
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 15/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ጠላትን ለመደምሰስ የተጀመረው ትግል ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የብልጽግና ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ዮሐንስ ቧያለው ገልጸዋል፡፡ በሕልውና ዘመቻው ሕዝቡ እያደረገ ያለው ርብርብ የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል፤ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአማራ ሕዝብ ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ውስጣዊና ውጫዊ ጠላቶችን አደብ የማስገዛት እና የሚፈጽሙትን ትንኮሳ የመቀልበስ ደማቅ ታሪክ አለው፤ የሚታገለው ለፍትሕ፣ ለነጻነት እና ለክብሩ እንጂ ሌሎችን በመውረር ትርፍ ለማግኘት አይደለም፤ በታሪኩም ተሸንፎ አያውቅም ብለዋል፡፡
የአማራ ሕዝብ በትግራይ ክልል ጣልቃ የገባበት የታሪክ አጋጣሚ የለም፤ አሸባሪው ትህነግ ግን በ1982 እና 1983 በፈጸመው ወረራ በየመንደሩ ገብቶ ንብረት በመዝረፍ ወደ ትግራይ ጭኗል፤ በስልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታትም ተነግረው የማያልቁ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ በደል አድርሷል፤ ይህም ሳያንሰው አሁን ሂሳብ አወራርዳለሁ ብሎ በግልጽ በመዛት ወረራ ፈጽሟል፤ ሕዝባዊ ማዕበል በመፍጠርም ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ገብቷል፤ የአማራን ሕዝብ ሕልውና በማጥፋት ኢትዮጵያን ለመበተን ነው እየሠራ ያለው፡፡ በገባባቸው አካባቢዎችም ዝርፊያ፣ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ የንብረት ውድመትና ሌሎች የጦር ወንጀሎችን ፈጽሟል ነው ያሉት፡፡
መከላከያ ሠራዊት፣ ከየክልሎች የተውጣጡ የልዩ ኀይል አባላት፣ የአማራ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ፣ ፋኖ እና ወጣቱ በቅንጅት ወረራውን እየመከቱ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም ከፍተኛ ሀብት በማሰባሰብ እየተረባረበ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
አቶ ዮሐንስ እንዳሉት የአማራ ሕዝብ አሸባሪውን ትህነግ ለመደምሰስ በአንድነትና በመተሳሰብ ተነስቷል፤ ባለሀብቶች፣ ምሁራንና ዲያስፖራዎች ሁለንተናዊ ድጋፍ እያደረጉ ነው፤ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመሳሳይ አቋም ወስደው የሥራ ክፍፍል አድርገዋል፤ ወጣቶች በገፍ ወደ ግንባር እየተመሙ ይገኛሉ፤ በርካታ ወጣቶች በመከላከያ ታግዘው ሀገራቸውን ለመታደግ ወስነዋል ብለዋል፡፡ ሕዝቡም አካባቢውን በንቃት እየተከታተለ ግንባር የሚገኘውን የወገን ኀይል እያበረታታ ነው የሚገኘው፤ ይህም አሸባሪው ቡድን የኢትዮጵያውያን ጠላት ለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
❝በተለመደው ታሪካችን አሁንም ለክብራችን እናሸንፋለን❞ ያሉት አቶ ዮሐንስ የገባ ጠላት ተመልሶ መውጣት እንደማይችል ገልጸዋል፡፡ አሸባሪው የጀመረው ጦርነት እየተመከተ ሲሆን በማዕበል የገባው ቡድን አሁን በየቦታው መቆራረጡን ተናግረዋል፡፡ የተቆረጠውን እንለቅማለን ፤ ዋናውን ቁንጮ በመምታት ቡድኑን ድጋሜ ሊረብሽ በማይችልበት ደረጃ ማጥፋት አለብን ነው ያሉት፡፡
አሸባሪው ያሰማራው ቡድን ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ እየደረሰበት መሆኑን በተለያዩ ግንባሮች መመልከታቸውንም አስረድተዋል፡፡ ወራሪው ቡድን በገባባቸው አካባቢዎችም ሕዝብ እንዳመጸባቸው አንስተዋል፡፡
አቶ ዮሐንስ የአሸባሪውን ሕልውና ለማሳጠር የተጀመረውን ርብርብ ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ወደ አማራ ክልል የገባ አንድም ጠላት እንዳይወጣ ሕዝባዊ አንድነት ፈጥሮ መንቀሳቀስ እንደሚገባም መክረዋል፡፡ አሁን ላይ ጠላት ያሰማራው ቡድን መውጫ ስለሌለው በየአካባቢው መበተኑ አይቀርም፤ በዚህ ጊዜ እያንዳንዱ የአማራ መሬት እሾህ ሆኖ ሊጠብቀው ይገባል ነው ያሉት፡፡ በተለይ በግንባር አካባቢዎች ሕዝቡ የጀመረው እንቅስቃሴ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜም ብዙ ጠላትን እየደመሰሱ ያሉ ጀግኖች መፈጠራቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
የወገን ኀይል ከነሙሉ አቅሙ ነው የሚገኘው ያሉት አቶ ዮሐንስ በሕዝብ ድጋፍና በውስጥ ኀይል ጥንካሬው ወረራውን በብቃት መክቶ በማጥቃት ጠላትን ላይመለስ እንደሚደመስስም ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m