃይል የነበራትን ኢትዮጵያም ክብሯን ሊያዋርድ ጫፍ ደርሶ እንደነበርም ተናግረዋል።

አሸባሪው ትህነግ በስልጣን ዘመኑ በዕውቀት ሳይሆን በእብሪት ሀገር መምራቱን እና የሀገር ፍቅር፣ ወኔና ጀግንነት የነበራቸውን ዜጎችን ይጠላ እና ያሳድድ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

፶ አለቃ አሻግሬ እንዳሉት አሁን ግን የአሸባሪው ትህነግ የእብሪት ገመድ ተበጥሷል፤ እናም የተጀመረው ተጋድሎ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል። እሳቸውም ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ነው የነገሩን፡፡

፻ አለቃ አየነው ታደሰ የቀድሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባል እንደነበሩ እና ሀገራቸውን በዘርፉ በታማኝነትና በጀግንነት ማገልገላቸውን ነግረውናል፡፡
ሽብርተኛው ትህነግ ከጥንስሱ ጀምሮ ሀገር የማፍረስ ዓላማ እንደነበረው ነው ያነሱት፡፡

አስተያየት ሰጪው እንደገለጹት ይህ የሽብር ቡድን በሥልጣን ላይ በነበረባቸው ዓመታት በእብሪት ተወጥሮ አማራንና ኢትዮጵያን አዳክሟል፤ የአሁኑ ትውልድ ይህን መሰሪ የሽብር ቡድን ለማስወገድ የተጀመረውን ትግል ማጠናከር አለበት፤ የሽብር ቡድኑ ፈጽሞ ሊደመሰስ ይገባል ነው ያሉት።

፻ አለቃ አየነው በህልውና ዘመቻው ሁለንተናዊ ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን ነግረውናል፡፡ ለሀገር እድገት ፀር የሆነውን አሸባሪ ቡድን እስከመጨረሻው ለማስወገድ የበለጠ መተባበር ይገባል ብለዋል።

ወጣቶች ሽብርተኛው ትህነግን በመደምሰስ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ እያበረከቱት ያለው አስተዋጽዖ እና ጉልህ ተሳትፎ የሚደነቅ መሆኑን ፻ አለቃ አየነው ገልጸዋል፡፡ ተጠናክሮ መቀጠል አለበትም ብለዋል።

ሌላኛው የቀድሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባል ፶ ጥላሁን ተፈሪ ሽብርተኛው ትህነግ የሀገር ክህደት መገለጫ ባህሪው መሆኑን ነው የጠቀሱት፡፡ ይህንን የሽብር ቡድን ለመደምሰስ መንግሥት ያስተላለፈውን የክተት ጥሪ በመቀበል በህልውና ዘመቻው ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን ነግረውናል፡፡

ትውልዱ በአሁኑ ወቅት ሀገር ለማዳን በአንድነት መነሳት እንዳለበትም ፶ አለቃ ጥላሁን ገልጸዋል።

“የእናት ጡት ነካሾችን ለመዋጋት ዛሬም ዝግጁ ነን” ያሉት ፶ አለቃ ጥላሁን አሸባሪው ትህነግን በጋራ ክንድ መቅበር እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡

ዘጋቢ፡-አዳሙ ሽባባው-ከደባርቅ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article‹‹ጠላት በገባበት ረግረግ ውስጥ ቀብረን እናስቀራለ›› አቶ ዮሐንስ ቧያለው
Next article“ከቀደምት አባቶቻችን የተረከብናትን ሀገር ሉዓላዊነት ለማስቀጠል እንታገላለን” ምልምል ሴት የሠራዊት አባላት