
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 13/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የሁመራ ከተማን ከፀጥታ ስጋት ሙሉ በሙሉ ነፃ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ርዕሰ መዲና ሁመራ ከተማ የአካባቢው የንግድ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ኮሪደር ናት። ከተማዋ ኢትዮጵያን ከኤርትራ ጋር ከሚያዋስነው የተከዜ ወንዝ ዳር ከመከተሟ በተጨማሪ ከሱዳን ድንበር በቅርብ ርቀት ላይም ትገኛለች።
ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት አሸባሪው ትህነግ በአካባቢው በነበረው መዋቅራዊ ብልሹ አሠራር የአካባቢውን ጸጋ በአግባቡ ተጠቅሞ ከመልማት እና ከማልማት ይልቅ ኮንትሮባንድን ጨምሮ በርካታ ሕገ ወጥ ድርጊቶች በብዛት ይስተዋሉባት ነበር። ለረጂም ጊዜያት የዘለቀውን ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ለማስቆም፣ ለነዋሪዎቿ የምትመች ከተማ ለማድረግ እና የሕልውና ዘመቻውን በድል አድራጊነት ለማጠናቀቅ በአካባቢው ጥብቅ የፀጥታ ቁጥጥር እየተደረገ ነው ተብሏል።
በቅርብም የፀጥታ ኀይሉ ሃሺሽ እና የእጅ ቦንቦችን ጨምሮ በሕገ ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ አካላትን በቁጥጥር ስር ማዋሉን መዘገባችን ይታወሳል። ከተማዋን ሙሉ በሙሉ ከሕገወጥ ድርጊትና ከፀጥታ ስጋት ነፃ ለማድረግ ያለመ ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ የሥራ ኀላፊዎች፣ የፀጥታ መዋቅሩ፣ የከተማዋ ነዋሪዎች እና ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች ያላቸው ሚና ተገምግሟል። ጥብቅ የኬላ ፍተሻ፣ የተጠናከረ የፀጥታ አደረጃጀት እና ፈጣን የፓትሮል እንቅስቃሴ መኖሩ ተጠቁሟል።
ከተማዋን ጨምሮ አካባቢው ድንበር በመሆኑ የውስጥ እና የውጭ ጠላቶች በብዛት እና በስፋት የሚንቀሳቀሱበት መሆኑን ነዋሪዎቹ አንስተዋል፡፡ አሸባሪው የትህነግ ቡድን ሰርጎ ገቦችን በማሰማራት ፀጥታውን ለማደፍረስ ያለዕረፍት እንደሚሰራም ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ የፀጥታ ስጋቶችን ሙሉ በሙሉ በማምከን ጥምረት የፈጠሩ የሀገር ታሪካዊ ጠላቶች ደብዛቸው እስኪጠፋ ያለዕረፍት መሥራት ይገባል ብለዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሸተ ደምለው የሕልውና ዘመቻው ለዞኑ ሕዝብ የተለየ እንድምታ እንዳለው ገልጸዋል። የሕልውና ዘመቻው ሁለት ክንፎች አሉት ያሉት ዋና አስተዳዳሪው የአሸባሪውን ቡድን ርዝራዦች ከማጽዳት በተጨማሪ የውጭ ተልዕኮ ተቀባዮችን ማምከን ይገባል ብለዋል። የውጭ ተልዕኮ ተቀባዮችን ለማምከን የሀገራት አዋሳኝ የሆነው ይህ አካባቢ የተለየ ተልዕኮ ይኖረዋል ብለዋል።
የጠላት ቡድን በርካታ ጊዜ የተከዜን ወንዝ ተሻግሮ ለመምጣት ሞክሮ የሚገባውን አግኝቷል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው “አይሻገሩም፤ ከተሻገሩ ደግሞ አፈር ለማልበስ አንሳሳም” ብለዋል።
ትግሉ ኢትዮጵያን ለመታደግ ነውና እስከቀራኒዮ ድረስ እንቀጥላለን ብለዋል ዋና አስተዳዳሪው። ቃፍታ ሁመራ በፍቅር ለሚቀርቡ የበርሃ ገነት ነች ያሉት አቶ አሸተ ሊወጉን ለሚመጡ ቡድኖች ግን እሾክ ትሆንባቸዋለች ሲሉ አሳስበዋል።
ዋና አስተዳዳሪው የሕልውና ዘመቻው እስኪጠናቀቅ ድረስ ለሕዝቡ “ጠርጥሩ፣ ወጥሩ በመጨረሻም መንጥሩ” ሲሉ የሥራ አመራር ሰጥተዋል።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው -ከሁመራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ