“ከ214 ሺህ በላይ የሰው ኀይል በማሠማራት የዘማች ቤተሰብ ማሳን የመንከባከብ ሥራ ሠርተናል” የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ መለስ መኮነን (ዶ.ር)

169
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 13/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በህልውና ዘመቻው ለሚሳተፉ ሚሊሻዎች እና ምልስ የሠራዊት አባላት ቤተሠቦች እየተደረገ ባለው እንክብካቤ ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ መለስ መኮነን (ዶ.ር) አሸባሪው የትህነግ ቡድን የደቀነውን የህልውና አደጋ ለመመከት በርካታ ሚሊሻዎች እና ምልስ የሠራዊት አባላት ወደ ግንባር መዝመታቸውን አንስተዋል፡፡
ኀላፊው በአማራ ክልል እስካሁን 3 ነጥብ 83 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑንም አብራርተዋል፡፡ በዘር የተሸፈነው የሚሊሻና የምልስ ሠራዊት ማሳ የአካባቢውን ማኅበረሰብ በማስተባበር የማረስ፣ የመዝራት እና የማረም ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡
“ከ214 ሺህ በላይ የሰው ኀይል በማሠማራት የዘማች ቤተሰብ ማሳን የመንከባከብ ሥራ ሠርተናል” ብለዋል፡፡
ዶክተር መለስ እንዳሉት እስካሁን
•10 ሺህ 747 ሄክታር መሬት በአካባቢው ማኅበረሰብ ታርሷል፤
•በ5 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአረም ሥራ ተከናውኗል፤
•10 ሺህ 330 ችግኞች በዘማች ቤተሰቦች ማሳ ላይ መተከሉን አንስተዋል፡፡ የስድስት ዘማች ቤተሠቦች ቤት መጠገኑንም ኀላፊው ጠቁመዋል፡፡
•539 ኩንታል ምርጥ ዘር አቅማቸው ዝቅተኛ ለሆኑ የዘማች ቤተሠቦች ድጋፍ ተደርጓል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
•በሥራው ላይ 214 ህ 77 አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል፡፡ ማኅበረሰቡ ገንዘብ በማዋጣት እና በማሰባሰብ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ከ33 ሺህ በላይ የግብርና ሠራተኞችም ለሁለተኛ ጊዜ የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለህልውና ዘመቻው መስጠታቸውን ኀላፊው አንስተዋል፡፡
ዶክተር መለስ አርሶ አደሩ ከግብርና ሥራው ሳይለይ አካባቢውን ነቅቶ እንዲጠብቅ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
በኢትዮጵያ ለምግብነት ከሚውለው ምርት 35 በመቶ ያህሉን የአማራ ክልል እንደሚሸፍን ዶክተር መለስ ጠቅሰዋል፡፡ በክልሉ ይከሰታል ተብሎ የሚገመተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከልም ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም አስታውቀዋል፡፡
በቀጣይ ዓመት የምግብ እህል እጥረት እንዳይከሠት የኅብረት ሥራ ማኅበራት በክልሉ የሚመረተውን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ በመግዛት ለሸማቹ ለማቅረብ በጋራ ለመሥራት እንቅስቃሴ መጀመሩንም ኀላፊው ጠቁመዋል፡፡
ዶክተር መለስ በዚህ ዓመት ከእርሻ ሥራቸው የተስተጓጎሉ አካባቢዎችን በቀሪ እርጥበት እና በመስኖ በመሸፈን በቂ ምርት ለማምረት ዝግጅት መደረጉንም አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleሽብርተኛው እና ወራሪው ትህነግ በወረራቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ እየደረሰበት መሆኑን የክልሉ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ ገለጹ፡፡
Next articleየሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ እና የተቀናጀ ሕዝባዊ ሠራዊት ጋሸና እና አካባቢውን ተቆጣጣረ።