ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቱርክ ያደረጉት የሥራ ጉብኝት ውጤታማ እንደነበር የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

195
ባሕር ዳር: ነሐሴ13/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በቱርክ የተሳካ ጉብኝት አድርገዋል። ጉብኝቱ የሁለቱን ሀገራት የግንኙነት ጥልቀት ያሳየም እንደሆነም ገልጸዋል። መሪዎቹ በሁለቱ ሀገራት ግንኙነትና በቀጣናዊ ጉዳይ ላይ ውይይት አካሂደዋል። ቱርክና ኢትዮጵያም በወታደራዊ ፋይናንስ የትብብር ስምምነት፣ የወታደራዊ ማዕቀፍ ስምምነት፣ የፋይናንስ ድጋፍን የተመለከተ የትግበራ ሰነድ፣ በውኃ ዘርፍ በጋራ ለመሥራት ስምምነቶችን እንደፈጸሙ አብራርተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ጋር በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል ላይ ስላለው ሁኔታ በስፋት ውይይት ማካሄዳቸውን አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ችግሮችን ለመፍታት የሄደችበትን ርቀትና አሜሪካም የያዘችው አቋም ትክክል አለመሆኑን አስረድተዋቸዋል ነው ያሉት።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ አሜሪካ በኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታ ላይ የያዘችው አቋም አሸባሪውን ቡድን የሚደግፍና የሀገራቱን የቆየ ግንኙነት የማይወክል መሆኑን ነግረዋቸዋል ብለዋል አምባሳደር ዲና።
በማይካድራና በአፋር በንጹሐን ላይ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ በዝምታ ማለፋቸውም ተገቢ እንዳልሆነ እንዲረዱ ተደርጓል፤ በብሔራዊ መግባባት ላይም የኢትዮጵያ መንግሥት ትኩረት እንደሚሰጥ ገለፃ መደረጉን አስረድተዋል።
የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን በበኩላቸው ለኢትዮጵያ አንድነትና ነፃነት ትኩረት እንሰጣለን ፤ በቀጣናው ያላትን ሚናም እናውቃለን ብለዋል። አሜሪካ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ እንድትፈታ ፍላጎቷ እንደሆነ መግለፃቸውን ጠቁመዋል።
በሳምንቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጪ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት እውቅና ተሰጥቷል ያሉት አምባሳደር ዲና አባላቱ በምክር ቤቱ በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ለሠሩት ሥራ እውቅና ለመስጠት ያለመ ነው ብለዋል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከሰሞኑ ያወጣው ሪፖርት የተሳሳተ፣ ለአንድ ወገን ያደላና የመረጃ አሰባሰቡም ትክክል አለመሆኑን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።
የአሸባሪው ቡድን የመንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ባለመቀበሉና ወረራ በመፈጸሙ ከ300ሺህ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን ለቀሪው ዓለም የማሳወቅ ሥራ ተሠርቷል፤ በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ኢምባሲዎችም ወቅታዊ ሁኔታዎችን ለማስረዳት ጥረት መደረጉን ነው የተናገሩት።
በኳታር ፣ በአልጀሪያ፣ በሕንድ፣ በዋሽንግተንና ሌሎችም አካባቢዎች የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲውን የሚደግፉና ኢንቨስትመንቱን የሚያስተዋውቁ ውይይቶችና ስምምነቶች ተካሄደዋል፤ በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ዜጎች ከመከላከያ ጎን መቆማቸውን የሚያሳዩ ሥራዎች ተሠርተዋል፤ ለተፈናቀሉ ዜጎችና ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድጋፍ የማሰባሰብ፣ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን ጫና የመቃወም ተግባራት መከናወኑን ቃል ዐቀባዩ አስረድተዋል።
አምባሳደር ዲና ከጅቡቲ፣ ከሱዳንና ከየመን ዜጎችን የመመለስ ሥራዎች መከናወኑን፤ከየመን ተጨማሪ ዜጎችን ለመመለስ የሚቻልበትን መንገድ የሚያመቻች ቡድንም ወደ ሀገሪቱ በመሄድ የጉዞ ሰነዶችን የሚመለከቱ ሥራዎች መሠራታቸውን፤ ከሳዑዲ አረቢያ ዜጎችን ለማስወጣትም መጀመሩን እና በሳምንት ሦስት ቀን የሚካሄድ በረራ መፈቀዱን አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፡-ዘመኑ ታደለ-ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“አይሻገሩም፤ ከተሻገሩ ደግሞ አፈር ለማልበስ አንሳሳም” የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አስተዳዳሪ
Next articleሽብርተኛው እና ወራሪው ትህነግ በወረራቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ እየደረሰበት መሆኑን የክልሉ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ ገለጹ፡፡