
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 16/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ወጣቱ መከላከያ ሠራዊትን እና ልዩ ኀይሉን በገፍ ተቀላቅሎ ሊያጠናክር እንደሚገባ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል ዮሐንስ ቧያለው ጥሪ አቀረቡ፡፡
አሸባሪው ትህነግ አሁን በለየለት የሽብር ተግባር ቢሰማራም በስልጣን ዘመኑ ጸረ ኢትዮጵያ እና ጸረ አማራ መሆኑ በተግባር የተረጋገጠ መሆኑን አቶ ዮሐንስ ተናግረዋል፡፡
ይህ የባንዳዎች ስብስብ በ1968 ዓ.ም ባረቀቀው ማኒፌስቶ አማራን በጠላትነት ፈርጆ ትግሉን ጀምሯል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎችም የአማራ ሕዝብን አጥቅቷል ብለዋል፡፡ በ1970ዎቹ ዓ.ም በወልቃይት ጠገዴ አማራዎችን በማጥቃት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ወገኖች ቀያቸውን ለቀው እንዲፈናቀሉ፣ ሀብትና ንብረታቸውን እንዲያጡ አድርጓል፤ በቅርቡ ከተፈጸመው የማይካድራ ጭፍጭፋ በፊትም የአማራ ተወላጆችን በተደጋጋሚ በጅምላ ጨፍጭፎ እንደቀበረ አቶ ዮሐንስ ተናግረዋል፡፡
ለዚህ ማረጋገጫ የሚሆኑ በርካታ መረጃዎች በእጃችን አሉ በማለትም ድርጊቱን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚያውቀው አስገንዝበዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ ቀደም ብሎ ለነጻነት፣ ለፍትሕ፣ ለዴሞክራሲ እና ለእኩልነት የሚታገል መስሎ ኢትዮጵያን ተቆጣጥሮ ነበር ነው ያሉት፡፡
ስልጣኑን በያዘ ማግሥት ጀምሮም በከፍተኛ የበቀልና የደመኝነት መንፈስ በአማራ ሕዝብ ላይ የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰት ፈጽሟል፣ ጥፍር ነቅሏል በጅምላ ጨፍጭፏል፣ ግብረ ሶዶማዊነት ፈጽሟል፣ ቶርች አድርጓል፣ ከእንስሳት ጋር አስሮም እንዲሰቃዩ አድርጓል፡፡
የአማራ ሕዝብ በሌሎች ኢትዮጵያውያን እንዲጠላ ለማድረግ ብዙ ጥሯል፤ ከልዩ ልዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንዲፈናቀል፤ ሀብትና ንብረቱ እንዲዘረፍና እንዲወድም አድርጓል፡፡ ውድ ሕይወቱን ከማሳጣቱም በላይ አስከሬኑ በክብር እንኳን እንዳይቀበር ማድረጉ በተለያዩጊዜያት ታይቷል፡፡ሌሎች ኢትዮጵያውያን እሕትና ወንድሞችም የችግሩ ሰለባ እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ የሚያደርሰውን ግፍና በደል የሚቃወሙም በአልሞ ተኳሽ አስገድሏል፡፡
በመላው ኢትዮጵያውያን ትግል ከስልጣን ከተባረረ በኋላ የሀሳብ ትግል ማድረግ ባለመቻሉ እኔ ያልገዘኋት ኢትዮጵያን በማለት ጦርነት አውጆ ወረራ ፈጽሟል፡፡ በዚህም በርካታ ንብረት ዘርፎ ወደ ትግይ ጭኗል፤ የግለሰብ መኖሪያ ቤቶችን፣ መንደሮችን፣ የመንግሥት ተቋማትን እና የሕዝብ መገልገያ መሰረተ ልማቶችን እያወደመ ይገኛል፡፡
አሸባሪው ትህነግ በአስተሳሰብ ደረጃ የኢትዮጵያ ሕዝብ የተፋው ደካማ ስብስብ ነው፡፡ የፖለቲካ እሳቤው ለኢትዮጵያ የማይበጅ ዘረኛ፣ አንዱን ካንዱ ለማጋጨት የሚጥር፣ ዘራፊ፣ ኢዴሞክራሲያዊና ኢሰብዓዊ ተግባር የፈጸመ መሆኑ ገሀድ የወጣ ነው፡፡
በሰላማዊ፣ ሕጋዊና ፖለቲካዊ የሀሳብ ትግል ማሸነፍ በማይችልበት ደረጃ የፖለቲካ አቅሙ ዜሮ መድረሱን አንስተዋል፡፡ የተነጠቀውን ስልጣን በትጥቅ ትግል ለማስመለስ ቢያስብም የኢትዮጵያ ሕዝብ አልተጠበቀውም።
አሁን ላይ በሥነልቦና፣ በፖለቲካ አስተሳሰብ፣ በሎጅስቲክስና በኢኮኖሚ አቅመቢስ መሆኑ የተረጋገጠ ሀቅ ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ ወረራ ፈጽመው ወደ አማራ ክልል የገቡ የጠላት ተላላኪዎች መንገዱ እንደጠፋው ጉንዳን እየተርመሰመሱ ይገኛሉ፡፡ መንግሥትና ሕዝብ ለሰላም ዋጋ በሰጠበት ጊዜ ሳይታሰብ በአንድ ጊዜ ግር ብለው መጥተው እንደ አንበጣ ነው ለመውረር የሞከሩት፡፡
ወረራ የፈጸሙት አቅም ኖሯቸው እንዳልሆነ አቶ ዮሕንስ ተናግረዋል፡፡ አንበጣ ወረራ የሚፈጽመው ከሰው የሚበልጥ አቅም ኖሮት አይደለም በማለትም የትህነግ ወረራ ከአንበጣ መንጋ ወረራ ተለይቶ እንደማይታይ ነው ያነሱት፡፡
ይህ ቡደን እስከቻለ ድረስ ዋንኛ ዓላማው ኢትዮጵያን መግዛትና መበዝበዝ፣ አልሳካ ሲለው ደግሞ ሐገርን ማፍረስ ነው፡፡ በእያንዳንዱ አካባቢ የገቡት የጸጥታ ኀይል በሌለበት መሆኑን በማንሳት የገቡት ግን እንደማይወጡና በቅርብ ጊዜ መደምሰሳቸው እንደማይቀር አረጋግጠዋል፡፡ አሁንም እየቀመሱ ነው ያሉት ብተዋል፡፡
ወደ አማራ ክልል መግባት ብቻ ሳይሆን እየጠለቁ ነው፤ ጠልቀው በገቡ ቁጥር ረግረግ ውስጥ እየገቡ መሆኑ ይታየኛል፡፡ አላማጣና ኮረም ሲገቡ ጉልበታቸው ላይ የነበረው ረግረግ አሁን አንገታቸው ላይ ደርሷል፡፡ እዛው ረግረግ ውስጥ ቀብረን እናስቀራቸዋለን ብለዋል፡፡
በዚህ ጊዜ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻና ፋኖ እንዲሁም ወጣቶች ወረራውን እየመከቱ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ከስንቅ ዝግጅት ጀምሮ የሕለውና ዘመቻውን በተለያየ መልኩ እየደገፉት እደሆነ አንስተዋል፡፡
ምሁራን እና ሀገር ወዳድ የዲያስፖራ አባላት የሚያደርጉት ድጋፍም የሚመሰገን ነው ብለዋል፡፡ ዘመቻው እስኪጠናቀቅ እና ከዚያም በኋላ የተጎዱ ወገኖችን፣ የዘማች ቤተሰቦችን እና የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ በማደራጀት እንቅስቃሴው ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡
ወጣቱም የጦርነቱን ዓላማ በግልጽ ተረድቶ ተዘጋጅቷል ያሉት አቶ ዮሐንስ አሁንም መከላከያ ሠራዊትን እና ልዩ ኀይሉን ተቀላቅሎ ሊያጠናክረው እንደሚገባ አንስተዋል፡፡ የአሸባሪውን የቅዠት ሕልም በማክሰም ሀገር ወደነበረችበት ሰላምና የልማት እንቅስቃሴ ለመመለስ የጀመሩትን እንቅስቃሴ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አሸባሪው ቡድኑ አቅመቢስነቱን ለመሸፈን በውሸት፣ የክህደትና ሕዝብን ረፍት ሊነሱ የሚችሉ ሀሰተኛ መረጃዎችን ይለቅቃል፣ በተለያዩ ሀገራት ያሰማራቸውን ተላላኪዎች ተጠቅሞ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተሳሳተ መረጃ እየሰጠ ነው፡፡ ይህም ከቀድሞ ባሕሪው የወረሰው እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
ወረራ በፈጸመበት አካባቢ ሕዝቡን ለማሳሳት ቢሞክርም ሕዝቡን ማታለል አልቻለም፡፡ ሕዝቡም ትክክለኛውን መረጃ ከታማኝ ምንጮች በመውሰድ የአሸባሪውን ትህነግ ዓላማ ማክሸፉን መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡
በደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m