
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 13/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን፣ በአፋር ዞን ሶስት እና አርጎባ ብሄረሰብ ልዩ ወረዳ ባሉ መተላለፊያ ቦታዎች የስጋት ቀጠናዎችን በመለየት በቅንጅት እየሠሩ መሆናቸውን የየዞኖቹ አመራሮች ተናግረዋል።
ከፌደራልና ከክልል የተውጣጡ የመንግሥት አመራሮች ከዞን ከወረዳና ከቀበሌ አመራሮች እና የፀጥታ ኃላፊዎች ጋር በአልዩ አምባ ከተማ ላይ መክረዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሐመድ (ዶክተር) የህወሃት የሽብር ቡድን ጥቃት መጀመሪያ ገፈት ቀማሽ የሆኑት የአማራና የአፋር ክልሎች ህልውናቸውን ለማረጋገጥ በጋራ እንዲቆሙ አድርጓቸዋል ብለዋል።
በሕዝቡ ውስጥ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ የሚነዙ አካላትን ለመቆጣጠር የአፋርን የመረጃ ስርዓት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ብልጽግና ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ብርሃኑ ጦርነት የሚጠይቀውን ሥነ ልቦና በመታጠቅ የህወሓት እና የኦነግ ሸኔ የሽብር ቡድኖችን የሰርጎ ገብ እንቅስቃሴ ለመግታት በትብብር መስራት ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።

አሸባሪው ህወሓት በውሸት ትርክት ተለያይተን የነበርን ሕዝቦች እንድንሰባሰብና ህብረት እንድንፈጥር አድርጎናል ያሉት የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ፍቅረማርያም ደጀኔ ይህንን ትብብር እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከድል በኃላ ለልማት ልናውለው ይገባልም ብለዋል።
በአፋር ክልል የዞን ሶስት ምክትል አስተዳዳሪ እና ጸጥታ ዘርፍ ኀላፊ አቶ አብዱ አሊ በአማራ ሕዝብ ላይ ሂሳብ አወራርዳለሁ ባለው የህወሃት የሸብር ቡድን ላይ በአፋር ሕዝብ ላይ በፈፀመው ጭፍጨፋ ቀድመን በጋራ ሂሳብ እናወራርድበታለን ብለዋል።
አመራሩን ከህወሃት አስተሳሰብ ማውጣት ላይ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸውም አንስተዋል።
የዞን፣ የወረዳና የቀበሌ አመራሮቹና የፀጥታ ኃላፊዎቹ በሚዋሰኑባቸው ቦታዎች በጋራ ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠር እየተሠራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ሃብት ማሰባሰብ፣ ለመከላከያ መመልመል፣ የህልውና ዘመቻውን ተቀላቅለው ወደ ግንባር የዘመቱ የዘማች ቤተሰቦችን መደገፍ ላይም ሊሠራ እንደሚገባ የጋራ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
ምንጭ: የሰሜን ሸዋ ዞን ኮምዩኒኬሽን
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ