ኢትዮጵያ ከሀዲዎቿን ድል ትነሳለች!

192

ባሕር ዳር: ነሐሴ14/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ማህፀነ ለምለም ናት። ልጆቿ ለክብሯና ለነጻነቷ ይዋደቁላታል። ሌላኛው ልጇ ደግሞ በባንዳነት ሀገርን ለማፍረስ ይሠራል። ኢትዮጵያ በባእዳን በተወረረችባቸው ዘመናት እናት ሀገራቸውን ከድተው ከጠላት ጋር ተሰልፈው በሀገራቸው ላይ ጦር የሰበቁባት ብዙዎች ናቸው። ምክንያታቸው ደግሞ እሴት አልባነት እና ስግብግብነት ነበር።

ሻምበል አስማማው አቡኔ የጦር ልምድ ያላቸው በኋላም በፖሊስነት ያገለገሉ በአሁኑ ወቅትም በጡረታ የተገለሉ ናቸው። ሀገራቸውን የከዱ ባንዳዎች በጣሊያን ወረራ ወቅት በሰሜን ኢትዮጵያ እነ አሉላ አባ ነጋ ላይ የተለያዩ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት ለጠላት ይሠሩ ነበር ብለዋል።

እነዚህ ባንዳዎች እውነተኛ የሀገር ፍቅር የነበራቸውን የትግራይ አካባቢ ጀግኖችን ለጠላት እየጠቆሙ ያስገደሉ ነበር ያሉት አቶ አስማማው ባንዳዎቹ ከሀገር ክብር ይልቅ ግላዊ ጥቅምን የሚያስቀድሙም ናቸው ብለዋል።

ዛሬም ኢትዮጵያን እየወጓት ያሉት ትናንት ከጣሊያን ጎን የተሰለፉ የባንዳ ልጆች ናቸው ይላሉ። ባንዳ ኀላፊነት ሊሰጠው የማይችል፣ እምነት ለማሳደር የማይሆን፣ ተሹሎክላኪ፣ የሀገርን ሚስጢር ለጠላት አሳልፎ በመስጠት ወገንን የሚወጋ ነው ብለዋል ሻምበል አስማማው።

ዛሬም የውጭ ተልዕኮ ውክልና ወስዶ ሀገር ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሰው አሸባሪው ትህነግ ጋር በጥቅም ተሳስረው መንገድ የሚመሩ ባንዳዎች አሁንም አሉ ነው ያሉት። ከወገን የተሰለፉ መስለው መረጃ የሚዘርፉ ጆሮ ጠቢዎች አሉ፤ እነዚህ ጆሮ ጠቢዎች ሲመቻችላቸው ያጎረሳቸውን እጅ ከመንከስ አይመለሱምና ወጣቱ በንቃት ሊከታተላቸው ይገባል ብለዋል።

ባንዳዎች ዋና መለያቸው ሀሰተኛ መረጃዎችን በመንዛት የወገን ጦር እንዲያፈገፍግ ወይም ለጠላት መንገድ እንዲከፍት በርትተው እንደሚሠሩ አብራርተዋል። “ጦሩ እኮ እየሸሸ ነው ለምን እኛ እዚህ እንሞታለን መሸሽ አለብን” በማለት ከጎናቸው ያሉ ሀገር ወዳድ ጀግኖችን ወኔ የማሸበር እና ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው ማድረግ ዋና መለያቸው ነው ይላሉ።

አሁንም “ጁንታ መጣ እዚህ ደረሰ ሊጨርሰን ነው” በማለት ሕዝቡ አካባቢውን ለቆ እንዲወጣ ማድረግ የባንዳዎች ተግባር ነውና ሁሉም ይሄን እኩይ ዓላማቸውን ማክሸፍ ይኖርበታል ብለዋል።

ሀገር እናት ናት እና እሷ ከሌለች መኖር እንዴትስ ይሆናል ነው ያሉት።

“ወንድሜ ነው ብየ ብነግረው የሆዴን፣
አጋም ቆርጦ ቆርጦ አጠረው መንገዴን” እንዲሉ በበጎ ግዜ ወዳጅ መስለው ጊዜ ሲከፋ ጠላት ሆነው ከተፍ የሚሉ ባንዳዎች የሚያሸንፉ ሳይሆኑ ራሳቸው የሚጠፉ ናቸው። ታሪክም የሚመሰክረው ይሄንን ነውና ኢትዮጵያም ከሀዲዎቿን ድል ትነሳለች።

ዘጋቢ፡- ፈረደ ሽታ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleአሸባሪው ትህነግ ከጥቅምት 24/2013 ጀምሮ የፈፀማቸው ወንጀሎች (በከፊል…)
Next articleበሰሜን አሜሪካ የአማራ ማኅበር ለደባርቅ ሆስፒታል የምግብና የአልባሳት ድጋፍ አደረገ።