ለአማራ ሕዝብ ማንነት የአርበኞቹ ተጋድሎ!

275

ለአማራ ሕዝብ ማንነት የአርበኞቹ ተጋድሎ!

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 16/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አርበኛ ወርቄ መለሰ ተወልደው ያደጉት ቃብቲያ አካባቢ ቢሆንም ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በአሸባሪው ቡድን ምክንያት ሃብት እና ንብረታቸውን፤ እርሻ እና መሬታቸውን፤ ትዳራቸውን ትተው በጫካ አሳልፈዋል፡፡

አሸባሪው ቡድን በኀይል ወሯቸው በነበሩት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ አካባቢ ቀደም ሲል በዋናነት እርሻ አልፎ አልፎም እስከ ሱዳን ድረስ የሚዘልቅ ንግድ መተዳደሪያቸው ነበር፡፡

የተራበን ማብላት፣ የተጠማን ማጠጣት፣ የታረዘን ማልበስ እና የደከመን ማሳረፍ የአማራ ሕዝብ እሴቱ ነው።

ይሁንና በ1980ዎቹ ዓ.ም አካባቢውን የወረረው አሸባሪው ትህነግ የአካባቢውን ባለሃብት እና ባለእርስት ማሳደድ ጀመረ።

የአሸባሪው ቡድን አባላት ከዚያም አልፈው የቻሉትን በህቡዕ ያልቻሉትን በአደባባይ መግደል፣ አማራ ነኝ ያለን ለመቀጣጫ ማቅረብ እና ሰውን ያክል ፍጡር እስከ ነፍሱ መቅበር ጀመሩ፡፡

ወልቃይቴዎች በአሸባሪው ቡድን ወልቃይቴ ሆኖ መሳሪያ መያዝ አይቻልም የሚል አዋጅ ሲታወጅባቸው ቤት እና ንብረታቸውን፤ ልጅና ሚስታቸውን ትተው ከወንድሞቻቸው ጋር ጫካ ገቡ።

በወቅቱ የአማራ ማንነትህን ቀይርና ትግሬነትን ተቀበል የተባሉት አርበኛ ወርቄም “ሞት ይሻላል” ብለው ከማንነት ይልቅ ስም መቀየር ይበጃል በሚል ለደኅንነታቸው ሲባል “ሽፈራው ተካ” እስከመባል ደረሱ፡፡ ከታላቅ ወንድማቸው እና አብሮአደግ ጓደኞቻቸው ጋር ወደ ጫካ የገቡት እነአርበኛ ወርቄ መለሰ ዝም ብለው አልሸሹም ነበር፤ በጥባጭ ናቸው ካሏቸው የአሸባሪው ህወሓት ታጋዮች መካከል ሦስቱን እስከወዲያኛው ሸኝተው መሳሪያቸውን አንስተው ዱር ቤቴ አሉ፡፡

እነአርበኛ ወርቄን እና ወንድሞቻቸውን አድኖ መያዝ ያቃተው የአሸባሪው
የህወሓት ቡድን እናታቸውን ለሁለት ዓመታት ጨለማ ቤት ውስጥ አሰሯቸው፡፡

“የአርበኛ ወርቄ ልጆች ተበተኑ” የሚሉት የአቶ ወርቄ የትግል አጋር እና አብሮ አደግ ጓደኛ አቶ ቻሉ ኑርየ ታላቅ ወንድማቸውን ደግሞ ፊት ለፊት ገጥሞ ሲታኮስ ማይካድራ አካባቢ ገደሉባቸው ይሉናል፡፡

እነአርበኛ ወርቄ ትግሉን ላያቆሙ ጀምረዋልና ምንም ቢፈጠር ወደኋላ እንደማይሉ ተማምለዋል፡፡ አርበኞቹ ከቀን ቀን ከአንዱ ጫካ ወደ ሌላው ጫካ፤ ከአንዱ ተራራ ወደ ሌላው ተራራ እየተሸጋገሩ የህወሓትን ቡድን በግልፅም በስውርም ሲለበልቧቸው በቀል መስሏቸው 15 ቤተሰቦቻቸውን ገደሉባቸው፡፡ ይህ የአሸባሪው ህወሓት የበቀል እርምጃ እነአርበኛ ወርቄን ቢፈትናቸውም እንደብረት አጠነከራቸው እንጅ አልበተናቸውም፡፡

ህወሓቶችን በተሰባሰቡበት እንደነብር እያጓሩ ገብተው በታትነዋቸው ሲወጡ እና በየጥሻው እየጠበቁ በዚያው ሲያስቀሯቸው የአሸባሪው ህወሓት ቡድን አባላት ተማረው ለመልቀቅ እስኪወስኑ ድረስ ፈተና ሆኑባቸው ነበር፡፡

“ሀገር ክትክታም እምቧጮም ያበቅላል” የሚሉት አርበኛ ወርቄ ለህወሓት ያደሩ ጥቂት ባንዳዎች መውጫ መግቢያቸውን እየተከታተሉ መረጃ በማድረስ ጉዳት እንዲደርስባቸው አደረጉ፡፡ ጓደኞቻቸው ተገደሉ እርሳቸውም ሁለት ጊዜ ቆሰሉ፡፡ ጫናው ሲበረታ እና ብቻቸውን ሲቀሩ አካባቢውን ለቀው ከኤርትራ እስከ ቋራ፣ ከሱዳን እስከ ማኅበረ ስላሴ፣ ከማንኩሽ እስከ ወለጋ ከቦታ ቦታ ራሳቸውን እየቀያየሩ መኖር ግድ አላቸው፡፡

“በየሄድኩበት ሁሉ እነርሱ አሉ” የሚሉት አርበኛ ወርቄ ያሉበት ታውቆ ቢያዙ የሚያደርሱባቸውን ስለሚያውቁ ቶሎ ቶሎ ቦታ መቀያየር ግድ ሆኖባቸውም ነበር፡፡

በመጨረሻም ቋራ ውስጥ ገብተው ትግላቸውን በአዲስ መንገድ ጀመሩ፡፡ የእኛ የአርበኝነት ትግል ከጊዜ ወደ ጊዜ በአሸባሪው ቡድን ላይ የነቃ ማሕበረሰብ እንዲፈጠር አድርጓል የሚሉት አርበኛ ወርቄ ከዚህ በኋላ አሸባረው የህወሓት ቡድን የወልቃይትን ምድር እንደማይረግጠው ገልጸዋል።

ሌላው የትግል አጋር እና ጓደኛ አዛናው ውብነህ አርበኛ ወርቄ ልጆቻቸውን ለ30 ዓመታት ጥለው መሰደዳቸውን ተናግረዋል። አዲሱ ትውልድም የተከፈለውን መስዋእትነት በሚገባ ተረድቶ ማንነቱን በተደራጀ መንግድ ሊጠብቅ ይገባል ብለዋል፡፡

አርበኛ ወርቄ መለሰ “ከፋኝ” ብለው ጫካ ሲገቡ በትነዋቸው ከሄዷቸው ልጆቻቸው መካከል እስካሁን ያላገኟቸው አሉ የሚሉት የአርበኛ ወርቄ የትግል አጋር እና አብሮ አደግ ጓደኛ አቶ አዛናው ውብነህ ለማንነት እና ለነፃነት መከበር የተከፈለ ውድ መስዋእትነት በመሆኑ እንኮራበታለን ብለዋል፡፡

ሁሉም አማራ ለማንነቱ እና ሲል መደራጀት የሚገባው ወቅት ላይ ነው የሚሉት አርበኛ ወርቄ እርሳቸውም ትግሉን በቃኝ ሳይሉ የአማራ ሕዝብ ሕልውና በአስተማማኝ ደረጃ እስኪረጋገጥ ድረስ ለመታገል ዝግጁ መሆናቸውን አጫውተውናል፡፡

“አሸባሪዎቹ ህወሓቶች ለአማራ ሕዝብ መርፌ ሆነው ገብተው ማረሻ ሆኑበት ነበር” የሚሉት አርበኛ ወርቄ መለሰ ከዚህ በኋላ ለአፍታ እንኳን በማንነቱ እና በእርስቱ የሚዘናጋ ትውልድ ቢፈጠር የሚጠይቀው መስዋእትነት መራር መሆኑን ማስረዳት ተገቢ ነው ይላሉ፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው -ከሁመራ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleወንጀል ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በሕግ አግባብ እንዲጠየቁ በማድረግ ማኅበረሰቡ እየፈጸመ ያለውን ተግባር አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።
Next article“ምዕራባውያን የአሸባሪውን ትህነግ እድሜ ለማራዘም እየጣሩ ነው፣ መንግሥትና ሕዝብም ጫናውን በመቋቋም ኢትዮጵያን ከመፍረስ አደጋ ለመታደግ ከፍተኛ ትግል እያደረጉ ናቸው” በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ