የአሸባሪውን ትህነግ አባላት በመደምሰስ በየግንባሩ የተፈጠሩ የአማራ ጀግኖች ተምሳሌትነት በሁሉም አካባቢ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አሳሰበ፡፡

223
ባሕር ዳር: ነሐሴ13/2013 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ወቅታዊ ክልላዊና ሀገራዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ መረጃ ሰጥቷል፡፡ የክልሉ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በሁሉም አውደ ግንባሮች ከፍተኛ ድል የተገኘ መሆኑን ተናግረዋል። ጠላት መጠነ ሠፊ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ እንደደረሰበትም አቶ ግዛቸው አስረድተዋል።
በሰሜን ጎንደር ዞን በዛሪማ ከተማ የገጠር አካባቢዎችን አድርጎ ወደጎንደር እና አካባቢው ታላሚ በማድረግ ሊገባ የሞከረው 2 ሺህ የሚጠጋ ጠላት በአብዛኛው ተደምስሷል ብለዋል።
የወገን ኃይሎች በሚገባ ተደራጅተው የሽምቅ ውጊያ ጭምር በማድረግ ጠላት የያዛቸው አካባቢዎች ምቹ እንዳይሆኑ አድርገዋል ነው ያሉት። እየተካሄደ በሚገኘው አውደ ውጊያ ታሪክ ሲዘክራቸው የሚኖሩ በርካታ ጀብድ የፈጸሙ ጀግኖች መፈጠራቸውን አቶ ግዛቸው አስረድተዋል።
ክምር ድንጋይ ላይ አንድ ግለሰብን 11 ጠላቶችን መደምሰሱ በታሪክ ሲዘከር የሚኖር ነው ብለዋል። ይህ ጀግንነት መስፋት እንዳለበት ነው አቶ ግዛቸው የገለጹት።
“የአማራን ዘር ለማጥፋት ሕዝብን እያስነሳ፣ መውረር ብቻ ሳይሆን እንዲገድልና እንዲዘርፍ ትዕዛዝ የሰጠን ቡድን የአማራ ጀግኖች ሊፋለሙት ይገባል” ብለዋል። በሰሜን ጎንደርም አንድ አርሶ አደር ብቻውን ሆኖ አንድ ሙሉ የጦር መሳሪያ የጫነ ተሽከርካሪን እንዳወደመም ተናግረዋል። በየግንባሩ የተፈጠሩ ጀግኖች ተምሳሌትነት ወደ ሁሉም አካባቢ እንዲሰፋ አቶ ግዛቸው ጠይቀዋል።
አረመኔው ቡድን እድል ካገኘ የማይፈጽመው ሰይጣናዊ ድርጊት የለም ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ንጹሐንን በጅምላ እየገደለ ነው ብለዋል። በየደረሰበት አካባቢ ሁሉ ታዋቂ ሰዎችን እየገደለ እንደሆነም አስረድተዋል።”መንገድ እንዲያሳዩት ያስገድዳል፤ መንገዱን ካሳዩት በኋላ ግን ይረሽናል” ነው ያሉት።
ሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ አካባቢ አጋምሳ ላይ አንድ መንደር ሙሉ በሙሉ አጥፍቷል ያሉት አቶ ግዛቸው በየአካባቢው ወጣቶችን በመግደል እና በማፈን ላይ እንደሆነም ነው ያብራሩት። በደረሰበት ቦታ ሁሉ የግልና የመንግሥት ተቋማትን ይዘርፋል ድልድዮችን ሳይቀር ያወድማል ብለዋል።
ዳይሬክተሩ ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ጀምሮ አሸባሪው ቡድን 484 ሺህ ዜጎችን እንዳፈናቀለ አስረድተዋል። አቶ ግዛቸው እንዳሉት እነዚህን ዜጎች የማቋቋም ሥራ እየተሠራ ነው። በመሆኑም እንዲህ አይነት ግፎች ዳግም እንዳይፈጸሙ በአንድነት ጀግኖቹ የፈጸሙትን ገድል መድገም እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት።
የሚደረገው ትግል የሕልውና በመሆኑ ከትግሉ ጋር ተያይዞ የኑሮ ውድነቱን እንዲያሻቅብ የሚያደርጉ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ነው አቶ ግዛቸው የጠየቁት። ነጋዴዎች በተለይ በዚህ ወቅት ገበያዉን የማረጋጋት ኀላፊነት እንዳለባቸውም ተናግረዋል። ይሁን እንጅ “ኾን ብለው ምርትን የሚደብቁና ዋጋ በሚጨምሩ ነጋዴዎች ላይ የክልሉ መንግሥት የማያዳግም እርምጃ ይወስዳል” ብለዋል። ያለ አግባብ ዋጋን መጨመር ከሕልውና ዘመቻው ተነጥሎ እንደማይታይ ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያሳሰቡት።
አርሶ አደሮችም ይሁኑ ነጋዴዎች ምርትና ምርታማነትን በሚጨምሩ ሥራዎች ላይ ጠንክረው ሊሠሩ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ አሁን በአግባቡ የምርት ሥራ ካልተሠራ ወደፊት አስቸጋሪ ስለሚኾን ምርት ላይም ትኩረት መደረግ አለበት ነው ያሉት፡፡
በዚህ ወቅት የዘማች ቤተሰቦችን እርሻ ማረስ፣ ቤታቸውን መጠገን፣ ሁለንተናዊ ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አቶ ግዛቸው አሳስበዋል፡፡ የዘማች ቤተሰቦች ጉዳት እንዳይደርስባቸው እንክብካቤ ሊያገኙ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
ዘመቻዉን በተመለከተ ኅብረተሰቡ ተዓማኒ ከኾኑ ሚዲያዎች ላይ ከሚያገኘው መረጃ ውጭ አላስፈላጊ መረጃን በመውሰድ ወደ ውዥምብር መግባት እንደሌለበት አስረድተዋል፡፡
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየአማራ ጀብድ በሰሜን ጎንደርም ተደግሟል፡፡
Next articleወላጅ እና ልጅን የነጠለው የትህነግ ሴራ።