“በሉዓላዊነታችን ላይ የተቃጣውን የባንዳ ጥቃት ለመቀልበስ እንደ አባቶቻችን ሁሉ እኛም በአንድ መንፈስ ለአንድ ዓላማ ሁሌም በፅናት ልንቆም ይገባናል” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ

281

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 14/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ዕለታዊ መረጃ አውጥተዋል መረጃው ቀጥሎ ቀርቧል።

እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ አንድ ነጻ ህዝብ በህልውናችን ላይ ከተጋረጠው አደጋ የበለጠ ቅድሚያ ሠጥተን የምንረባረብበት ጉዳይ የለንም፡፡ እንደ አንዲት የቀደመ ሥልጣኔና ታሪክ ባለቤትና ነጻነቷን አስከብራ እንደኖረች ሀገር ባለቤትነታችን ከሉዓላዊነታችን አስበልጠን የተዋደቅንለት ሀገራዊ አደራ አልነበረንም፤ ዛሬም የለንም ነገም አይኖረንም፡፡

ህልውናውን እና ሉዓላዊነቱን የተቀማ ህዝብ ሆኖ ከመኖር ይልቅ ስለ ህልውና እና ሉዓላዊነታችን ስንል እየተዋደቁ ማለፍን የመረጥን አይበገሬዎች ነን፡፡

ይህ ኢትዮጵያዊ ስብና ከቀደምት አባቶቻችን የወረስነው እና ዛሬም እኛ እየኖርነው ያለነው ከኢትዮጵያዊነት የተቀዳ ህያው መርሃችን ሥለመሆኑ እንኳንስ እኛ የእሴቱ ባለቤቶች ይቅርና የውጭ ወራሪዎችም ሆኑ ተላላኪ ባንዳዎቻቸው አይዘነጉትም፡፡

ይህን ታሪካዊ እና ነባራዊ ሐቅ ክደው በኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ላይ የክህደት ሠይፋቸውን በመዘዙት የትህነግ የሽብር ቡድን መሪ እና ጀሌዎቻቸው ላይ የመዘዝነው “ሠይፈ-ኢትዮጵያ” የዘመናችን ባንዳዎች የአባቶቻቸውን ፍጻሜ እንዲደግሙት እያደረገ ይገኛል፡፡

ህልውና እና ሉዓላዊነታችንን ለማስጠበቅ የገባንበት ጦርነት የህይወት፣ የአካል እና የሃብት መስዋእትነት መጠየቁ እሙን ነው፡፡

ይሁን እንጂ በጦርነቱ ምክንያት ሊፈጠር የሚችለውን ምጣኔ ኃብታዊ፣ ማኅበራዊ እና የመልካም አስተዳደር ተግዳሮቶችን ለማስወገድ እጥፍ ድርብ ኃላፊነትን ወስደን የሚደራረብብንን ሁለንተናዊ ጫናዎችን ሁሉ ተቋቁመን የትም መቼም በምንም አይነት ሁኔታ ውስጥ ህልውና እና ሉዓላዊነታችንን ለማስከበር እንደአባቶቻችን ከመዋደቅ ውጭ ሌላ ሁለተኛ አማራጭ የለንም፡፡

ሥለሆነም በአንድ እጃችን በመላ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ላይ እልቂትን እና ሥር የሰደደ ድህነትን የመዝራት ተልእኮን አንግቦ የተሰማራውን የአሸባሪው ትህነግን ቡድን መቀመቅ የመወርወሩን የጦር ሜዳ ተግባር እየፈጸመን፤ በሌላኛው ክንዳችን ደግሞ የግብርና ምርትና ምርታማነታችንን ለማሳደግ፤ የህግ የበላይነትንና መልካም አስተዳደርን የማረጋገጥ ጥምር ኃላፊነታችንን መወጣት ይገባል፡፡

በጦርነቱ ልናጣው ከምንችለው ሀብት የበለጠ ምርትን በማምረት በድህረ ጦርነት ወቅት ሊከሰት የሚችልን ሠብዓዊ እና ቁሳዊ ጉድለት ማካካስ የሚችል አቅምን የመፍጠር ስራ ከጦርነቱ መሳ ለመሳ እየከወኑ ማለፍ ይገባናል፡፡

እንደ ግብርና ስራችን ሁሉ በየአካባቢያችን የሚሥተዋሉ ህገ ወጥ ድርጊቶችን ለማስወገድ እና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደር መዋቅሮች ከመደበኛው ጊዜ በበለጠ ትጋት በዚህ ወቅት ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል፡፡

በተለይም መሰረታዊ ምርቶችና ሸቀጦችን ፍሰት በማስተጓጎል፤ ምርትን በመሰወር እና በመከዘን የኑሮ ውድነት እንዲባባስ የሚያደርጉ ህገወጥ ነጋዴዎች እና ተባባሪዎቻቸው ላይ ምህረት የለሽ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ የማድረጉ ተግባር በጦር ሜዳ ውሎ የአሸባሪው ትህነግ አንጋቾችን ግንባር ከመበርቀስ የማይተናነስ ጀብድ ሥለመሆኑ አያጠራጥርም፡፡

በመሆኑም የግብርና ምርት የማሳደግ፣ መልካም አስተዳደርን በማስፈን ህገ ወጥነትን የመከላከል እና በንግዱ ስርዓት ውስጥ የሚፈጸምን አሻጥር የመበጣጠስ ተግባር በመከወን በተቀናጀ መልኩ በህልውና እና በሉዓላዊነታችን ላይ የተቃጣውን የባንዳ ጥቃት ለመቀልበስ እንደ አባቶቻችን ሁሉ እኛም በአንድ መንፈስ ለአንድ ዓላማ አሁኑኑ ልንቆም ይገባናል፡፡

በአውደ ውጊያው በሁሉም ግንባሮች በጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ አማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና ፋኖዎቻችን ጥምረት በጠላት ላይ እየተወሰደ ያለው የማጥቃት እርምጃ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

በሁሉም ግንባሮች በተናበበ ቅንጅት ጠላት እየተደቆሰ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ህዝባችን ከጀግኖቻችን ጋር ያሳየውን ጥምረት አሁንም በጠላት ፕሮፖጋንዳ ሳንበረከክ አኩሪውንና ዋናውን ድል ለማስመዝገብ ደጀንነቱን በሚሰጠው ማንኛውም ሚና አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል፡፡ በየአውደ ውጊያው ዛሬም እንደትላንቱ መልካም ድሎች እየተገኙ ነው። እነዚህን ድሎች እያሰፋን የማጥቃት ፍጥነታችንን አጠናቅረን ወደፊት መጓዛችንን መቀጠል ለነገ የሚባል ተግባር አይደለም። ዝርዝሩን እንደ አስፈላጊነቱ በቀጣይ ቀናት የምናሳውቅ ይሆናል።

ለኢትዮጵያ ሀገሬ እዘምታለሁ፤
መቼም፤ የትም፤ በምንም !!!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየደብረ ታቦር ወጣቶች ግንባር ድረስ በመሰለፍ ደጀንነታቸውን እያሳዩ ነው።
Next articleአሸባሪው ትህነግ በደብረታቦር ሕዝብ ላይ የፈጸመው የከባድ መሳሪያ ድብደባ የአማራ ሕዝብን በጠላትነት መፈረጁን በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።