ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ በደሴ ከተማ ለተጠለሉ ተፈናቃዮች የሚውል የምግብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡

326
ባሕር ዳር: ነሐሴ14/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በወሎ ዩኒቨርሲቲ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ የቀረበውን የድጋፍ ጥሪ ተከትሎ ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ በደሴ ከተማ ለተጠለሉ ተፈናቃዮች የሚውል ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ አስረክቧል፡፡
ለተፈናቃዮች ድጋፍ ለማድረግ ደሴ ከተማ የተገኙት የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲው ተወካይ ኡመር ኑሩ (ዶክተር) ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንደገለጹት በአሸባሪው ትህነግ ከሰሜን ወሎ ዞን ተፈናቅለው በደሴ ከተማ ለተጠለሉ ተፈናቃዮች የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አጋርነቱን ለማሳየት ፈጣን ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ወሎ ዩኒቨርሲቲ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባደረገው ጥሪ መሰረት ድጋፉን በአፋጣኝ ገዝተው እንዳጓጓዙም ገልጸዋል፡፡ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብ እና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውንም አስረድተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዶክተር ኡመር አብራርተዋል፡፡
“የሽብር ቡድኑን በጋራ መመከት ይኖርብናል” ብለዋል።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት አፀደ ተፈራ (ዶክተር) በበኩላቸው የተፈናቃዮች ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ በመምጣቱ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ድጋፍ በማድረግ አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ ጥሪ አቅርበዋል።
ጥሪውን ተከትሎም ዩኒቨርሲቲዎች በጎ ምላሽ እያሳዩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በዚህም ከ10 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል፡፡ ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ለሰጠው ፈጣን ምላሽም አመስግነዋል፡፡ በዚህ ወቅት የተደረገው ድጋፍ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለማጠናከር ወሳኝ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀን አምባቸው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleአሸባሪው ትህነግ በደብረታቦር ከተማ የፈጸመው የሽብር ጥቃት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያወግዝ የትዊተር ዘመቻ ተካሄደ፡፡
Next articleበአሸባሪው ቁንጮ ፃድቃን ገ/ትንሣይ የሚመራው የጠላት ኅይል በመከላከያ ሠራዊታችን ተመታ።