ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በሕግ አግባብ እንዲጠየቁ በማድረግ ማኅበረሰቡ እየፈጸመ ያለውን ተግባር አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።

305

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 15/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

ኮሚሽነሩ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ወጣቶች ከመከላከያ እና ከክልሉ የጸጥታ ኀይል ጋር በመቀናጀትና ጠላትን ፊት ለፊት በመጋፈጥ እየፈጸሙት ያለው ጀብዱ የሚያኮራ ነው፡፡ በዚህም ድል እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ማኅበረሰቡም ስንቅ በማዘጋጀት እና በማቅረብ፣ ደም በመለገስ፣ የተፈናቀሉ ወገኖችን በመርዳት እና በማቋቋም እና ሰርጎ ገቦችን ለሕግ በማቅረብ ከፍተኛ ጀብድ እየፈጸመ እንጀሚገኝ ተናግረዋል፡፡

አካባቢውን በመጠበቅ፣ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ የሚነዙ አካላትን በመዋጋት እና ሕገወጥነትን በመከላከል በኩል ኅብረተሰቡ እያከናወነ ያለውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ነው የጠየቁት፡፡

ይሁን እንጅ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ የሚፈጸሙ ሕገወጥ ድርጊቶች ሊቆሙ እንደሚገባ ነው ኮሚሽነር ተኮላ ያሳሰቡት፡፡

ማንኛውም ‹‹ወንጀል ፈጽሟል›› ተብሎ የተጠረጠረ ግለሰብ በሕግ አግባብ መዳኘት ሲገባው አንዳንድ አካላት በግለሰቦች ላይ እርምጃ መውሰዳቸው ሕገወጥ ድርጊት መሆኑን አንስተዋል፡፡

ግለሰቦች የተጠረጠሩ አካላትን በሕግ እንዲያዙ የመጠቆም፣ የማጋለጥ እና የሚያውቁትን ቀርበው ከመመስከር ውጭ ጉዳዩ በሕግ አግባብ ሳይጣራ የደቦ ፍርድ መስጠት ወንጀል ነው ብለዋል፡፡

ድርጊቱን የፈጸሙ አካላትም በሕግ እንዲጠየቁ እንደሚደረግ አንስተዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ማኅበረሰቡ ሊተባበር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article❝ጠላት መውጫ ስለሌለው በየአካባቢው መበተኑ አይቀርም፤ በዚህ ጊዜ እያንዳንዱ የአማራ መሬት እሾህ ሆኖ ሊጠብቀው ይገባል❞ አቶ ዮሐንስ ቧያለው ቧያለው
Next articleለአማራ ሕዝብ ማንነት የአርበኞቹ ተጋድሎ!