
ባሕር ዳር: ነሐሴ13/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ትህነግ በአማራ ክልል ጦርነት ከከፈተበት ጊዜ አንስቶ የመንግሥት እና የሕዝብን ሀብት እና ንብረት በመዝረፍ፣ በማውደም እና ንጹሃን ዜጎችን በመግደል ላይ ይገኛል፡፡ የአሸባሪውን ትህነግ ወረራ ለመቀልበስ የሰሜን ጎንደር ሕዝብም በተለይም ደግሞ ወጣቶች ከሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ከክልሉ የጸጥታ ኀይል ጋር በመቀናጀት እየተፋለሙ እንደሚገኙ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ያለዓለም ፈንታሁን ለአሚኮ ገልጸዋል፡፡
በተለይም ባለፉት አራት ተከታታይ ቀናት በተካሄደው ጦርነት ወጣቶች በርካታ ታጣቂዎችን በመደምሰስ፣ በርካታ የነፍስ ወከፍ እና የቡድን የጦር መሳሪያ በመማረክ ከፍተኛ ጀብዱ መፈጸማቸውን ነው አቶ ያለዓለም የገለጹት፡፡ በውጊያው ከፍተኛ ጀብዱ ከፈጸሙት መካከል አርሶ አደር ተስፋሁን ይገኙበታል፡፡ አርሶ አደሩ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን በቦንብ አራት የጠላት ታጣቂዎችን እስከ ተሸከርካሪያቸው ማውደሙን አስተዳዳሪው ነግረውናል፡፡
‹በር ማሪያም› በምትባል ቀበሌም የቀበሌው አስተዳዳሪ አራት የአሸባሪው ትህነግን ታጣቂዎች በሬዎቹን አርደው እየበሉ ባሉበት ቦታ መደምሰሱን ገልጸዋል፡፡ አንድ ታዳጊም የአባቱን አብራራው የጦር መሳሪያ በማንሳት ሶስት ታጣቂዎችን በመግደል ሶስት የጦር መሳሪያ መማረኩን አቶ ያለዓለም ተናግረዋል፡፡
አንድ የቀበሌ አመራርም ካደራጀው ኀይል ጋር በመቀናጀት በወሰዱት እርምጃ ከፊሉን የጠላት ጦር በመደምሰስ የመገናኛ ሬዲዮ እና የዲሽቃ መሳሪያ መማረካቸውን ነግረውናል፡፡ ለአብነት እነዚህን አርሶ አደሮች እና ወጣቶች የፈጸሙትን ጀብዱ አነሳን እንጅ በርካታ የአካባቢው ወጣቶች በመደራጅት ግንባር ላይ ለሚገኘው ሠራዊት ሎጀስቲክስ በማቅረብ፣ ቁስለኞችን በማከም፣ አካባቢያቸውን በተደራጀ መንገድ በመጠበቅና ሰርጎ ገቦችን እያደኑ በመያዝ ከፍተኛ ጀብዱ እየፈጸሙ እንደሚገኙ አንስተዋል፡፡
በዚህ ወቅት በዞኑ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ሕዝባዊ ትግሉን በመቀላቀል እና በመፋለም የሕይዎት መስዋእትነት ጭምር እየከፈሉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ አቶ ያለዓለም እንዳሉት በዚህ ወቅት የጠላት ጦር ከሁለት ተቆርጦ በወገን ጦር ተከብቦ መውጫና መግቢያ አጥቷል፡፡
አሸባሪው ትህነግ በውጊያ የደረሰበትን ሽንፈት ለመደበቅ በፎቶ ሾፕ የተሰሩ ፎቶዎችን በመለጠፍ ድብ ባሕርን እና ደባርቅን እንደተቆጣጠር አድርጎ የሚያናፍሰው ፕሮፖጋንዳ ጥርሱን የነቀለበት የተለመደ መሆኑን በመገንዘብ ማኅበረሰቡ እካባቢውን እንዲጠብቅ እና ትግሉን እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ