
ባሕር ዳር: ነሐሴ14/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትህነግ ቡድን የፈጸመውን ወረራ ለመቀልበስና ቡድኑን ለመደምሰስ መከላከያ ሠራዊት፣ የየክልሎች ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻና ፋኖ በቅንጅት ርብርብ እያደረጉ መሆኑን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የአደረጃጀት ጉዳይ ኀላፊ ጋሻው መርሻ ገልጸዋል፡፡ በዚህም የጠላት አቅም መዳከሙን ተናግረዋል፤ በደረሰበት ከፍተኛ ምት ‹‹መስመሩ እንደጠፋበት ጉንዳን እየተርመሰመሰ ነው›› ብለዋል፡፡
አሁን የቀረው ጉልበት ምላሱ ብቻ በመሆኑ የሽብርና የውዥምብር ወሬ እየነዛ ይገኛል፤ ምላሱን ደግሞ በቅርቡ እንቆርጠዋለን ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እገባለሁ ያለውን የባንዳዎች ስብስብ እንዳይመለስ አድርገን ወደ ሲኦል እንሸኘዋለን ብለዋል፡፡
አሸባሪው ቡድን በፈጸመው ወረራ ምክንያት የልማት፣ የንግድና ሌሎች ሥራዎች እንዳይስተጓጎሉ ዘመቻውን በአጭር ጊዜ መጨረስ የግድ ይላል ያሉት አቶ ጋሻው ጠላትን እየመታ ያለውን የወገን ኀይል ማገዝና ማጠናከር እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡
ሕዝቡ ድጋፍ በማድረግ፣ ስንቅ በማቀበል እና ሎጅስቲክስ በማጓጓዝ እያደረገ ያለው ከፍተኛ ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑን አቶ ጋሻው ተናግረዋል፡፡ አቶ ጋሻው ዘመቻው በአጠረ ጊዜ እንዲጠናቀቅ አሁንም የበለጠ ርብርብ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ለሕልውና ዘመቻው በፌዴራልና በክልል ደረጃ የጋራ ጥምር ግብረ ኀይል ተቋቁሟል፤ ግብረ ኀይሉ ባለበት ቦታ ሁሉ የአብን የሥራ ኀላፊዎች ሥምሪት ወስደው በልዩ ልዩ ዘርፎች የድርሻቸውን እየተወጡ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ እሳቸውም በደብረታቦር ሕዝቡን ሲያስተባብሩ መቆየታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ