
ባሕር ዳር፡ መስከረም 16/2012 ዓ/ም (አብመድ) በበዓሉ ወቅት ሊፈጠሩ የሚችሉ ድንገተኛ የእሳት አደጋዎችን ለመከላከል ዝግጁ መሆኑን የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር አገልግሎት አቅርቦት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡
በጽሕፈት ቤቱ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ መንግሥቱ ዘላለም ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት እንደተናገሩት ድንገተኛ አደጋዎችን ለመከላከል የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል፡፡ የእሳት አደጋ ሠራተኞች በበዓሉ ዕለት ሙሉ ጊዜያቸውን በሥራ ላይ እንደሚሆኑና የእሳት ማጥፊያ ተሽከርካሪም ዝግጁ መሆኑን ገልጿል፡፡
ከአቅም በላይ የሆነ የእሳት አደጋ ቢያጋጥም እንኳ በአፋጣኝ ለመቆጣጠር ባሕር ዳር ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ጋር በቅንጅት ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውንም አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡
በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የሚገኙ ስድስት ክፍለ ከተሞች፣ አራት ሳተላይት ከተሞችና ከከተማው 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ የሚገኙ 21 የገጠር ቀበሌዎች አገልግሎቱን ያገኛሉ ተብሏል፡፡ ከጎንደር፣ ከደሴና ከደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደሮች ጋርም ቅንጅታዊ አሠራር መፈጠሩ ተብራርቷል፡፡
የመከላከል ኃላፊነት የተሰጣቸው ተቋማት በሚደርሱባቸውም ሆነ በማይደርሱባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የእሳት አደጋ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸውም አስተባባሪው መክረዋል፡፡
እንደ አስተባባሪው የጥንቃቄ መልክት በበዓሉ የሃይማኖቱ ተከታዮች ችቦ አቀጣጥለው በቤት ውስጥ ሲንቀሳቀሱ በአጋጣሚ ሊወድቅ የሚችልን ፍም ሙሉ በሙሉ መጥፋቱን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ ደመራ ሲደምሩም እንደ ኤሌክትሪክና መሰል ተቀጣጣይ ቁሶች በሌሉበት ነፃ ቦታ መሆን እንዳለበት መክረዋል፡፡
ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ምግብና መጠጦችን ለማዘጋጀት በሚደረገው ሂደትም በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ማድረግ ሌላኛው ጥንቃቄ የሚሻው ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ድንገት የእሳት አደጋ ቢከሰት ደግሞ ፈሳሽ ባልሆኑ ነገሮች የሚፈጠሩ ድንገተኛ አደጋዎችን በውኃና ሌሎች ቁሶች ታግዞ ማጥፋት፣ እንደ ቤንዚን ባሉ ፈሳሽ ተቀጣጣይ ነገሮች የሚከሰቱ አደጋዎችን ደግሞ በአፈር፣ በአሸዋና በጆንያ በማፈን አየር እንዳያገኙ ማድረግ የመፍትሔ እርምጃዎች መሆናቸውን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡
የበለጠ ጉዳት የሚያስከትል ከሆነ ግን ለባሕር ዳር ከተማ በ058 220 00 22 ደውሎ አገልግሎት ማግኘት የሚቻል መሆኑን አስተባባሪው ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ሀይሉ ማሞ