ወላጅ እና ልጅን የነጠለው የትህነግ ሴራ።

110
ባሕር ዳር: ነሐሴ13/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በአሸባሪው ትህነግ የአገዛዝ ዘመን የተነጠቀችው ክብሯን ብቻ ሳይሆን ማንነቷን ጭምር ነው፡፡ አግላይ በነበረው የሦስት አስርት ዓመታት መዋቅራዊ ሥርዓት የተጎዳው ቁሳዊ ሃብቷ ብቻ ሳይሆን ልዩ የሆነው እሴቷም ጭምር ነበር፡፡ ልክ እንደ 13 ወራት ውብ ጸዳሏ ሁሉ ለቀሪው የዓለማችን ክፍል ብርቅ እና ድንቅ የነበረው መከባበር፣ ፍጹማዊ እምነት እና መተሳሰብ እንዳልነበር ሆኖ ተቦርቡሯል፡፡ ታናሽ ታላቁን ማክበር፣ ለቃል መታመን እና የሰው ገንዘብ መናቅ ደብዛቸው እንዲጠፋ ተደርጎ “መንግሥት እንኳን ይሰርቃል” እየተባለ እንደሥራ በአደባባይ የተነገረበት ጊዜ ሩቅ አልነበረም፡፡
ትውልዱ ከሰውነት በታች ወርዶ አጥንት እየቆጠረ እንዲቧደን ልምምዱን የወሰደው ከአሸባሪው ቡድን መዋቅራዊ ሥርዓት ነበር፡፡ የሐሳብ ልዩነትን እንደጸጋ ወስዶ ከመጠቀም ይልቅ ልዩነቱን እያሰፉ በሕይዎት እስከመፈላለግ ድረስ የዘለቀ ሴራ ምንጮቹ የእናት ጡት ነካሾቹ እንደነበሩ ታሪክ ይነግረናል፡፡
አቅፎ ስሞ ማነቅ፣ ጋብዞና አጉርሶ ከኋላ መምታት እና አብሮ ተኝቶ ማረድ ቡድኑ እንደታሪክ እና ጀብዱ ለትውልዱ ሲያወሩት የነበር አሳፋሪ ውርሳቸው ነው፡፡ “እንኳን መብላት ማብላት ይቀራል” ለሚሉት ኢትዮጵያዊያን የአሸባሪው ትህነግ ስግብግብ አካሄድ ፍጹም መለመድ የሚገባው ባህል አልነበረም፡፡
አንድን ብሔር ጠርቶ እና ለይቶ እንደጠላት ፈርጆ ትግል የጀመረ ቡድን ቢኖር ምናልባትም ትህነግ በዓለም ላይ የመጀመሪያው ሳይሆን አይቀርም፡፡
አሸባሪው ትህነግ ልዩነትን በደም የሚያደምቅ፤ በደም ተመስርቶ ደም ሳያደርቅ በደም ወደመቃብር ለመውረድ የተዘጋጀ ቡድን ነው፡፡
አሸባሪው ትህነግ ከፋፍለህ ግዛ መርህ በሀገረ- መንግሥት ምስረታ ሂደት ብቻ ሳይሆን እስከ ቤተሰብ ድረስ ይወርዳል፡፡ በቡድኑ የስልጣን ዘመን ወንድም ወንድሙን ይሰልል ነበር፡፡ በጓደኞች መካከል ጥርጣሬ እንዲነግስ እና ፍቅር እንዲያንስ እንደ አንድ የመታገያ መንገድ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ የዛሬ ባለታሪካችን የአሸባሪው ቡድን የልዩነት ሴራ ያቆሰለውን የአባት እና ልጅ ታሪክ ያስቃኘናል፡፡
ሐጅ ንጉሥ ወንድም ተወልዶ ያደገው በጥንታዊዋ የስሜን በጌምድር ጠቅላይ ግዛት ዳባት አውራጃ ዳንሻ አካባቢ ነበር፡፡ እነዚያ ጡት ነካሾች የኢትዮጵያን ሥነ መንግሥት እርካብ እስኪቆናጠጡ ድረስ ተወልዶ ያደገው በአማራዊ ሥነ ልቦና እንደነበር የልጅነት ጊዜ ትዝታዎቹን እያነሳ አጫውቶናል፡፡ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ አካባቢን ለቆ ሲወጣም አካባቢው የአማራ ግዛት እንደነበር ያስታውሳል፡፡
በወቅቱ የሚነሳው የትግል ጥያቄ መርሆ ወጣቱን ገና በለጋ እድሜው ወደትጥቅ ትግል እንዲገባ ገፋፋው እና ታጋይ ሆነ፡፡ በትጥቅ ትግሉ ወቅትም ከበኩር ልጁ እናት ጋር የፍቅር ግንኙነት መሰረተ፡፡ በወቅቱ ታጋዮች የፍቅር ግንኙነት ይመሰርቱ ዘንድ አይፈቀድም ነበር እና እስኪፈቀድ ድረስ በዓይን ፍቅር ቆየ፡፡ ትግሉ ወደ መጠናቀቁ ሲቃረብ ታጋዮቹ የፍቅር ግንኙነት እንዲኖራቸው በመፈቀዱ የሁለቱ ጥንዶች የልብ መሻት ለአብሮነት የሚሆን እድል አገኘ፡፡
የእነ ሐጂ የፍቅር ግንኙነት በትግሉ ቆይታቸው የመጨረሻዎቹ ዓመታት በጋብቻ ተሳሰረ፡፡ ሴቷ ታጋይ ከትግሬ ወንዱ ታጋይ ከአማራ ትግል አገናኝቶ በጋብቻ አጣመራቸው፡፡ ከጋብቻ ጥቂት ጊዜ በኋላ ትዳራቸው ለሁለቱም የበኩር ልጃቸውን አስገኘ፡፡ የተወሰኑ ጊዜያትን በትዳር የቆዩት ጥንዶቹ ታጋዮች እናት ከትግሉ መቀነሳቸውን ተከትሎ የሕወሓት ተቀናሽ ታጋዮች መቋቋሚያ በመዘጋጀቱ ልጃቸውን ይዘው ወደ ዳንሻ ዲቢዥን በሚባል አካባቢ ከልጃቸው ጋር መጥተው እንዲሰፍሩ ሲደረግ አባት ሐጂ ንጉሤ በውትድርናው ዓለም ቀጠሉ፡፡ በዚህ ሁሉ መካከል ግን ትዳሩ እንደቀጠለ ነበር፡፡
1988 ዓ.ም ታጋዮች ለቀጣይ ሰባት ዓመታት በውትድርና እንዲያገለግሉ ስምምነት እንዲወስዱ ሲጠየቅ ከ10 ዓመታት በላይ የቆዩበትን ውትድርና ለቀው ለመውጣት ወሰኑ፡፡ መከላከያ ሚኒስቴር ጥያቄያቸውን ተቀብሎ ከመከላከያ ተቀንሰው ወደትውልድ አካባቢያቸው ተመለሱ፡፡ ከባለቤታቸው እና ልጃቸው ጋር ድጋሜ ተገናኝተውም በጋራ መኖር ቀጠሉ፡፡
እናት የትህነግ ተቀናሽ ታጋይ በመሆናቸው በመንግሥት ይደጎማሉ፤ አባት የዚህ እድል ተጠቃሚ ባይሆኑም ሕይዎትን በሥራ እየተረጎሙ መከፋት እንኳን ቢኖር የውስጣቸውን በውስጣቸው ይዘው ቀጥለዋል፡፡ ስለፍቅር ሲሉ ከትግል በኋላ ያሉ መድሎዎችን ችለው በሌላ የሕይዎት መንገድ ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን መምራት ቀጥለዋል፡፡
ነገሮች አልመች ሲሉ በትግል ዘመን የተጀመረው የሐጂ እና የባለቤታቸው ትዳር አንድ ልጅ ብቻ አፍርቶ ፈረሰ፡፡ አሁን ባል እና ሚስት ተለያይተውም ቢሆን የጋራ የሚያደርጋቸው ልጅ ስለተፈጠረ ላለመስማማት ተስማምተው ተለያይተዋል፡፡ ግን መገናኘት አይቀርም ልጅ አላቸውና በክፉ በደጉ ይገናኛሉ፡፡ በዚህ መካከል እናት ሌላ ትዳር መስርተው ወደ ትውልድ ቀያቸው ሽሬ ያቀናሉ፡፡ ሐጂ ልጃቸው ከእርሳቸው ጋር እንዲያድግ በመፈለግ ትተውላቸው እንዲሄዱ ቢጠይቁም እናት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ልጅ ከእናቱ ጋር ወደ ሽሬ አቀና፡፡ በአካል የተለዩት አባት ከአብራክ ክፋያቸው ጋር በመንፈስ አልተለዩምና የቻሉትን ሁሉ ይደጉማሉ፡፡
በአካል እና መንፈስ እየጎለመሰ የመጣው የሁለቱ ታጋዮች ልጅ 11ኛ ክፍል ላይ ሲደርስ ወደ አባቱ መጥቶ ዳንሻ መማሩንም አባቱ ነግረውናል፡፡ ወደ ሽሬ ተመልሶ የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን ያጠናቀቀው የሐጂ የበኩር ልጅ ምንም እንኳን የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት ቢመጣለትም መቀጠል ስላልፈለገ ወላጆቹ መንጃ ፈቃድ ያወጡለታል፡፡ በመቀጠልም ሽሬ አካባቢ በመንግሥት ተቋም ተቀጥሮ እየሠራ እያለ ወላጆቹ የግል መኪና ገዝተው ስለሰጡት የግል ሥራ ይጀምራል፡፡
የአባት እና ልጅ ልዩነት የተጀመረውም በዚህ ሰሞን እንደነበር ሐጂ ይናገራሉ፡፡ 2008 ዓ.ም አካባቢ የወልቃይት የማንነት ጥያቄ እያየለ መምጣቱን ተከትሎ የአሸባሪው ትህነግ ቡድን ሽብር ውስጥ ገብቷል፡፡ የአሸባሪው ቡድን ሹመኞች በአደባባይ የሚናገሩት ሌላ ቢሆንም ውስጥ ውስጡን ግን ከፍተኛ መረበሽ ላይ ነበሩ የሚሉት ሐጂ ንጉሤ የእነርሱን ጭንቀት ሕዝቡ ውስጥም አሰራጭተውት ስለነበር አማራ የተለየ ስዕል እንዲኖረው አድርገውታል ይላሉ፡፡
ሐጂ የግል ሥራ የጀመረውን ልጃቸውን ዳንሻ አካባቢ መጥቶ እንዲሠራ ጥሪ ያቀርቡለታል፡፡ በወቅቱ የሐጂ ምክንያት የተሻለ የሥራ እንቅስቃሴ በአካባቢው በመኖሩ የተሻለ ተጠቃሚ ይሆናል በሚል ነበር፡፡ ልጃቸው ግን ፍቃደኛ አልነበረም።
በአሸባሪው ቡድን ላይ የተጀመረው የሕዝብ አመጽ ተባብሶ ቀጥሎም ከአራት ኪሎ ወደ መቀሌ ሲሸሹ ጉዳዩ ይበልጥ አሳሳቢ እየሆነ መጣ፡፡ በዚህ መካከል ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም አሸባሪው የትህነግ ቡድን በመከላከያ ሠራዊት ላይ በፈጸመው ክህደት ነገሮች እየተባባሱ መጡ፡፡ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥም ወልቃይት ከዘመናት ትግል በኋላ ነጻነቷን አገኘች የሚሉት ሐጂ በዘመናቸው ደስታ ከሚሏቸው ነገሮች አንዱ ይህንን እውነት ያዩበት ጊዜ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ሐጅ አሸባሪውን ቡድን ከልጅነት እስከ እውቀት በሚገባ ያውቁታል፡፡ ሴራቸውን፣ ክህደታቸውን፣ ግፋቸውን፣ የከፋፍለህ ግዛ መርሃቸውን ተገንዝበውታል፡፡ ነገር ግን ልጅ እና አባትን ክፉ ከመናገር አልፎ በሕይዎት እስከመፈላለግ የሚያደርስ የጥላቻ መርዝ ይረጫል ብለው ግን አልጠበቁም ነበር፡፡
ከሕግ ማስከበር ዘመቻው ጀምሮ በአካል ቀርቶ በስልክ እንኳን ያላገኙት የበኩር ልጃቸው ጉዳይ ያሳሰባቸው ሐጂ ልጃቸውን ሲያገኙ አቅፎ ስለመሳም እንጂ ሌላ ነገር በአዕምሯቸው እንዳልነበር ይናገራሉ፡፡
ከብዙ ወራት መጠፋፋት በኋላ ከተከዜ ወዲያ ማዶ ከአብራካቸው ክፋይ ከበኩር ልጃቸው የተደወለ ስልክ ሐጂን ያነቃቸዋል፡፡ የልጃቸውን ድምጽ የሰሙት ሐጂ በወላጅ አንጀት ከፍቅር እና ከእውነት በመነጨ ስሜት ደኅንነታቸውን ሲጠይቁ ያገኙት ምላሽ ግን ያልጠበቁት ነበር፡፡ ልጅ በጥላቻ ተሞልቶ እና በበቀል ተቀብቶ ለአባት ቀርቶ ለታላቅ የማይባል የስድብ ናዳ በሐጂ ጆሮ ይጎርፋል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ይላሉ ሐጂ ያስገረማቸውን የልጃቸውን ንግግር ሲያስታውሱ “ጠብቅ ቀን ሊወጣልን ነው፤ ሌላ ሳይኾን እኔ መጥቼ በገጀራ እገልሃለው፡፡ አንተ ለገንዘብ ስትል ሀገርክን የካድክ እና ሀገር የሸጥክ ነህ” ተባልኩ ይላሉ፡፡
መሰደባቸው አልገረማቸውም፤ ከልጃቸው የተወረወረው ዛቻም አላስደነገጣቸውም፡፡ ነገር ግን ይላሉ ሐጂ “የአሸባሪው ቡድን የከፋፍለህ ግዛው መርህ እና የጥላቻ ማኒፌስቶ እስከዚህ ድረስ ወርዶ ነበር? ስል እንድጠይቅ አስገድዶኛል ነው ያሉት፡፡
ሐጂ በዘመናት ትግላቸው ማንነታቸው ተመልሶ ማየታቸው አስደስቷቸዋል፡፡ ነገር ግን የልጃቸው ልብ ተመልሶ እና እውነቱን ተረድቶ የሚያዩበት ጊዜ እንዲመጣ አሁንም ይመኛሉ፡፡
በታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየአሸባሪውን ትህነግ አባላት በመደምሰስ በየግንባሩ የተፈጠሩ የአማራ ጀግኖች ተምሳሌትነት በሁሉም አካባቢ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አሳሰበ፡፡
Next articleጠላትን በአጭር ጊዜ ለማጥፋት የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ በቅንጅት እየሠሩ መሆኑን ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞ ገለጹ፡፡