
ባሕር ዳር፡ መስከረም 16/2012 ዓ/ም (አብመድ) ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽን ኢትዮጵያዊውን የሩጫ አሰልጣኝ ወልደመስቀል ኮስትሬን (ዶክተር) በምርጥ አሰልጣኝነት መረጠ፡፡
የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማኅበር ትናንት መስከረም 15 ቀን 2012 ዓ.ም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰባት የአትሌቲክስ አሰልጣኞችን ‹‹የዓለማችን ምርጥ የአትሌቲክስ አሰልጣኝ›› በማለት ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ ከሰባቱ መካከል ኢትዮጵያዊው አሰልጣኝ ወልደመስቀል ኮስትሬ (ዶክተር) ብቸኛው አፍሪካዊ ተመራጭ ሆነዋል፡፡
ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ ኃይሌ ገብረስላሴን፣ ደራርቱ ቱሉን፣ ብርሃኔ አደሬ፣ ቀነኒሳ በቀለን፣ ገብረእግዚያብሔር ገብረማርያም፣ ስለሽ ስህንን፣ ጥሩነሽ ዲባባን፣ መሠረት ደፋርን እና ሌሎች ስኬታማ እና ታዋቂ አትሌቶችን አሰልጥነዋል፡፡ አትሌቶቹም በተሳተፉባቸው ውድድሮች ባለድል ሆነው ሀገራቸውን አስጠርተዋል፡፡
በተያያዘ ዜና በ2019 (እ.አ.አ) የዓለም አትሌቲክስ ሻምፕዮና ላይ የሚሳተፉት ሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ሌሊት 8፡30 ዶሃ ኳታር ገብተዋል፡፡ ከዛሬ ምሽት ጀምሮ በተለያዩ ርቀቶች በፍጻሜና በማጣሪያ ውድድሮች የሚሳተፉ ይሆናል፡፡
ምንጭ፡- የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን
በደጀኔ በቀለ