
የአማራ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በዕለታዊ መረጃው እንዳለው አሸባሪውና ወራሪው ትህነግ ወረራ በፈፀመባቸው ሁሉም አካባቢዎች የፀጥታ ኃይላችንና ሕዝባችን በተቀናጀ ሁኔታ እየመከቱት ይገኛል።
የአማራ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዕለታዊ ያደረሰን መረጃ ቀጥሎ ቀርቧል:-
አሸባሪውና ወራሪው ትህነግ ከወረራቸው አካባቢዎች መካከል ወልዲያና አካባቢው የፀጥታ ኃይላችን በቅንጅት እያደረገ ባለው ተጋድሎ ወሳኝና ስትራቴጅክ ቦታዎችን እየያዘ ይገኛል። በውስን መስዋዕትነት በርካታ የጠላት ኃይል ተመቷል፡፡ ጠላት በፈለገው አቅጣጫ መንቀሳቀስ እንዳይችል ተደርጓል ነው ያለው፡፡
በጋይንት በኩል የገባው ጠላት ባሰበው ልክ መንቀሳቀስ እንዳይችል ተደርጎ ቀለበት ውስጥ ገብቷል፡፡ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የምድር ኃይል፣ አየር ኃይላችን እና የአማራ ክልል የፀጥታ ኃይላችን በሰማይና በምድር እጅግ ስኬታማ የማጥቃት ስልት ሲከተሉ ውለዋል፡፡ በአየርም ሆነ በምድር በጠላት ላይ ከፍተኛ ሰብዓዊ ኪሳራ ደርሷል፡፡
የጠላት ቁስለኞች የህክምና እርዳታ የማያገኙበት ሁኔታ በመኖሩ ኪሳራውን ከዕለት ዕለት እየጨመረበት መጥቷል፡፡
ተከዜን ተሻግሮ በማይጠምሪ በኩል የገባው የአሸባሪውና ወራሪው ትህነግ መንጋ ዛሬም እንደሰሞኑ ሽንፈቱን ሲከናነብ ውሏል፡፡
በወልዲያ፣ በላሊበላና ጋይንት በኩል የነበረው ጠላት፣ በተለይም ለዘረፋና ለጭፍጨፋ ያሰማራው መንጋ፣ የዘረፈውን ንብረት ጭኖ ወደ ትግራይ ለመውጣት በዋግኽምራ በኩል ጥረት ሲያደርግ ጀግናው የዋግ ሚሊሻና ሕዝብ በደፈጣ እየቀጣው ይገኛል። ይህም ሁኖ ሰቆጣ ከተማ ውስጥ ከፍተኛ ዝርፊያ የፈጸመ ሲሆን፤ በዘረፋው ቁልፍ ማህበራዊ ልማቶች ላይ አተኩሯል፡፡ በዚህ ተፈራ ኃይሉ መታሰቢያ ሆስፒታል፣ ሰቆጣ መምህራን ኮሌጅ ፣ አመልድ፣ እርሻ ምርምር፣ ቴሌኮምዩኒኬሽንና የግሉ ዘርፍ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ላይ ውድመትና ዘረፋ ፈጽሟል፡፡
አሸባሪው ትህነግ “ሒሳብ አወራርዳለሁ” ብሎ በተነሳው መሰረት በወረራቸው አካባቢዎች ታዋቂና ተሰሚነት ያላቸው ግለሰቦችን፣ ባለሀብቶችን፣ በሕዝብ ዘንድ ተስፋ የተጣለባቸው ተጽዕኖ ወጣቶችንና የእምነት አባቶችን ቤት ለቤት እየዞረ አፍኖ ወስዷል፤ ከፊሉንም ገድሏል።
ሕዝባችን በአጠቃላይ፣ የሕዝብ ተስፋ የሆኑትን ልሂቃኑን ለማጥፋት አቅዶ በተነሳው መሰረት የጥፋት ሰይፉን መዝዟል። አጋምሳ ላይ ሙሉ አንድ መንደር እስከማጥፋት የደረሰ የንፁሃን ጅምላ ጭፍጨፋ ፈጽሟል፡፡ ማይካድራ ቁጥር ሦስት ተፈጽሟል፡፡ ማይካድራ ቁጥር ሁለት በአፋር ጋሊኮማ እንደተፈጸመ ይታወሳል፡፡ እነዚህ ጭፍጨፋዎቹ በጦር ወንጀለኝነት እንደሚስፈርጁት አንዳንድ ዓለም-አቀፍ ሚዲያዎች እየዘገቡት ይገኛል።
የዚህን አሸባሪና ወራሪ ቡድን የጥፋት ተልዕኮ የተረዳውና በግንባር አካባቢ የሚገኘው ሕዝባችን ከወገን ጦር ጎን ተሰልፎ በጀግንነት እየተፋለመ ይገኛል፡፡ ሕዝባችን አጋጣሚውን ተጠቅሞ የጠላትን እንቅስቃሴ ለመግታት መረጃ በመስጠት፣ አካላዊ ፍልሚያ በማድረግ ሠራዊቱን በማገዝ ላይ ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሸባሪውና ወራሪው ትህነግ ሕዝባችን ሲታገለው ለማጭበርበር ጥረት የሚያደርግባቸው ሁኔታዎች በስፋት ተስተውለዋል። ከአካባቢው አለባበስ ጋር በመመሳሰል፣ ዕድሜቸው የገፉ (በዕድሜ ጠና ያሉ) አባላቱን ከፊት በማድረግ ሰርጎ በመግባት፣ የአካባቢው ሚሊሻና የወገን ጦር በመምሰል ለማለፍ ጥረት ያደረገባቸው አካባቢዎች አሉ፡፡ በተጨማሪም “እኛ እናንተን አንነካም” ብሎ ከገባ በኋላ የማህበረሰቡን ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ለይቶ ገድሏል፡፡
የግለሰቦችን ሀብትና ንብረት በመዝረፍ፣ ቁልፍ የማህበራዊ ልማት ተቋማትን ኢላማ በማድረግ የቻለውን በመዝረፍ፤ ያልቻለውን በማውደም፤ የክልላችንና የሕዝባችን ደመኛ ጠላት መሆኑን በተግባር አሳይቷል፡፡
በተመሳሳይ የመንገድ አቅጣጫዎችን ለሚያመላክተው ገንዘብ እንደሚከፍል ቃል በመግባት፣ በአስገዳጅ ሁኔታና በጫና ግለሰቦች መንገድ ከመሩት በኋላ ሲመለሱ መረጃ እንዳያወጡ በሄዱበት በመግደል አረመኔነቱን አሳይቷል።
በገባባቸው ቦታዎች በተደራጀ መልኩ መንቀሳቀስ ባልቻለበት በየመንደሩና ከተማው እየገባ ሽብር ለመፍጠርና ለመዝረፍ እየጣረ ያለው አሸባሪው ትህነግ፣ በተደራጀ ሁኔታ እየተመታ ቢሆንም፣ እያደረሰ ካለው ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ አኳያ መላ የክልላችን ሕዝብ ዳር እስከዳር እንደሕዝብ ተነስቶ ደመኛ ጠላቱን ሊደመስስ ይገባል፡፡
በግንባር አካባቢ ያለው ሕዝባችን ጠላቱን ለመታገል እያሳየ ያለው ርብርብ ከፍ ያለ አድናቆት የሚሰጠው ነው። ከግንባር በራቁ የክልላችን አካባቢዎች ያለው ሕዝባችን፣ በተለይም ዕድሜውና ቁመናው ለውጊያ ብቁ የሆነ ሁሉ ወደግንባር ዘምቶ ጠላቱን እንዲፋለም ጥሪያችንን በድጋሚ እናቀርባለን፡፡
አሸባሪውና ወራሪው ትህነግ ከሚተኩሰው ጥይት ይልቅ በቀዳሚነት የሀሰት ወሬና ማደናገሪያ በመፍጠር ሕዝብ ቦታውን ለቆ እንዲሄድ በማድረግ የፈለገውን ዘርፎና ጨፍጭፎ ወደቀጣይ ኢላማው መሄድን እንደ ስልት አድርጎታል። በመሆኑም በጠላት ወሬ ባለመረበሽ፣ የሚመለከተው አካልና የፀጥታ ኃይላችን የሚሰጡትን ተልዕኮ በመከተል ጠላትን በየቀየው ሆኖ መታገል ይኖርበታል።
ሕዝብ ቦታውን ካልለቀቀ ይህ ኃይል በቀላሉ ሰርጎ መግባት፣ መዝረፍና ውድመት ማድረስ እንደማይችል ያውቀዋል። ጠለት በዋነኛነት ሕዝባችንን አስገድዶ ወይንም አባብሎ መንገድ እንዲያሳየው የሚጠይቅ ሲሆን፤ መንገድ ካገኘ በኋላ መጀመርያ መንገድ መሪዎቹ ላይ እርምጃ በመውሰድ ተጨማሪ ዘረፋና ጭፍጨፋ ይፈፅማል።
በመሆኑም የጠላት ኃይል አጭበርብሮ እንዳያልፍ በመጠንቀቅ፣ መረጃ ባለመስጠት፣ በግድ መንገድ ጠቁሙኝ በሚልበት ወቅት ባለመጠቆም አስገዳጅ ከሆነም በወገን ጦር ቀለበት ውስጥ የሚገባበት ዕድል በመፍጠር ሕዝብንም ራስንም በማዳን ሕዝባችን የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲወጣ ጥሪ እናቀርባለን። መንግሥታችንና ሕዝባችን ተገዶ የገባበት ጦርነት ፍትሐዊ በመሆኑ ማሸነፋችን ጥርጥር የለውም፡፡