
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 13/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (IOM) በመራው ውይይት ላይ የተባበሩት መንግሥታት የሀገራት ቡድን (UNCT)፣ የተባበሩት መንግሥታት የሕዝብ ፈንድ (UNFPA) እና የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ጽሕፈት ቤት (OHCHR) ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን ብዙኃን መገናኛ ምን ያህል የተጋነነ እና የተዛባ መረጃ ሲያሰራጩ እንደነበር አንስተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ኀላፊ እና በአፍሪካ ሕብረት እና የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ተወካይ ሞሪን አቺንግ በትግራይ ክልል ተፈጸመ ስለተባለው የጾታዊ ጥቃትና አስገድዶ መድፈር ተብሎ ሲሰራጭ የነበረውን መረጃ እውነታነት ለማረጋገጥ ብዙ ርቀት መኬዱን በውይይቱ ላይ ሲያብራሩ ይደመጣል፡፡ ነገር ግን በትግራይ ክልል ተፈጸመ ስለተባለው አስገድዶ መድፈር በእውነቱ ምንም ዓይነት የተረጋገጠ ማስረጃ እንደሌላቸውም ጠቅሰዋል፡፡

ሌቲ ቺዋራ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥርዓተ -ፆታ እኩልነት እና የሴቶች አቅም ማጎልበት (ዩ ኤን ውሜን) የኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ ሕብረት እና የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ተወካይ ናቸው፡፡ ሌቲ ቺዋራ በውይይቱ ላይ የድርጅታውን ዓላማ በመጥቀስ በትግራይ ክልል ተፈጸመ የተባለው ጾታዊ ጥቃት በቀጥታ እንደሚመለከታቸው እና ጉዳዩን በትኩረት እየተከታተሉት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ አፈትልኮ በወጣው የድምጽ መረጃ ሌቲ ቺዋራ በሕግ ማስከበሩ ወቅት በትግራይ ክልል ተፈጸመ ስለተባለው የጾታ ጥቃት ተጨባጭ ማስረጃ አለመኖሩን ያስረዳሉ፡፡
ተወካዮቹ ከብዙኃን መገናኛ ስሜታዊ የሆኑ ጥያቄዎች ይቀርቡላቸው እንደነበር አንስተው ሽብርተኛው ትህነግ እና አንዳንድ ዓለም አቀፍ ብዙኃን መገናኛ ተቋማት እንደሚያራግቡት በክልሉ ተፈጸመ ስለተባለው ጾታዊ ጥቃት ተጨባጭ መረጃ እንደሌላቸው አስታውቀዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ጽሕፈት ቤት ተወካዩ ቻርለስ ንዲይማ ክዌይሞይ ተፈጸመ ስለተባለው ወንጀል ምንም ተጨባጭ ማስረጃ እንዳልተገኘ ሲያስረዱ ተደምጠዋል፡፡ ተወካዮቹ ከብዙኃን መገናኛ ተቋማት ምን ያህል ሴቶች ተደፍረዋል? በምን ዓይነት ሁኔታ? ምን ተጨባጭ መረጃ አላችሁ? እና መሰል ጥያቄዎች እንደሚነሱ እና ትክክለኛ መልስ ለመስጠት የሚያስችል ማስረጃ እንደሌላቸው ነው ሲገልጹ የሚደመጡት፡፡
የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ እና ቃል ዐቀባያቸው ጭምር ከዚህ በፊት በክልሉ ተፈጽሟል ተብሎ ሲገለጽ የነበረው መረጃ ተዓማኒነት የሌለው መሆኑ ግራ አጋብቷቸዋል፡፡ እናም ያንን መረጃ እንዴት ወደ እውነታው እናምጣው የሚለው የውይይቱ አወዛጋቢ አጀንዳ ሆኖ እንደነበር ተገልጿል፡፡

በየማነብርሃን ጌታቸው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ