
ባሕር ዳር፡ የካቲት 22/2011 ዓ.ም(አብመድ) ይስማ ንጉስ ላይ ታሪኩን የሚዘክር ሙዚዬም እየተገነባ ነው፡፡

ይስማ ንጉስ ( ንጉሱ ይስማ) በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ ውጫሌ በተባለ ሥፍራ ይገኛል፡፡ ይስማ ንጉስ የቦታ መጠሪያ ነው፤ ‹ጉዳዩን ንጉሱ ይስማው› ከሚለው ንግግር የተወሰደ እንደሆነም የታሪክ አካል ከሆኑ ሰነዶች ላይ ተጽፏል፡፡ ለአድዋ ጦርነት መነሻ የሆነው ሴራ የተጎነጎነበት ሥፍራም ይሄው ነው ይስማንጉስ፡፡
አሁን ይስማ ንጉስ ላይ የአድዋ ድል 123ኛ ዓመቱን በሚደፍንበት ዓመት ሙዚዬም እየተገነባ ነው፡፡ የመሰረት ድንጋዩ የተቀመጠውም አምና ነበር፡፡ የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ነው ከ25 ሚሊየን 7መቶ ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ የባህል ማዕከሉን እያሰገነባ ያለው፡፡
የይስማ ንጉስ የባህል ማዕከል ግንባታ ዋናውን የመግቢያ በር ከታሪኩ ጋር ለማስተሳሰር ታስቧል፡፡ ለዚህም ለአድዋ ጦርነት ምክንያት ከሆነው አንቀጽ 17 ጋር በማስተሳሰር በግዕዝ ፲፯ ቁጥርን ሊገልፅ በሚችል መልኩ ንድፍ ተሰርቶለታል፡፡
ግንባታዉ ከታሪኩ ጋር ቁርኝት ባላቸዉ ንድፎች ነዉ እየተገነባ ያለዉ፡፡ የሙዚየም ህንፃ ፤ ካፍቴሪያ እና ዋና መግቢያ በርን ያካተተ ነው፡፡ የባህል ማዕከል ግንባታው ከ62 በመቶ በላይ መድረሱንም ሰምተናል፡፡
የፕሮጀክቱ የቦታ ርክክብ የተደረገዉ ጥር 18/2010 ዓ.ም ነበር፡፡ የካቲት 26/2010 ዓ.ም ነው የግንባታዉ ስራ የተጀመረው፡፡ የይስማ ንጉስ የባህል ማዕከልን ግንባታ በ720 የስራ ቀናት ለማጠናቀቅ ታቅዷል፡፡
ዘጋቢ፡- አዩብ ሙሃመድ