
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 14/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የእውቁ ኢትዮጵያዊ ፊልም ባለሙያ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ አባት ገሪማ ታፈረ “ጎንደሬ በጋሻው” በሚል ርዕስ በአምስቱ ዓመት የአርበኝነት ዘመን የነበረውን ተጋድሎ በሚያወሳው መጽሐፋቸው በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ አካባቢ የነበረውን የጎንደር አርበኞች ተጋድሎ በሰፊው ይዘረዝራሉ፡፡
አርበኞቹ ከወፍ አርግፍ እስከ ቃፍታ፣ ከዳንሻ እስከ ሁመራ፣ ከማይ ለመሞ እስከ አዲ ኮከብ፣ ከጠለምት እስከ አርማጭሆ ለሀገር ክብር ተዓምራዊ ጀብዱ ፈፅመዋል ይላሉ፡፡ ከአርበኛ ብሬ ዘገየ እስከ ፊታውራሪ መስፍን ረዳ፣ ከደጃዝማች ደስታ ማሩ እስከ ደጃዝማች አዳነ መኮንን ጣሊያንን መውጫ መግቢያ አሳጥተው ለብልበውታል፡፡
ለጣሊያን ወራሪ አድሮ መረጃ እያቀበለ የቡና ቁርስ የሚያክል ፍርፋሪ እየተቀበለ ያስቸገራቸውን የውስጥ ሰውም “ካለቦታው የተገኘ ነጭ ሰሊጥ ከኑግ ጋርም ቢሆን ይወቀጥ” እያሉ ሰላቶን ከባንዳ ቁም ስቅሉን አሳይተውታል ይባላል፡፡ በዚያ የአርበኝነት ዘመን በዱር በገደሉ የሚዋደቁ አርበኞች ለነፍሳቸው እንኳን ሳይሳሱ ጦርነቱን እንደባህላዊ ጨዋታ ጨፍረውበታል፡፡

በውጊያ የሚማርኳቸውን የጣሊያን ወታደሮች “ፈረንጅ ጌታ” እያሉ መቀለጃ እና መጫዎቻ አድርገዋቸው ነበርም ይላሉ፡፡ የሀበሻ አርበኞች ትህትናቸው ጭንቀትን፣ ርህራሄያቸው ጥርጣሬን እና ጀግንነታቸው ፍርሃትን የለቀቀባቸው የጣሊያን ወታደሮችም የሀበሻ አርበኞችን የሚገልጹበት ገጸ ባህሪ አጥተው ነበር፡፡ በወልቃይት ጠገዴ ከአዲ ኮከብ ምሥራቃዊ አቅጣጫ የሚገኘውን የማይ ለመሞን ተራራ ተጠግቶ የመሸገው አርበኛ ጦርነቱ ከዛሬ ነገ ተጀምሮ ፈረንጂ እና ጠበንጃ እማርካለሁ እያለ ቢጠብቅ ምክክር ላይ ያሉት የጦር አበጋዞች አልጨርስ አሉ፡፡
አምስት ቀን ከአምስት ሌሊት ተራራ ላይ ተጠግተው የተቀመጡት አርበኞች “ደግሞ ለፈረንጂ ጦር ይህን ያክል መዶለት ምን የሚሉት አዋቂነት ነው” እያሉ ቢያጉረመርሙም ሰሚ አጡ፡፡ ማታ አርበኞቹ ተሰባስበው ቅሬታቸውን በቀረርቶ እና በፉከራ ሲገልጹ ከአርበኞች መካከል አንዱ የነበረው አርበኛ ስጦት መኮንን፤
“ቂርቆስ ማይ ለመሞ የሁለት ፈሪ ሀገር
ወይ እነርሱ አይመጡ ወይ እኛ አንሻገር” ሲል የጦርነቱን መዘግየት በሚመለከት ቅሬታውን ገልጧል ይባላል፡፡ ዛሬም በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ባለው የአማራ ምድር ሁሉ ስንቀሳቀስ መሰል አስተያየቶችን እንሰማለን፡፡
በተለይ አሸባሪው የትህነግ ቡድን በወሎ እና ጎንደር መሃል ሀገር ገብቶ ንጹሃንን እየጎዳ ንብረት እያወደመ መሆኑን የሰሙት ወልቃይቴዎች ድርጊቱ እንደ እሳት እና ድፍረቱ ክፉኛ ለብልቦናል ሲሉ ታዘብን፡፡ ወልቃይቴዎች ስለአሸባሪው ቡድን ጥንተ ባህሪ በደንብ ያውቃሉና ለእነርሱ ማዘንም ሆነ እነርሱን ማመን ቀብሮ ብቻ ነው ሲሉ ይናገራሉ፡፡

የአካባቢው ሕዝብ ልበ-ሙሉነት በኢትዮጵያ ላይ ተስፋ ለማድረግ ብቻውን ምክንያት ይሆናል፡፡ አማራነት ያለስጋት የሚቀነቀንበት ቦታ የት ይሆናል ካላችሁ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን መልስ ነው፡፡ መሬት ማረስን እና ጠላት ማፍረስን የተካኑት እነዚህ አማሮች አሸባሪው ቡድን ለኢትዮጵያ ስጋት ከማይሆንበት ደረጃ ላይ እስኪደርስ ድረስ እንቅልፍ አያስፈልግም ባዮች ናቸው፡፡
ከሁሉም የሚገርመው ግን ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ማንነታቸው እንዲከበር መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎናቸው አድርገው ሲታገሉ የነበሩት ወልቃይቴዎች ዛሬ ደግሞ እንዲህ ይላሉ “እባካችሁ ብድር መላሽ አድርጉን” ኢትዮጵያ ትናንት የተደረገላቸውን በማይረሱ ልጆቿ ዘመናትን ትዋጃለች፡፡
በታዘብ አራጋው -ከሁመራ ግንባር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ