ማኅበረሰቡ አካባቢውን በመጠበቅ፣ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ የሚነዙ አካላትን በመዋጋት እና ሕገወጥነትን በመከላከል እያከናወነ ያለውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ፡፡

348

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 15/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ትህነግ በአማራ ክልል በፈጸመው ወረራ እየተወሰደ ባለው እርምጃና ያደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ኮሚሽነሩ በመግለጫው እንዳሉት የትህነግ አሸባሪ ቡድን ከዛሬ ሰማንያ ዓመት በፊት ጣሊያን ከፈጸመችው ተመሳሳይ ግፍ በአማራ ሕዝብ ላይ ፈጽሟል፡፡ በዚህም አሸባሪ ቡድኑ በወረራቸው አካባቢዎች የግለሰብ እና የመንግሥት ሀብት እና ንብረት ዘርፏል፤ ንጹሐን ዜጎችን ገድሏል፤ አስገድዶ ደፍሯል፡፡ ለዚህ ደግሞ በሰሜን ወሎ ቆቦ ሮቢት አካባቢ አጋምሳ የተባለ መንደር ነዋሪዎችን በመጨፍጨፍና መኖሪያ ቤቶችን በማቃጠል፣ በወልድያ እና ደብረታቦር ደግሞ በመድፍ በመደብደብ ንጹሐን ዜጎችን መግደሉን በማሳያነት አንስተዋል፡፡

የአማራ ሕዝብና የጸጥታ ኀይል ከሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ከሌሎች ክልሎች የጸጥታ መዋቅር እንዲሁም ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በመቀናጀት በአሸባሪው ቡድን ላይ እየተወሰደ ባለው እርምጃ አመርቂ ድል እየተመዘገበ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡ በተወሰደው እርምጃም አሸባሪ ቡድኑ በርካታ የሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ ደርሶበታል ብለዋል፡፡

በተለይም ደግሞ ወጣቶች ከመከላከያ እና ከክልሉ የጸጥታ ኀይል ጋር በመቀናጀት ከጠላት ጋር ፊት ለፊት በመጋፈጥ በርካታ የነፍስ ወከፍ እና የቡድን የጦር መሳሪያዎችን በመማረክ ከፍተኛ ጀብዱ መፈጸማቸውንም ኮሚሽሩ ገልጸዋል፡፡ ሰርጎ ገብ የጠላት ኀይልንም በየሰፈሩ በደፈጣ እና በሽምቅ ውጊያ መግቢያ እና መውጫ እያሳጡት እንደሚገኝ ኮሚሽነሩ አመላክተዋል፡፡

ማኅበረሰቡም ስንቅ በማዘጋጀት እና በማቅረብ፣ ደም በመለገስ፣ የተፈናቀሉ ወገኖችን በመርዳት እና በማቋቋም እና ሰርጎ ገቦችን ለሕግ በማቅረብ ከፍተኛ ጀብድ ፈጽመዋል ብለዋል፡፡

አሸባሪው ትህነግ ምንም የማያውቁ ያልታጠቁ ሕጻናትን እና ሴቶችን ፊት ለፊት በማሰማራት እያዋጋ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

አሸባሪው ቡድን የውሸት ፕሮፖጋንዳ በመንዛት የሥነ ልቦና ጦርነት እያካሄደ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡ ለዚህም በማኅበረሰቡ ውስጥ ሰርጎ ገቦችን በማስገባት ፎቶ በመነሳት አካባቢውን እንደተቆጣጠሩ በማስመሰል በማኅበራዊ ሚዲያ መልቀቅ፣ ማኅበረሰቡ እንዲሸሽ ‹‹ትህነግ ከፍተኛ ኀይል እያስገባ ነው፤ ልቀቁ›› በሚል የሥነልቦና ጦርነት እያካሄደ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

በማኅበረሰቡ ውስጥም አንዳንድ ግለሰቦችን በመደለል በመረጃነት እየተጠቀመ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ባደረገው ክትትል በርካታ ተጠርጣሪዎችን በሕግ ቁጥጥር ስር ማዋሉንም አንስተዋል፡፡ ክትትሉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስገንዝበዋል፡፡ ማኅበረሰቡም እነዚህን አካላት ተከታትሎ ለሕግ ሊያቀርባቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ማኅበረሰቡ አካባቢውን በመጠበቅ፣ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ የሚነዙ አካላትን በመዋጋት እና ሕገወጥነትን በመከላከል እያከናወነ ያለውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleA glimpse of atrocities committed by TPLF since November 3, 2020
Next articleበአሸባሪው ትህነግ ላይ በተወሰደው እርምጃ ተመትቶ የተበታተነውን ጠላት ሕዝቡ ሊለቅመው እንደሚገባ የሰሜን ምዕራብ እዝ የአንደኛ ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ብርሃኑ ጥላሁን ገለጹ።