
አቶ ግዛቸው ያስተላለፉት ዕለታዊ መረጃ ቀጥሎ ቀርቧል።
አሸባሪው ትህነግ የአማራና የአፋር አካባቢዎችን በመውረር ኢትዮጵያን ለመበተን ያስችላል ያለውን ስልት ሁሉ ነድፎ እየሰራ ይገኛል። ይህ አሸባሪ የከሰረውን ከስሮ ሕዝባችንና ሀገራችንን መጉዳቱን እንደ ትርፍ ቆጥሮ የተላላኪነት ተግባሩን ለመወጣት እየተንቀሳቀሰ ነው።
አሸባሪው ቡድን ለእኩይ አላማው በዚህ መጠን ሲንቀሳቀስ የአማራ ክልል ሕዝብና ወዳጆቻችን ጠላትን ለመመከት እና ሀገራችን ከገጠማት ፈተና ለማዳን የማንከፍለው መስዋእትነት የለም። ሁላችንም ያለንበት አካባቢና ሙያ ሁሉ የጦር ግንባር ነው፡፡
እስካሁንም ተስፋ የቆረጠውን ወራሪ ጠላት በገባበት አካባቢ ሁሉ በከፍተኛ ደረጃ ሰብዓዊ ኪሳራ እያጋጠመውና እየተደመሰሰ ይገኛል፡፡ ከግንባር አውደውጊያው ባሻገርም ጠላትን ለመመከትና ለመደምሰስ የግድ ጦር ሜዳ ዘምተን መስዋእትነት እንድንከፍል አይጠበቅብንም። ይልቁንም በየፊናችን የሕልውና ዘመቻው አካል በመሆን የጀመርነውን ሚና አጠናክረን እንወጣለን ።
በዚህም መሰረት ፦
1. የክልላችን ህዝብና የንግዱ ማኅበረሰብ የኢኮኖሚ አሻጥርን በመዋጋት የድል ባለቤት ሊሆን ይገባል!
የኢኮኖሚ አሻጥር አንደኛው የጠላት የውጊያ መስክ ሆኗል። በአሻጥር ኢኮኖሚውን ጤናማ ጉዞ እንዳይኖረው እክል በመፍጠር ሕዝብን ትኩረቱን እንዲቀይር የማድረግ ስራዎች በተጠና መልኩ ለመስራት ጥረቶች ተደርገዋል። በሸቀጣሸጦች ላይ ሕገወጥ የዋጋ ጭማሬ፣ ደብቆ በመከዘን የአቅርቦት እጥረት መፍጠር የመሳሰሉ የአሻጥሩ አካሎች ናቸው።
አብዛኛው የንግዱ ማኅበረሰብ የሕልውና ዘመቻውን በገንዘብና በቁሳቁስ በመደገፍ የአርበኝነት ተግባሩን እየተወጣ ይገኛል። ይሁንና ጠላት በዚህ መስክ አሻጥር በመፈፀም እየሰራበት ነው፡፡ አንዳንድ የንግዱ ማኅበረሰብ አካላትም ያለንበትን ሁኔታ ከልብ ባለመውሰድ ለአሻጥር ተጋላጭ ሆነዋል።
አሸባሪውና ወራሪው ትህነግ በወረራቸው አካባቢዎች ማንንም ሳይለይ ሀብትና ንብረት እየዘረፈና እያወደመ ይገኛል። በመሆኑም በዚህ ወቅት ጀግኖች የሕይወት መስዋእትነት ለመክፈል ሲዘጋጁ እኛም ያልተገባ ትርፍን ባለመፈለግ፣ ከመጠን በላይ ዋጋ የሚጨምሩና አቅርቦት የሚደብቁ ካሉ በማጋለጥ ሕዝባችን በኑሮ ውድነት እንዳይጠቃ በመስካችን የበኩላችንን አርበኝነት መወጣት አለብን።
ሕዝባችን በኑሮ ውድነት ሳይማረር ዋና ትኩረቱን የሕልውና ዘመቻው ላይ እንዲያደርግ የሕልውና ዘመቻውን በገንዘብና በዓይነት ከመደገፍ በተጨማሪ የንግዱ ማኅበረሰብ በራሱ መስክ ድል ለመቀዳጀት ወቅቱን የሚመጥን መስዋእትነት በመክፈል ይኖርበታል።
ለመሰል ጠላት የሚጠቅም አሻጥርን በንግዱ ዘርፍ በማስወገድና በመታገል የሕልውና ዘመቻውን ስንቀላቀል በግል ለራሳችን፣ ለሀገራችንና ለሕዝባችን አርበኝነት እየፈፀምን እንደሆነ፣ በጦር ግንባር ባይሆንም በመስካችን ዘምተን ድል እንደተቀዳጀን መገንዘብ ይገባናል።
2. በውጭ አገራት የምትገኙ ወገኖቻችን በውጭ ምንዛሬ የጥቁር ገበያ አሻጥርን በመዋጋት ድላችሁን አጠናከራችሁ ቀጥሉ፡፡
የዲያስፖራ ወገኖቻችን አገር በታኙን ታሪካዊ ጠላት ለመደምሰስ በተጀመረው ትግል አኩሪ ደጀንነቱን እያሳየ ነው፡፡ ከፍተኛ የገንዘብ መዋጮ ያደርጋል፣ ተፈናቃዮችን ያቋቁማል፣ የጠላትን ሐሰተኛ መረጃ ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ እንዲገነዘበው ይሠራል፡፡ ከመቼውም ጊዜ በተለየ እያሳየው ያለው ያገባኛል ባይነት እና እየፈጠራቸው ያሉ የመሰባሰብና መደራጀት ስራዎች የሰፊው ዲያስፖራ ደጀናችን ሚና እንዲጨምር ያደረገ ነው፡፡ ከጦር ግንባር ሰልፍ ያልተናነሰ ሚና ጀምሯል፣ ሊያጠናክረው ይገባል፡፡
በተለይም በውጭ የሚኖሩ ወገኖች በግል ለቤተሰብና ወዳጅ ዘመድ ወደ ሀገር ቤት ገንዘብ ይልካሉ። ብዙዎች ተቀባዮች በጥቁር ገበያ የምትገኘውን ትርፍ ለማግኘት ምንዛሬውን በባንክ የማይፈፅሙበት ሁኔታ ሰፊ ነው።
የጥቁር ገበያ ደግሞ በዚህ ወቅት የጠላት መጠቀሚያ በመሆን ላይ ይገኛል። ጠላት በዘረጋው የቀጥታ እና ተዘዋዋሪ የሰርጎ ገብ መረቡ የከፈተው የኢኮኖሚ ጦርነት ረጅም ጊዜ የቆየ ቢሆንም አሁን ተጠናክሮ መጥቷል፡፡ የውጭ ምንዛሬን ዋጋ በማሻቀብ ሕዝብንና ሀገርን ከኋላ ለመውጋት ይሠራበታል።
በመሆኑም በውጭ የምትገኙ ወገኖች በቀጥታም ሆነ ተዘዋዋሪ የእነዚህ ጠላቶች ተባባሪ ላለመሆን፣ ወቅቱም የትርፍ ፍላጎት የምናሳይበት ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ ላይ መሆናችንን በመገንዘብ ገንዘባችሁን በአገራችን ባንኮች በመላክ እንድትታገሉ እንጠይቃለን።
3. የአማራ ምሁር የእውቀት እና የጠላትን ትርክቶች ትግል አጠናክሮ የድል ባለቤትነቱን አጠናክሮ ይቀጥል፡፡
ከውስጥ እስከ ውጭ አገር ያለው የአማራ ምሁር በወቅቱ የዘመቻ ትግል አኩሪ ተሳትፎ እያደረገ ነው፡፡ ዛሬ ከአማራ አርሶአደርና ወጣት ጋር ስለህልውናው ሲመክርና ሲያደራጅ የሚውል የህልውና ዘማች ምሁር ታድለናል፡፡ የክልላችሁ ህዝብና መንግስት ይኮራባችኋል፡፡
ትህነግ በዋነኛነት “ልሂቃን” እያለ በዋና ጠላትነት የፈረጃው አንድም የአማራን ምሁራን ነው፡፡ ከትናንት እስከዛሬ አማራን ሰው አልባ ለማድረግ ምሁር ተኮር ጥቃትን ሳያሰልስ ሲፈፅም የኖረ ነው፡፡ ዛሬም ይሔው የአሸባሪው ትህነግ ጠላት ቡድን የአማራን ልሒቅ በመፍጀት ዳግም እንዳይነሳ አደርጋለሁ የሚል የቆየ ደመኛነቱን በአደባባይ አውጇል፡፡ ይህንን ክፋት ለመመከት የእውቀትና የመፍትሔ ሃሳብ ትጥቅ በስፋት የሚያስፈልግበት ወቅት ነውና ትግላችሁ ይጠናከር፡፡
አሸባሪው ጠላት ቡድን ሀገር የማፍረስ አላማውን በሁሉም የማጥቂያ ግንባር እያከናወነ ቀጥሏል፡፡ ምሁራችን ይሔንን የሚመክት አንዱ ዘማች ነው፡፡
የሀሰት ፕሮፖጋንዳ በሚያሰራጩ ደጋፊዎቹ በኩል የሀገራችን እውነታዎች ለዓለምአፍ ማህበረሰብ አዛብቶ ማቅረብ አንድ የጦርነት ግንባር ካደረገው ውሎ አድሯል። ለዘመናት በህዝባችን ላይ የተሠራ አሉታዊ ገፅታ ዘመቻ አካል ነው፡፡ ይህንን በመመከት ረገድ ምሁራኖቻችን የምትወጡት ሚና ከፍ ያለ ነው፡፡ በየመስኩ እና በተለያዩ አገርአቀፍና ዓለምአቀፍ ተቋማት የምትገኙ ምሁራን የአማራ ክልልን ሕዝብ እና የሀገራችንን እውነታ በማሳወቅና የትህነግን የሀሰት ፕሮፖጋንዳ በማጋለጥ የድል ድርሻችሁን አጠናክራችሁ ቀጥሉ እንላለን።
4. የዲጅታል እና ማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች የጋራ ድላችንን ለመጨበጥ ትግላችሁን አጠናክራችሁ እንድትሰለፉ ያስፈልጋል፡፡
ወትሮም ጠላት የሆነውን ትሕነግ አስተሳሰብ እና ተግባር በመዋጋት ረገድ የክልላችን አንቂዎች እና የአማራ ወዳጆች የዲጅታል እና ማህበራዊ ሚድያ ትግል ከፍተኛውን ድርሻ የያዘ ነው፡፡
በዚህ የሕልውና ዘመቻን እያካሔድ ልዩነትን ወደጎን በመተው በአንድ ዕዝ እየተንቀሳቀስን እንገኛለን። ከትናንት በቀጠለው የጠላት የጦርነት ጊዜም የጠላትን የሀሰት ፕሮፖጋንዳ በማጋለጥ ፣ የሰከኑ በሳል ትንታኔዎችን በማቅረብ፣ እለታዊ መረጃን በማስተላለፍ ፣ ለወገን ኃይል የሞራልና ስነልቦና ድጋፍ በመስጠት የላቀ ሚና የሚወጣው በርካታ ነው፡፡ በሕልውና ዘመቻው ወቅት የማሕበራዊ ሚዲያ በተለይ የቲውተር ተጠቃሚዎች እጅግ ገንቢ የሆነ ሚና እየተወጡ ይገኛል።
በሌላ በኩል ግን ጠላት የማሕበራዊ ሚዲያን የሐሰተኛና አሳሳች አጀንዳ መድረክ በማድረግ “ዲጅታል ሠርጎ ገቦችን” አሠማርቶ በውስጣችን የልዩነት አጀንዳ መስበኪያ አድርጎ ከጉዳያችን እያስወጣ ሲያነታርከንና ሲጠቀም ቆይቷል።
በእኛ ወገንም በፌስቡክና መሰል የማሕበራዊ ትስስር ገፆች ወቅቱንና ሁኔታዎችን ከግምት ያላስገቡና ሁኔታዎችን የማይመጥኑ፣ ልዩነትን የሚያሰፉ፣ ከጋራ ጠላት ትግል አጀንዳ የሚያወጡ፣ ህገወጥነትንና የደቦ ፍርድን የሚያበረታቱ፣ በትክከለኛ መረጃ ላይ ያልተመረኮዙ ተገቢ ያልሆኑ ዘመቻ ተኮር መረጃዎች እና አንዳንድ ወገኖችን የሚረብሹ ጥርጣሬ መፍጠርን ዓላማ ያደረጉ አሉታዊ መረጃዎች የሚሰራጩበት ሁኔታ ተስተውሏል፡፡ ይሔ ለጠላት ጥይት እንደማቀበል የሚቆጠር ሚና በመሆኑ የዲጅታል እና የማሕበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ወገኖቻችን ማስተካከያዎችን በማድረግ በጠላት ላይ እንደሚሠሩ እናምናለን፡፡
ከዚህ የሕልውና ዘመቻ በላይ በአንድ የሚያሰልፈን ጉዳይ የለም፡፡ እናም የዲጅታል እና ማህበራዊ ሚድያ ፀሐፊዎችና አዘጋጆች የጠላትን ሐሰተኛ መረጃና ፕሮፖጋንዳ በማጋለጥ፣ በውጭ አካላትና የገዛቸው ደጋፊዎች በኩል የሚያሰራጨውን የተሳሳተ ትርክት በመመከት፣ በህዝባችን ላይ የሚፈፅመውን ሰብዓዊ ግፍ እና በአገር ህልውና ላይ የደቀነውን አደጋ ለአገር ውስጥና የውጭ አካላት በማጋለጥ ላይ በማተኮር የድሉ አካል እንድትሆኑ ጥሪ እናቀርባለን።
5. መላው ህዝባችን ለጦር ግንባር ዘማች አርሶአደር የምናደርገውን የግብርና ስራ ድጋፍ እጠናክረን እንቀጥል፡፡
ሚሊሻዎቻችን አሸባሪውን ለመፋለም ዘምተዋል። ሌሎች ወጣቶችም ከግል ስራቸው ሕዝብና ሀገር ይበልጥብናል ብለው ዘምተዋል። እነዚህ ጀግኖች ለህልውናችን አውደ ውጊያ ሲውሉ ወቅቱ የሚጠይቀውን የእርሻ ስራ በመስራት የተጀመረውን ድጋፍ አጠናክረን መቀጠል ይገባል፡፡ በዘር ወቅት ያሳየነውን ድጋፍ በአረም ስራና በቀሪ የሰብል ልማት ተግባራት መድገም ይገባናል፡፡ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሰማራት የሚሊሻዎቻችንን ማሳ መንከባከብ ጦርነቱን በቀጥታ ከመደሳተፍ ተለይቶ የማይታይ ወሳኝ ስራችን በመሆኑ በትኩረት ልናከናውነው ይገባል።
6. መላው የአገራችን እና የክልላችን ሕዝብ ተፈናቃዮችን መደገፍና ማቋቋም ላይ እንረባረብ
አሸባሪው ትህነግ “ሂሳብ አወራርዳለሁ” ብሎ በፈፀመው ወረራ ብዙ ውድመቶችን አድርሷል። ንፁሃንን ጨፍጭፏል። ሀብት ንብረት አሸሽቷል። አውድሟል። ከምንም በላይ በመቶሺህዎች የሚቆጠረውን ህዝባችንን ከቀየው አፈናቅሏል፣ መኖሪያ መንደሮችን እና ቤቶችን በእሳት እያቃጠለም ይገኛል፡፡ ጠላት ይህንንም የጦርነቱ አካል አድርጎ እየሠራበት ይገኛል ፡፡ በዚህ የሚፈታ ትግል አልጀመርንም እና ወገኖቻችንን በመደገፍ ድላችንን እናስፋ፡፡
በመሆኑም የፌደራልና የክልል ተቋማት፣ የሰብአዊ መብት ተቋማትና ተቆርቋሪ ግለሰቦች፣ ሚዲያዎቻችን፣ ማህበረሰብ አንቂዎች፣ ወዘተ ተፈናቃይ ወገኖቻችንን ለመደገፍ እያደረጉት ያለው ድጋፍ የሚበረታታ ቢሆንም የችግሩን መጠን የሚመጥን አይደልም፡፡ ስለሆነም የትህነግን ውድመት ለሕዝባችንና ለዓለም ከማሳወቅ በተጓዳኝ ተጎጂዎችን በማቋቋምና በማገዝ የሕልውና ዘመቻውን እንድትደግፉ ጥሪያችን እናቀርባለን።
7. የጠላት ሠርጎ ገብንና ተላላኪዎችን ለማጋለጥ ከምንግዜውም የተለየ ትኩረት ሰጥተን እንሰለፍ፡፡ አሸባሪው ኃይል በሰርጎ ገብ በኩል ሕዝባችንን ለማሸበር ብዙ ጥረት አድርጓል። በዚህ ረገድ ወጣቶች አካባቢያቸውን በመጠበቅ እያደረጉት ያለው አስተዋፅኦ የሚደነቅ ነው። የአሸባሪው ሰርጎ ገብ ስልቱን እየቀያየረ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በመለየት ሕዝባቸውን ከጥቃት ሲከላከሉ፣ ይህን ስራቸውን ከፀጥታ ኃይል ጋር በመተባበርና፣ ፀጉረ ልውጥ ሲያገኙም ለፀጥታ ኃይል በመጠቆም ወይንም ይዞ በመስጠት ልንስራ ይገባል። በሌላ መንገድ ጠላት የራስን ወገን ጨምሮ መተማመን እንዳይኖርና ትርምስ ለመፍጠር ፣ የደቦ ፍርድን ለማንገስ ፍላጎት ያለው መሆኑን በመገንዘብ በጥንቃቄ፣ ብልሀት በተሞላበትና በንቃት እንድንሠራ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
በመጨረሻም የአውደ ዉጊያ ውሎአችን በሁሉም ግንባሮች በጥሩ ሁኔታ እየቀጠሉ ሲሆን በትናንሽ ድሎች ሳንኩራራ ግባችንን እያሰብን ጉዟችን ሁሉ ወደፊት ይሁን!!!
ድል ለፍትህና ለነፃነት ታጋይ ጀግኖቻችን!!!