
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 16/2013 ዓ.ም (አሚኮ) “ከመከላከያ እና ከሕዝባዊ ኃይል ጎን በመቆም የድርሻዬን እወጣለሁ” በሚል መሪ ቃል በለንደን የበይነ መረብ ሰልፍ ተካሂዷል፡፡
የ“ዲፌንድ ኢትዮጵያ” ዩናይትድ ኪንግደም ግብረኃይል በለንደን ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር በተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ሰልፍ ላይ ከዩናይትድ ኪንግደም፣ ከአውሮፓ፣ ከሰሜን አሜሪካና ከአፍሪካ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተሳትፈዋል፡፡
በበይነ መረብ ሰልፉ ላይ በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ በኢትዮጵያ በሽብርተኛው ትህነግ እና በኦነግ ሸኔ ሀገርን የማፍረስ ጦርነት መከፈቱን አብራርተዋል፡፡

አምባሳደር ተፈሪ ምዕራባውያን የሽብርተኛው ትህነግን እድሜ ለማራዘም እየጣሩ መሆናቸውን እና መንግሥትና ሕዝብ ጫናውን በመቋቋም ኢትዮጵያን ከመፍረስ አደጋ ለመታደግ ከፍተኛ ትግል እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ሕዝብና መንግሥት ሀገርን ከጥፋት ቡድኖች ለመታደግ በአንድነት በተነሱበት በዚህ ወቅት በውጪ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲ፣ በገንዘብ በመደገፍ፣ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማምከን እና እውነተኛውን መረጃ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የማስረዳት ኀላፊነት አለባቸው ብለዋል፡፡
በመጪው ሳምንት በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ታላቅ የሆነ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት መሰናዳቱን አምባሳደር ተፈሪ አስታውቀዋል፡፡ በዩናይትድ ኪንግደም እና ሰሜን አየርላንድ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በዝግጅቱ ላይ እንዲገኙም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት “ኢትዮጵያን እናድን” በሚል መሪ ቃል ለንደን ላይ የተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ሰልፍ በሀገር ቤት እየተካሄደ ላለው ሕዝባዊ ሀገርን የማዳን ንቅናቄ ከፍተኛ እገዛ አለው ብለዋል፡፡ ለህልውና ዘመቻው 3 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ወር ባልሞላ ጊዜ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡

ዳያስፖራው በመጀመሪያው ዙር የድጋፍ ጥሪ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉንና ባለፈው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ በድጋሜ በቀረበው ጥሪ ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡ ወይዘሮ ሰላማዊት ዳያስፖራው እያካሄደ ያለውን የሕዝብ ለሕዝብ እና የዲጂታል ዲፕሎማሲ ዘመቻ ግለቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተመሳሳይ ገንዘብ በሕጋዊ መንገድ መላክ ለሀገር አስተዋጽኦው ከፍተኛ በመሆኑ ዳያስፖራው በዚህም ለሀገሩ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲገልጽ አሳስበዋል፡፡
ከሰሜን አሜሪካ የተሳተፉት አቶ ነአምን ዘለቀ አሸባሪው ትህነግ ከኦነግ ሸኔ ጋር በመተባበር በጀመረው ሀገርን የማፍረስ ጦርነት በአማራና በአፋር ክልሎች የበርካታ ዜጎችን ሕይወት ማጥፋቱንና ንብረት ማውደሙን ገልጸዋል፡፡ በሌሎች አካባቢዎች ተመሳሳይ ጥፋት እንዳያደርሱ እና ሀገርን እንዳያፈርሱ መከላከል የሚቻለው በአንድነት በመቆም መሆኑን አንስተዋል፡፡ በውጪ ሀገራት የሚኖር ሁሉም ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ከምንጊዜውም በላይ ስለሀገሩ በአንድነት የሚነሳበት ጊዜ ነው ብለዋል፡፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊቱን በገንዘብ፣ በሞራል፣ በፖለቲካ እና በዲፕሎማሲ በመደገፍ የተጋረጠውን ፈታኝ ሁኔታ መወጣት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
ሌላው ተሳታፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ዳያስፖራው በሀገር ቤት በአንድነት የተነሳውን ሕዝብ የሚከፋፍሉ የውጪ እና የሀገር ውስጥ ጠላቶችን በመዋጋት የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ጠይቀዋል፡፡ “የሽብርተኛውን ትህነግ ቡድን መሰሪ ማንነት ማንም አይስተውም” ያሉት አቶ አንዳርጋቸው ሽብርተኛው ትህነግ ከድህነት ወጥቶ ወደ ብልጽግና ሊያመራ የሚችለውን ሕዝብ ወደ ጨለማ ሳይመራው ሊደመሰስ ይገባል ብለዋል፡፡
የ“ዲፌንድ ኢትዮጵያ” ዩናይትድ ኪንግደም ግብረኃይል አስተባባሪ አቶ ዘላለም ተሰማ እንደተናገሩት የመከላከያ ሠራዊትን ስምና ዝና ለማጉደፍ የምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎች የከፈቱትን ዘመቻ የመመከት ኀላፊነት መወጣት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
“ኢትዮጵያዊነት ጠፋ ሲባል የሚለመልም ማንነት ነው” ያሉት አቶ ዘላለም ሽብርተኛው ትህነግ እና ኦነግ ሸኔ በጥምረት የከፈቱት ሀገርን የማፍረስ ሴራ ፈጽሞ ሊሳካ አይችልም ብለዋል፡፡ ተሳታፊዎቹ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በቋሚነት ለመደገፍ እንዲቻል በየወሩ ከባንካቸው ክፍያ የሚያከናወንበትን አሠራር እንዲዘረጋ ጠይቀዋል፡፡
ምንጭ፡- በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ