በአሸባሪው ትህነግ ላይ በተወሰደው እርምጃ ተመትቶ የተበታተነውን ጠላት ሕዝቡ ሊለቅመው እንደሚገባ የሰሜን ምዕራብ እዝ የአንደኛ ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ብርሃኑ ጥላሁን ገለጹ።

460

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 15/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በክምር ድንጋይ አካባቢ ሲዋጋ የነበረው ጠላት እየተደመሰሰና ከፊሉ እየሸሸ መሆኑን የሰሜን ምዕራብ እዝ የአንደኛ ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ብርሃኑ ጥላሁን ተናግረዋል።

አሁን ላይ ቡድኑ የመዋጋት ቁመና የሌለውና የተከበበ መሆኑን ገልጸዋል። “አሸባሪው ትህነግን ዛሬ ካልደመሰስነው ነገ ሀገር ማፍረሱ ጥርጥር የለውም፤ ስለዚህ ሙሉ በሙሉ ሳንደመስሰው አናርፍም” ነው ያሉት ብርጋዴር ጀኔራሉ።

የተበታተነው ቡድን ነገ ድጋሜ ሊሰባሰብ ስለሚችል ሕዝቡ አንድ ሆኖ ጠላትን በማነቅ መደምሰስ ያለበት ጊዜው አሁን ነው ብለዋል።

በጥምር ኀይሉ ተመትቶ የሸሸውን ጠላት ሕዝቡ ሊለቅመው እንደሚገባም ብርጋዴር ጀኔራል ብርሃኑ አሳስበዋል።

አሸባሪው ትህነግ በሚያሰተላልፈው የሐሰት ፕሮፖጋንዳ መረበሽ እንደማይገባም ገልጸዋል።

በርካታ የጠላት ኀይል ረግፏል ያሉት ብርጋዴር ጀነራሉ
ጠላት ይዞት የገባው ከባድ መሳሪያዎችና ተሽከርካሪዎቹ ወድመዋል ብለዋል።

ሕዝቡ በግንባር በመዝመት፣ ስንቅ በማቀበልና መረጃ በመስጠት ለሠራዊቱ እያደረገ ባለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

አሸባሪው ቡድን ሙሉ በሙሉ እስኪጠፋ ድረስ የሕዝቡ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

“ሕዝቡ ድሉ የእሱ ድል መሆኑን አውቋል” ያሉት ብርጋዴር ጀኔራል ብርሃኑ ሌሊት ሳይቀር በስኬት ያታገለልን ሕዝቡ ነው ብለዋል።

በጋይንት ግንባር የሜካናይዝድ ክፍሎች አስተባባሪ እንዲሁም የአየር ኀይልና የምድር ኀይል እንቅስቃሴ አስተባባሪ ኮሎኔል ዘለቀ አለባቸው የጠላት ዓላማ ኢትዮጵያን መበታተን መሆኑን ከምርኮኞች አንደበት ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል። ጠላት በአየር እና በምድር ኀይል ከፍተኛ ውድመት እንደደረሰበት መሆኑን ገልጸዋል።

ሕዝቡ በውጊያው ከመሳተፍ በተጨማሪ እስከ ምሽግ ድረስ ስንቅ በማቅረብና ሰርጎ ገቦችን በመቆጣጠር ደጀንነቱን አስመስክሯል ነው ያሉት።

ሌሊት ላይ በጋሳይ የመጣው ጠላትም ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን ኮሎኔል ዘለቀ አስረድተዋል።

አሁንም የጠላትን እግር በመከተል የመደምሰስ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም ኮሎኔሉ ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ- ከጋሳይ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleማኅበረሰቡ አካባቢውን በመጠበቅ፣ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ የሚነዙ አካላትን በመዋጋት እና ሕገወጥነትን በመከላከል እያከናወነ ያለውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ፡፡
Next article❝ጠላት መውጫ ስለሌለው በየአካባቢው መበተኑ አይቀርም፤ በዚህ ጊዜ እያንዳንዱ የአማራ መሬት እሾህ ሆኖ ሊጠብቀው ይገባል❞ አቶ ዮሐንስ ቧያለው ቧያለው