
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 12/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ ከ400 በላይ ወጣቶች እንዲሁም ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በአዲስ አበባ ምክክር እያካሄዱ ነው።
በውይይቱ ኢትዮጵያ በምን አይነት ሁኔታ ላይ ትገኛለች የሚለውን አሁናዊና የቀደመ ቁመናዋን በማየት ከመቸውም ጊዜ በላይ አንድነታችን ጠብቆ በተግባር መታየት እንዳለበት የብልጽግና ወጣቶች ሊግ ምክትል ፕሬዝዳንት አክሊሉ ታደሰ ገልጸዋል፡፡
ባለፉት 30 ዓመታት የትህነግ መራሹ የሽብር ቡድን በኢትዮጵያ ጠልነት ላይ የቆመ አካሄድን መከተሉ አሁን ለገጠመን ችግር ባለቤት ነው ያሉት አቶ አክሊሉ በተለይ አንድነት እንዳይኖር፣ ወደብ አልባ እንድንሆን እና የኢኮኖሚ አሻጥርን በመሥራት ጠላትነቱን አሳይቷልም ብለዋል ባቀረቡት ጽሑፍ።

ባለፉት ዓመታት አሸባሪው ትህነግ ልዩነት እና የተሳሳተ የታሪክ ትርክት ላይ መሥራቱ አንዱ አንዱን እንዲጠራጠር አድርጓል፤ ይህ ደግሞ ከኢትዮጵያ ጠልነት ፖሊሲው የተነሳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አሸባሪው ቡድን ላይመለስ እንዲቀበር የህልውና ትግሉን ሁላችንም መደገፍ አለብን ብለዋል።
አሁን ላይ ምእራባውያን በኢትዮጵያ ጫና ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ ያሉት ለነሱ ታዛዥ መንግሥት እንዲኖር በመፈለግ መሆኑንም አቶ አክሊሉ ጠቅሰዋል፡፡ በሀገር ጉዳይ የማይደራደር መንግሥት መምጣቱና ኢትዮጵያ ቀጣናውን በሁሉም መስክ ለማስተሳሰር የሄደችበትን መንገድ ለመስበር ምእራባውያን እጃቸውን እኛ ላይ ቀስረዋል፤ ለዚህ መፍትሔው ደግሞ ጸንቶ በጋራ መቆም ነውም ብለዋል።
ለጥቅማቸው እውነታን በመካድ የሚጮሁ የመገናኛ ብዙኃንን የሚያራግቡትን የተሳሳተ መረጃ በመመከት በኩልም ወጣቶች ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠይቋል።

አንድነታችን መጠበቅ፣ ላልተገባ የውሸት ፕሮፖጋንዳ ተጋላጭ አለመሆን፣ አካባቢን ነቅቶ መጠበቅ፣ ጠላትን አቅልሎ አለመገመት፣ በየተሰማራንበት የሥራ መስክ ሁሉ ውጤታማ መሆን፣ ድምጻችንን ለዓለም በተለያዩ መንገዶች ማሰማት እንደሚገባም ተጠቅሷል፡፡
በህልውና ዘመቻው ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ በማድረግና በግንባር በመዝመት ወጣቶች ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም ተጠይቋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች አሸባሪውን የትህነግ ቡድን ለመደምሰስ ሁሉንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡
አንድነትን የሚፈታተኑ ሁኔታዎችን በብስለት መፈተሽና ሀገርና ሕዝብን ማስቀደም ላይ ሁሉም ሊሠራ እንደሚገባም ከተሳታፊዎች ሐሳብ ተነስቷል፡፡
ዘጋቢ፡- ጋሻው ፈንታሁን
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ